fbpx

‹‹ከ20 ዓመት በፊት እንደነበረው እንዋደድ?!›› ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ

‹‹ከ20 ዓመት በፊት እንደነበረው እንዋደድ?!›› ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ
(በኃይሉ ሚዴቅሳ ፍስሃጽዮን)

ለውጥ የዲያሌቲካል ሕግ ነው፡፡የማይለወጥ ለውጥ ብቻ ነው፡፡ ይህ ቋሚ እውነት ነው፡፡ የዚህ ለውጥ ፍጥነት በምሥራቅ አፍሪካ ሰማይ ሥር አዲስ የተስፋ ነፋስ አሳይቷል፡፡ በደም አፋሳሽ ውጊያ የተጠናቀቀው የኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት ለአካባባው ሰላም አብይ ሚና አለው፡፡ ይህ እንዲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣት ነበረባቸው፡፡ መጡ፡፡

ኢሕአዴግም፣ ሻዕቢያም አሰላለፋቸውን ቀየሩ፤ ኢትዮጵያና ኤርትራ በሌላ ትርክት ፍቅር ከአንደበታቸው ተሰማ፡፡ ፍቅር እንደገና!

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደጋግመው እንደተናገሩት ለፍቅር ሲባል የትኛውም መሥዋዕትነት ቢከፈል ክፋት የለውም፡፡ ይህንን መቃወም ጤነኝነት አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ፍቅሩ ከአንገት ሳይሆን ከአንጀት፣ ከጥርስ ሳይሆን ከልብ ሊመነጭ ይገባል፡፡ የፍቅር ፍላጎቱም ሆነ ጥያቄው ከአንድ ወገን ከሆነ ግን እንደ ጀማሪ አፍቃሪ ራስን እስከማጥፋት ሊያደርስ ይችላል- ፈረንጆቹ ሱሳይድ እንደሚሉት፡፡
ከኤርትራ ጋር እርቅ መፍጠር ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ እንዳለው አንድ ሺህ ምክንያቶችን መዘርዘር ይቻላል፡፡ ሁለቱም ሕዝብ ስለሚያገኘው ጠቀሜታ አንድ ሚሊዮን አስረጂዎችን ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ ይህንን ጠቀሜታ ግን በሕግና በመርህ መምራት ግድ ይላል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ረገድ በሚገባ ሊታገዙ ይገባል፡፡

ንግግሬን በግልጽ አማርኛ ላስቀምጠው፡፡ የኢሳያስ አፈወርቂን ባሕርይ እስካሁን ማንም አልደረሰበትም፡፡ አልበሽርም አልደረሱበት፤ ሙሴቬኒም አላገኙት፤ ለኡመር ጊሌህም ሩቅ ነው፤ ለአረቦቹም፣ ለኢራኖቹም ሩቅ ነው፤ አቶ መለስ ዜናዊም የኢሳያስን ፍላጎትና ባሕርይ መተንበይና ማወቅ እንዳቃታቸው በጦርነቱ ወቅት ያሳዩት አቋም ያስረዳል፡፡

በእርሳቸው ላይ ብዙ ጥናት ያደረጉ እነ ዳን ኮኔልና አሌክስ ዲ ዋል እንኳ የአቶ ኢሳያስን ባሕርይ ማወቅና መተንበይ ተስኗቸዋል፡፡ በመቸገራቸው ምክንያትም Militaristic President ጦረኛው ፕሬዚዳንት በማለት ብቻ ያልፏቸዋል፡፡ አቶ ኢሳያስ ይህንን ባሕርያቸውን ስለመተዋቸው እርግጠኛ መሆን ባይቻልም፣ የማይለወጥ ለውጥ ብቻ ነው እንዳልነው እርሳቸውም ተለውጠው ሊሆን ይችላል፡፡ ቢያንስ ዕድሜያቸው ይለውጣቸዋል ተብሎ ተስፋ ይደረጋል፡፡

በኢትዮጵያ በኩል ግን ይህንን ነገር ማሰብ ያስፈልጋል-ሰውዬው ያልተለወጡ እና በሚታወቁበት ተለዋዋጭ ባሕርይ ቢቀጥሉና አንድ ቀን ሞቅ ሲላቸው ሱዳንንም የመንንም ጅቡቱንም እንዳደረጉት ቢያደርጉንስ ብሎ ማሰብ!! አቶ ኢሳያሳ ከነባር ባሕርያቸው አንፃር ከታዩ ይህንን አያደርጉም ተብሎ አይገመትም፡፡

ስለዚህ ጥንቃቄው ከዚህ መነሳት አለበት፡፡ ከኢትዮጵያ መሪዎች ሁሉ የኤርትራ ባለውለታ አቶ መለስ ዜናዊ ናቸው፡፡ ሁለቱንም ወደቦቻቸውን ይዘው እንዲገነጠሉ፣ ከተገነጠሉ በኋላ በኢትዮጵያ እገዛ እንዲቆሙ፣ በኢትዮጵያ ብር እንዲጠቀሙ፣ ዜጎቻቸው በኢትዮጵያ እንዲነግዱ ወዘተ የፈቀዱት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ናቸው፡፡

ለኤርትራዊያንና ለራሳቸው ለአቶ ኢሳያስ መንግሥት ይህንን ያህል ፈቃድ የሰጡትን አቶ መለስንና አገራቸውን ግን አቶ ኢሳያስ ከመውረር አላመነቱም፡፡ ያን ያህል ውለታ የዋለላቸውን መንግሥትና መሪ በጦርነት ለመማረክ ጦር የሰበቁት አቶ ኢሳያስ ከአሁኑ የዶ/ር ዓብይ መንግሥት ጋር ዘላቂ ፍቅር ይኖራቸዋል ወይ ከሆነስ እንዴት የሚለውን ማጤን ያስፈልጋል፡፡

ቅድመ ደም መፋሰስ፣እንዴት ያለ ፍቅር?

የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከጥቂት ወራት በፊት በራሳቸው ቴሌቭዥን ጣቢያ ረዥም ቃለ ምልልስ ሰጥተው ነበር፡፡ በዚያ ቆይታቸው ኢትዮጵያና ኤርትራን በተመለከተ በርካታ ጉዳዮችን አብራርተዋል፡፡ ‹‹ያለፉት ዓመታት ለሁለቱም ሀገራት አክሳሪ ነበሩ፤ ይህ መሻሻል አለበት፡፡ ይህም ከ1990 ዓ.ም. በፊት ወደነበረው ሁኔታ መቀየር ይገበዋል›› የሚለው ጉዳይ ፕሬዚዳንቱ ካነሷቸው ኃሳቦች አንዱ ነበር፡፡

በርግጥ ግንኙነቱ አክሳሪ እንደነበር ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትርም ጉዳዩ ከሁለቱም ሕዝቦች ባሻገር የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናን እየረበሸው መሆኑን ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ በዚህ ትንተና የአቶ ኢሳያስ ክርክር ጥያቄ የሚነሳበት ‹‹ከ1990 ዓ.ም. በፊት ወደነበረው ግንኙነታችን መመለስ አለብን›› የሚለው ነው፡፡ ይህ ገለፃቸው የኤርትራን እብሪተኛ ፍላጎት የማስቀጠል እቅድ አሁንም እንዳልተቀየረና እንዳልቆመ የሚያሳይ ነው የሚሉ አሉ፡፡ ብዙዎች እንደሚስማሙት ከጦርቱ በፊት (ቅድመ-1990) የነበረው የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት ኢፍትሀዊና ለኤርትራ ያደለ፣ ኤርትራዊያንን ጠቅሞ ኢትዮጵያዊያንን የጎዳ ነበር፡፡

ይህ ደግሞ ገና ኤርትራ ሕዝበ-ውሳኔ አድርጋ ከኢትዮጵያ ከመገንጠሏ በፊት የታቀደ እንደነበር ብዙ ተጽፏል፤ ተነግሯል፡፡ ይህ አስቀድሞ የታቀደ እቅድ ሕጋዊነት ስላልነበረውና ውልየለሽ መሆኑ ሀገራቱ ወደ ደም አፋሳሽ ጦርነት እንዲገቡ አድርጓቸዋል፡፡ እንዴት የሚለውን ጉዳይ እንመልከተው፡፡

ኢሳያስ ምን ማለታቸው ነው?

ሻዕቢያዎች 30 ዓመታትን የፈጀውን ጦርነታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የሀገረመንግሥት መዋቅርም ሆነ መሠረታዊ የኢኮኖሚ መዋቅር ያለበት አገር አልተረከቡም፡፡ ነፃ ሐገር ሲመሰርቱ በተሰናበተው ሥርዓት ውስጥ የነበሩ ቢሮክራሲ አባላትን መጠቀም የሚያስችል ሁኔታ አልነበረም፡፡

የደኅንነትም ሆነ የኢኮኖሚ (ለምሳሌ ብሔራዊ ባንክ) ተቋማት አልነበሯቸውም፡፡ እናም አንዳንዱን በጫካ ዓመልና መንፈስ ለመምራት ሞከሩ፡፡ በዚህም በኢኮኖሚ የበለፀገችና ራስዋን የቻለች ለማድረግ ብዙ ፕሮፓጋንዳዎችን ሰሩ፡፡

አገራቸው በተፈጥሮ ሃብት የበለጸገች፣ ሕዝቧም ከጎረቤቶቹ ሁሉ የነቃና የሰለጠነ እንደሆነ በዚህም ኤርትራን አፍሪካዊቷ ሲንጋፖር እንደሚያደርጓት ቃል ገቡ፡፡ ይህንን ቃላቸውን ለመፈፀምም ያደረጉት ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ ከጎረቤቶቻቸው ጋር ግጭት ውስጥ ከተታቸው ይላል ታዋቂው የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ተመራማሪ Alex De Wall :Political marketplace in the horn of Africa በሚለው መጽሐፉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷ ናት፡፡

ገብሩ አስራት (ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ) እንደፃፈው፣ የኤርትራ ባለሥልጣናት ኢትዮጵያን ተጠቅሞ ሀብታም መሆን እንደሚገባ በይፋ ያቀዱት ገና አገራቸውን ከመሠረቱ ከሁለት ወራት በኋላ ሐምሌ 1983 ዓ.ም. በተጠራ ጉባኤ ነው፡፡

‹‹በዚህ ኮንፈረንስ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኤርትራዊያን ባለሙያዎችና የሻዕቢያ ከፍተኛ ካድሬዎች ተሳትፈው ወደ አርባ የሚጠጉ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ነበር፡፡ ጽሁፎቹ ጥልቀት ያላቸው ባይሆኑም በጥቂት ወራት ውስጥ መቅረባቸው ግን ጉዳዩ ቀደም ብሎ የታሰበበት እንደነበር ፍንጭ ይሰጣል›› ይላል፤ በዚያ ዘመን የትግራይ ክልል ርዕሰ-መስተዳድርና የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ አባል የነበረው አቶ ገብሩ አስራት፡፡

ከአራት መቶ በላይ ገፆች ባሉት መፅሐፉ እንደሚለው በኮንፈረንሱ ላይ የቀረቡት ጥናቶች የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ተቋማት ተጠቅሞ እንዴት መጠቀም እንደሚገባ የሚተነትኑ እንደነበሩ ያስታውሳል፡፡ማሳያዎችንም ይጠቅሳል፡፡

በመድረኩ ላይ ኤርትራ የራሷ አየር መንግድ በአጭር ጊዜ ማቋቋም እንደሚያቅታት የሚያሳይ ፅሁፍ የቀረበ ሲሆን፣ በአስተዳደርና በቴክኒክ ብቃት ስመጥር ከሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአክሲዮን ሽርክና መፍጠር እንደሚገባ ይመክራል፡፡

በኤርትራ ውስጥ ባንክ ማቋቋም እንደሚገባ የሚመክር ሐሳብ በጉባኤው ላይ ቢቀርብም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኤርትራ ለምታልመው ስልጣኔ የማይሆንና ኋላቀር በመሆኑ እንደ አየር መንገድ ለሽርክና አይሆንም ተብሎ መታለፉንም አቶ ገብሩ ይገልፃል፡፡

የመንገድ ልማትን በተመለከተም ‹‹በትግራይ/በኢትዮጵያ የሚሰራን የመንገድ ዕቅድ አምጥተን ኤርትራ ላይ እንሰራዋለን›› ተብሎም ተደምድሞ ነበር፡፡

እነዚህ እቅዶች የቀረቡበትን መድረክ መርቀው የከፈቱት እራሳቸው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ነበሩ፡፡ ይህ ሁሉ መንግሥታዊ ዕቅድ ሲታቀድ የኢትዮጵያ መንግሥት ስሜት አልተጠየቀም፡፡ በኋላም እቅዱን ገቢራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴዎች ተጀመሩ፡፡

አንድ የቡና ዛፍ የሌላት ሀገረ- ኤርትራ ከአፍሪካ አንደኛ ቡና ላኪ ሆና ቀረበች፡፡ ይህ የሆነው ከኢትዮጵያ በሕገወጥ ንግድ በብር ተገዝቶ ወደ ኤርትራ የሚገባ ቡና ነው-ወደ አውሮጳና ኤስያ ተልኮ የኢሳያስን መንግሥት አንደኛ ቡና ኤክስፖርተር ያደረገው፡፡
ሰሊጥንም በተመሳሳይ ተግባር ወደ ውጭ ሀገር መላካቸውን ቀጠሉ-ኤርትራዎች፡፡ ይህንን ሁሉ የሚያደርጉት በመንግሥት ውስጥ ሳይቀር የደኅንነትና የጉቦ መዋቅር ዘርግተው፣ በአፋር አሳይታና በትግራይ መቀሌ በከፈቷቸው ቆንስላዎችና በአዲስ አበባው ኤምባሲያቸው ትብብር ነው፡፡ በዚህም በኢትዮጵያ ውስጥ ሻዕቢያን ይቃወማሉ የተባሉ ፖለቲከኞች ታፍነው ተወሰዱ/ተገደሉ፡፡

ኤርትራዊያን ወደ ኢትዮጵያ ያለ ቀረጥና ታሪፍ ምርት ያስገባሉ፤ በጉልት ንግድ ላይ ሳይቀር ይሳተፋሉ፤ ሰለሞን ዕንቐይ (ዶ/ር) ‹‹የሻዕቢያ ክህደት›› በሚለው መጽሐፉ እንዳተተው፣ 60 በመቶ የኤርትራ ኤክስፖርት ሸቀጥ ማራገፊያ ኢትዮጵያ ሆነች፡፡
ኢትዮጵያዊያን በአንፃሩ ከኤርትራ በግፍ ተባረሩ፡፡ ሐብት ንብረታቸውን ትተው እንዲወጡ ተደረጉ፡፡ በድንበር አካባቢ ያሉ ዜጎችም ሐብታቸውና ከብቶቻቸው በሻዕቢያ ሰርጎ ገቦች ይዘረፉ ጀመር፡፡

አቶ ኢሳያስ ‹‹ከ1990 ዓ.ም. በፊት ያለው ግንኙነት ይመለስ ዘንድ እንሻለን›› ያሉት እንግዲህ ይህንን ግንኙነት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ኢ-ፍትሐዊና ለኢሳያስ ሀገር ያደላ ነው፡፡ እናም በቀጣይ ያለው ግንኙነት ይህንን ኢ-ፍትሐዊነት ያስቀረና ለጋራ ጥቅም የቆመ ካልሆነ ከድጥ ወደ ማጥ የሚያስገባ ሊሆን ይችላል፡፡ አቶ ኢሳያስ ዶ/ር ዓብይ ይህንን ጉዳይ አፍረጥርጠው ስለመወያየታቸው የተነገረ ነገር የለም፡፡

እና ምን ይሁን

አሁን የ20 ዓመት ግድግዳ ቢያንስ ገርበብ ብሏል፡፡ ያ አክሳሪ ግንኙነት ሊጠናቀቅም መሠረቱ ተጥሏል፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያና የኤርትራ ጉዳይ እጅጉን ጥንቃቄ የሚፈልግ ፕሮጀክት ነው፡፡ የአቶ ኢሳያስ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት የድንበር ጉዳይ አድርጎ መተንተን ይፈልጋል፤ እያደረገ ያለውም ይህንን ነው፡፡ ባሳላፍነው ሳምንት እንኳ ‹‹ወደ ኢትዮጵያ የምንልከው ልዑክ በድንበር ጉዳይ የሚወያይ ነው›› ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ በኩል ያለው እይታ ግን ከዚህም ከፍ ብሎ ቀርቧል፡፡ ጠቅላይሚኒስትሩ በሰመራ ቆይታቸው ‹‹ሁለታችንም ጦራችንን ከድንበር እናስወጣ›› የሚል ሐሣብ እንዳለ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከኤርትራ መንግሥት ባሕርይ አንፃር ይህ አዋጭ መሆኑ በሚገባ ሊታይ ይገባዋል፡፡ከላይ እንደተገለፀው በ1990 ዓ.ም. ኤርትራ ኢትዮጵያን የወረረችው አዲስ አበባ የላከችው ተደራዳሪ ቡድን ወደ ሀገሩ በቅጡ ሳይመለስ ነው፡፡ በኢትዮጵያ በኩል በወቅቱ ድንበር ላይ በቂና አስተማማኝ ሠራዊት አለመኖሩን አረጋግጠው ነው-ውጊያ የከፈቱት፡፡ ይህንን ድርጊት ደግሞ የመንም ላይ ጅቡቲም ላይ አድርገውታል፡፡ እናም ጦር የማስወጣት ነገር ከሻዕቢያ የተንኮል ሥምሪት አንፃር በጥንቃቄ መጤን አለበት፡፡

ሌላኛው ወሳኝ ጉዳይ የአዳራዳሪና ተደራዳሪ ነገር ነው፡፡ ይህ ድርጊት ከከፍተኛ ደም መፋሰስ በኋላ የሚመጣ ነው፡፡ እናም ይህንን ደም መቃባት፣ በይቅርታ ለመተካት አደራዳሪዎች ሚናቸውና ገለልተኛነታቸው በጥንቃቄ ሊቃኝ ይገባዋል፡፡ የተደራዳሪዎችም ማንነት ይህንን ሂደት ይወስነዋል፡፡

ኤርትራ ነባር ተደራዳሪዋንና ጉዳዩን የሚያውቁትን አቶ የማነን ከነ ኡስማን ጋር ስትመድብ አሮጌውንም ሆነ አዲሱን አቁማዳ አጣጥማ ለመጠቀም ያላትን ፍላጎት ያሳያል፡፡ በዚህም በኩል ያሉት ሰዎች የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያውቁ፣የችግሩን ምንጭ የሚረዱ፣የሁለቱ ሀገራት የፖለቲካ አሰላለፍ የሚገባቸው፣ ከኤርትራ በኩል ያሉትን ተደራዳሪዎች ሰብዕና የሚያውቁ፣የሻዕቢያን ነባርና አዳዲስ ባሕርያትና ፍላጎቶች የሚገነዘቡ መሆን ይገባቸዋል፡፡ይህ ከሆነ ኢትዮጵያ ለሌላ ሽንፈት ሳትዳረግ፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ መብቷን አስከብራ ይህንን ድርድር ታጠናቅቃለች፡፡ DireTube

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram