fbpx

HT

ሐበሻ ታይምስ ሚዲያ

AMHARIC

ክቡር ጠ/ሚ በህውኃትን የበላይነት ፈንታ የኦህዴድን የበላይነት እንዳያመጡብን እሰጋለሁ

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር በህውኃትን የበላይነት ፈንታ የኦህዴድን የበላይነት እንዳያመጡብን እሰጋለሁ
(አሳዬ ደርቤ )

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር እስካሁን ድረስ እርስዎም ፈገግ ብለው ስለ አገራዊ ፍቅር ሲያስተምሩን ሰንብተዋል፡፡ እኛም ከአፍዎ ጠብ የሚለውን ‹ማር› እየቀሰምን ስንደግፍዎና ስንደመርልዎ ከርመናል፡፡

አሁን ግን ፈገግታዎንና ንግግርዎን ቆጠብ አድርገው ኮስተር በማለት ወደ ስራ ገብተዋል፡፡ ስለዚህ እኛም ለእርስዎ ያለንን ፍቅር ሳንቀንስ ስጋታችንን ብናካፍልዎ አይከፋዎትም ብዬ አስባለሁ፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር ለባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ሲመራን የነበረው መንግስት በዋነኝነት ሲወቀስ ከነበረባቸው ነገሮች መሃከል ዋነኛው…. ስልጣኑን ሙጥጥ አድርጎ ለአንድ ድርጂት ማስረከቡ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ደግሞ ስሙ ሲብጠለጠልባቸው የነበሩ በርካታ ነገሮች ያሉ ቢሆንም በአዲስ ሃይል በተተኩ አመራሮች ላይ ጥይትና ቃላት ማባከኑ አይጠቅምምና እሱን ችላ ብዬ ‹አሁን› ላይ አተኩራለሁ፡፡

ያው እርስዎም እንደሚያዉቁት የህብረተሰቡ ጥያቄ የስልጣን የበላይቱም ሆነ ተጠቃሚነቱ ከነባሩ አካል ወደ ሌላ አካል እንዲተላለፍ ሳይሆን ‹እንዲከፋፈል› የሚጠይቅ ነው፡፡ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች በማንኛውም ልማት ላይ እኩል ተጠቃሚ የሚሆኑበት ስርዓት እውን እንዲሆን የሚያሳስብ ነው፡፡

እናም ይህ ጥያቄ ‹በኢህአዴግ ሊመለስ አይችልም‹ የሚል እምነት ስለነበረ የህዝቡ ትግል ስርዓት መቀየር ላይ ያጣጠረ እንደነበር ግልጽ ነው፡፡ በመሃል ግን ከምንጠላው ድርጅት ውስጥ እርስዎን ያህል መሪ ተከሰተና ጥያቄያችንንም ሆነ ተስፋችንን አስረከብንዎ፡፡

ይሄም ሆኖ ግን በባለፉት ጊዜያት ስንፈነጥዝ የነበረው የሚያባርሯቸውን በማየት እንጂ የሚተኳቸውን አመራሮች ፐሮፋይል በመመልከት አልነበረም፡፡

አሁን ላይ ግን ከተሻሩት ሰዎች ላይ ያነጣጠረ እይታችንን አንስተን የሚሾሙት ላይ ስናሳርፈው ወንበሩ ላይ ከተቀመጡት ሰዎች መሃከል የኦሆዴድ ሰዎች መብዛታቸውን አየን፡፡ (በተለይ በዋና ዋና የስልጣን ቦታዎች ላይ!)

ካየነውም ነገር ተነስተን አስተያየታችንን ለመስጠት ስንነሳሳ…. ለአገራችንም ሆነ ለእርስዎ ዘላቂ መረጋጋት ስንል እንጂ ‹‹የእኔ ብሔር በበቂ ሁኔታ አልተወከለም›› ወይም ደግሞ ‹‹የሚሾመው ሁሉ ለምን ከኦህዴድ ብቻ ይሆናል?›› ከሚል ቁንጽል ሃሳብ በመነሳት አይደለም፡፡

ይልቅስ ለአንዱ የሚሰጡት መልስ ለሌላው ጥያቄ እንዳይሆን፣ የአንዱን ችግር ሲፈቱ ለሌላው አካል ቅዋሜ እንዳይፈጥሩ በመስጋት ነው፡፡

የኔ ፍላጎት እርስዎ ተወዳጅነትን ያገኙበትን ሃገራዊ ስሜት ተጻራሪ ፍላጎት ባላቸው ሰዎች ግፊት ተመርተው ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ያገኙትን ፍቅር እንዳያጡት ከማሰብ የሚቀዳ ነው፡፡

ስለሆነም ‹‹ታሪክ ራሱን ይደግማል›› እንደሚባለው ያለፈን ታሪክ ላለመድገም መጠንቀቅ ይኖርበዎታል፡፡ በአዲስ መንገድ እንጂ በሄድንበት መንገድ እንዳንመለስ ከአንደበትዎ የማትጠፋውን ኢትዮጵያን ወንበሩ ላይ እንዲያስቀምጧት ሁሉም ሰው ይፈልጋል፡፡

እናም አንድን ብሄር በጩኸቱ ማነስ ወይም ደግሞ በቁጥሩ ማነስ ሳይንቁ ሁሉም እንደ አቅሙ ከወንበሩም ሆነ ከበጀቱ የድርሻውን እንዲያገኝ ማድረግ አለብዎ፡፡

ከዚህ ውጭ ግን ለአገር ሳይሆን ለስርዓቱ ቀጣይነት ሲባል ብቻ የተዋቀሩ ብልሹ ሴክተሮችን ለመለወጥ እያደረጉት ያለውን ጥረት….. ለአገራችንም ሆነ ለህዝብዎ ያለዎትን መልካም አመለካከት…… ከጎረቤት አገራት ጋር እያመጡት ያለውን የሰመረ ግንኙነት አደንቃለሁ፡፡

ይህ ሁሉ ግን እርባና እና ዘላቂነት የሚኖረው የሚያስተዳድሩት ህዝብ እስዎ በሚመሩት ስርዓት ላይ በቂ ተወካዮች እንዲኖሩት በመፍቀድ ‹የባዕድነትና የመገለል ስሜት› እንዳይሰማው ማድረግ ከተቻለ ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም ይሄ ህዝብ የኔ ከሚለው ‹‹ልማት›› ይልቅ የኔ የሚለው ‹‹ስርዓት›› በጽኑ ይፈልጋልና የስልጣን አሰጣጡን ከታማኝነትና ከአንድ ድርጅት አላቀው ሁሉንም ብሔሮች ባሳተፈ መልኩ በብቃት ላይ ቢያስቀምጡት ጥሩ ነው እላለሁኝ፡፡

ከልባዊ አድናቆት ጋር! | DireTube

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram