fbpx

ከአዲሱ ከንቲባዬ የምፈልገው?!

ከአዲሱ ከንቲባዬ የምፈልገው?! | ጫሊ በላይነህ በድሬቲዩብ

እነሆ አዲስአበባ አዲስ ከንቲባ አግኝታለች፡፡ ያው ሕጋዊ ሒደቱን ለመጠበቅ ሲባል አዲሱ ከንቲባ የተሾሙት “ምክትል ከንቲባ” ተብለው ነው፡፡

ለምን ቢባል በከተማዋ መተዳደሪያ ቻርተር መሠረት ከንቲባው መመረጥ ያለበት ከከተማው ምክርቤት አባላት መካከል በመሆኑ ነው፡፡

አዲሱ ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ይህንን ስለማያሟሉ፣ በምክትል ከንቲባነት ወንበር ሊቀመጡ ግድ ሆኗል፡፡ ያው በከንቲባ ማዕረግ ምክትል ከንቲባ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡

ለነገሩ ይህንንም የምክትል ከንቲባነቱን ሥልጣን ያገኙት ባለፈው ወር ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የቀረበው የአስተዳደሩ ቻርተር ምክትል ከንቲባው ከምክርቤት አባላት መካከል ይመረጣል የሚለውን አዋጅ ማሻሻል በመቻሉ ነው፡፡

የተሻሻለው አዋጅ ምክትል ከንቲባው የምክርቤት አባል ባይሆንም መመረጥ እንዲችል ይፈቅዳል፡፡ ይህ ሕግ በሩጫ የተሻሻለው ቀድሞውኑ ኢንጅነር ታከለ ኡማን ወደፊት ለማምጣት ታሳቢ ተደርጎ ይሁን፣ አይሁን ዝርዝሩን የሚያውቀው አስፈጻሚው አካል ብቻ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ኢንጅነር ታከለ በተጨባጭ ከተማዋን የመለወጥ ብቃት እስካላቸው ድረስ ለእሳቸው ተብሎ ሕጉ ተሻሻሎ ቢሆንም ለመልካም ዓላማ የታሰበ በመሆኑ በግሌ ቅር የምሰኝበት አይሆንም፡፡ ግን ግለሰብን ወይንም የራስን ብሄር ቦታ የማስያዝ ጉዳይ ከሆነ፤ ነገሩ ሁሉ ዳቦ ተቆረሰ፣ ጨዋታ ፈረሰ ይሆናል፡፡

ወደመጣጥፌ ትኩረት ልመለስ፡፡ ተሰናባቹ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ ወንበራቸው ላይ ላለፉት አምስት ዓመታት መቀመጣቸውን ከትላንቱ ርክክብ በኋላ በፌስ ቡክ ገጻቸው የጻፉት ማስታወሻ ይጠቁማል፡፡

በእነዚህ ዓመታት አስመዘገብን ያሉት ውጤት ለጊዜው አቆይተነው በሙስና እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች አሁንም እንዳልተፈቱ በግልጽ ያመኑበትን ሁኔታ እንፈትሸው፡፡ ለአዲሱ ከንቲባም የሰጡት የቤት ሥራ ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው፡፡

የሚገርመው በእሳቸው የስራ ዘመን በከፍተኛ የአስተዳደሩ የሥልጣን እርከን ጭምር ይታገዛል ተብሎ በብዙዎች ዘንድ የሚጠረጠር እስከታች መዋቅር ድረስ የሕገወጥ ጥቅም ኔትወርክ ሲዘረጋ አቶ ድሪባ ኩማ ተኝተዋል፡፡

አንዳንዶች ከእንቅልፋቸው ቀስቅሰው ጭምር የነገሩዋቸውን ስሞታ፣ ቅሬታ፣ አቤቱታ፣ ሰምተው ችግሩን ለመፍታት አለመሞከራቸው
ለብዙዎች እንቆቅልሽ ሆኖ የሰነበተ ሐቅ ነው፡፡

እነሆ ዛሬ እንደደራሽ ውሃ ድንገት ተነስተው ስለሙስናና መልካም አስተዳደር ችግር አሁንም መፈታት አለመቻሉን አፋቸውን ሞልተው ሲነግሩን “እኔ በዚህ ረገድ ምን ሰራሁ” ብለው ራሳቸውን የጠየቁም አይመስልም፡፡

ወይንም ጉዳዩ እሳቸውን እንደማይመለከት ራሳቸውን ሳያሳምኑ አልቀሩም፡፡ እናም ስለችግሩ ሲጠቅሱ ሲመሩት ስለቆዩት ከተማ ሳይሆን ስለሌላ አገር ወይንም ከተማ የሚያወሩ አስመስሏቸዋል፡፡

እናም አዲሱ ከንቲባችን የመጀመሪያ ሥራቸው መሆን የሚገባው በከተማዋ እስከወረዳ ጭምር የተዘረጋ ሕገወጥ የሙስናና የብልሹ አሠራር ኔትወርክ በአስተማማኝ ሁኔታ መበጣጠስ መሆን ይኖርበታል፡፡

የአስተዳደሩ ቢሮዎች በሰለጠኑ ባለሙያዎች እንዲመሩ ማድረግ አለባቸው፡፡ ወረዳዎች፣ ክፍለከተማዎች ሕዝብን የማገልገያ ተቋማት እንዲሆኑ ሰፊ ለውጥ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ እንደአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ያሉ የሙስናና ብልሹ አሠራር መቀፍቀፊያ ቢሮዎች፣ እንደአዲስአበባ መገናኛ ብዙሃን ያሉ በደካማ አመራሮች የደከሙ ተቋማት ተቆጥረው በሕግ የሚጠየቀውን መጠየቅ፣
አቅም የለሹን መሸኘት ይገባል፡፡

አዲሱ ከንቲባ ሌላውና ትልቁን አዳጣፊ እርምጃ ሊወስዱበት ከሚገቡ ጉዳዮች ቀዳሚዎቹ የአዲስአበባ የትራንስፖርት ችግር እና የመኖሪያ ቤቶች ችግር እጠቅሳለሁ፡፡ ባለፉት 20 ዓመታት የአዲስአበባን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ እርምጃዎች መወሰዳቸው እውነት ቢሆንም ችግሩ ግን የሕዝቡን የትራንስፖርት ፍላጎቱን በሚመጥን መልኩ መቅረፍ ያስቻለ አልነበረም፡፡

በዚህም ምክንያት ዛሬም በርካታ ሠራተኞች ወደስራቸው ቦታ ለመሄድና ወደቤታቸው ለመመለስ ረጃጅም ሰልፎችን ለረጅም ሰዓታት ቆሞ ማሳለፍ ግዴታ ሆኖባቸዋል፡፡ ነዋሪዎች በፈለጉት ሰዓት ወደፈለጉት አካባቢ ለመጓጓዝ አዳጋች ሆኖባቸዋል፡፡

በተጨባጭ ለመናገር ከፒያሳ እስከ ሳሪስ አቦ ደርሶ ለመመለስ ብቻ ከሶስትና አራት ሰዓታት ወይንም ግማሽ ቀን በላይ በትራንስፖርት ጥበቃ እንግልት ማሳለፍ የተለመደ መደበኛ ተግባር ሆኗል፡፡ በእንዲህ መልኩ ተሰላችቶና ደክሞ ወደስራ የሚገባ ሠራተኛ በምርታማነት፣ በአገልጋይነት መንፈሱ ላይ የቱን ያህል ከባድ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚደርስ መገመት ይቻላል፡፡

ባለፉት ዓመታት የመኖሪያ ቤቶችን ችግር ለመቅረፍ በ20/80፣ በ10/90 እና በ40/60 ፕሮግራሞች ብዙ ተሠርቷል፣ ብዙ ተደክሟል፡፡

ይህም ሆኖ የቤት ልማት ፕሮግራሙ ከተጀመረ ከ13 ዓመታት በሃላም በመጀመሪያው ዙር የተመዘገቡ ከ350 ሺ ገደማ ዜጎችን ሙሉ በሙሉ የቤት ባለቤት ማድረግ አልተቻለም፡፡

እስካሁን ባለው መረጃ መሠረት የቤት ባለቤት መሆን የቻሉት ወደ 175 ሺ የሚደርሱ ዜጎች ብቻ ናቸው፡፡ እነዚህ ዜጎች የራሳቸው መኖሪያ አግኝተው ችግራቸውን እንዲቀረፍ መንግስት ያደረገው አስተዋጽኦ የማከብረው ሆኖ ግን የመኖሪያ ቤትን ያህል ሰፊ ማህበራዊ ችግር በመንግስት አቅም ብቻ እፈታለሁ ብሎ መነሳት ከዕቅዱ ጀምሮ ችግር የነበረበት መሆኑን ውጤቱ
ይናገራል፡፡

እናም በአጭሩ በድጋሚ ምዝገባ የተካተቱትን ጨምሮ ከ900 ሺ በላይ ሕዝብ ዛሬም በተሟጠጠ ቀቢጸ ተስፋ የኮንደሚኒየም ዕጣ እየጠበቁ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ነው፤ መንግሥት ባለፉት ዓመታት ዜጎችን የኮንደምኒየም ዕጣ ጠባቂ በማድረጉ ካገኘው ትርፍ ይልቅ ኪሳራው ይበልጣል የሚባለው፡፡

ከመንግስት በተደጋጋሚ በተነገራቸውና በገቡት ኮንትራት መሠረት ሳይተርፋቸው ተቸግረው እየቆጠቡ የሚገኙ በሺ የሚቆጠሩ ዜጎች በመንግሥት ላይ ያላቸው አመኔታ ተሟጦና ተንጠፍጥፎ ከማለቁ በፊት አዲሱ ከንቲባ መላ ሊዘይዱ ይገባል፡፡ ሌሎች የመኖሪያ
ቤቶችን መቅረፊያ አማራጮች በሙሉ ሥራ ላይ ለማዋል ፈጥነው መንቀሳቀስ ይገባቸዋል፡፡

የሙስና እና መልካም አስተዳዳር ችግሮች ስብሰባ ማድመቂያና ንግግር ማሳመሪያ ብቻ አድርጎ መቀጠል ከጊዜው አስተሳሰብ ጋር አብሮ የማይሄድ ነው፡፡

ከሕዝብ የለውጥ መንፈስ ጋር አብሮ የሚሄድና ተመጋጋቢ የሆነ የለውጥ ሥርዓት በተጨባጭ መሬት አውርዶ ማሳየት ከአዲሱ ከንቲባ ይጠበቃል፡፡

በሥራዎቻቸው ሁሉ ግልጽነትና የአሳታፊነት መንገዶች መተግበር ከቻሉ ልክ እንደዶ/ር አብይ አሕመድ ሁሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ የከተማዋን ሕዝብ ከጎናቸው ማሰለፍ ይችላሉ፡፡ ለአዲሱ ከንቲባችን መልካም የሥራ ጊዜ በመመኘት እሰናበታለሁ፡፡ DireTube

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram