በመላ አገሪቱ ተግባራዊ የሚሆነውና ለስድስት ወራት የሚቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ አንድ ወር ሊሞላው በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ብቻ ናቸው የቀሩት፡፡ አዋጁ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም. እንደታወጀና የካቲት 23 ቀን 2010 ዓ.ም. ደግሞ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደፀደቀ ይታወሳል፡፡ አዋጁ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይፀድቃል? ወይስ አይፀድቅም? የሚለው የወቅቱ ዋነኛ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ነገር ግን በኢሕአዴግ የሥልጣን ዘመን ብዙም ባልተለመደ መንገድ ጥቂት የማይባሉ የምክር ቤት አባላት ከተቃወሙትና ድምፃቸውን ከነፈጉት በኋላ ፀድቋል፡፡ አዋጁ ላይፀድቅ ይችላል የሚለው ዋነኛ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ ቢቆይም፣ በምክር ቤቱ አባላት አብላጫ ድምፅ ለመፅደቅ ችሏል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መፅደቅን ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል በተጠራው አድማ የዜጎች ሕይወት አልፏል፡፡ በትንሹ ከአሥር ያላነሱ ንፁኃን ዜጎች ላይ የሞት፣ በፀጥታ አካላት ላይ የአካል ጉዳት፣ የመሣሪያ ነጠቃ፣ በቀላልና በከባድ ተሽከርካሪዎች ላይ መሰባበርና ፋብሪካዎች ሥራቸውን እንዲያቆሙ የማድረግ እንቅስቃሴዎች መከሰታቸውን በኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያት ተገልጾ ነበር፡፡
አዋጁ ሲታወጅ በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ያመጣል ተብሎ ቢጠበቅም ፀድቆ በሥራ ላይ ከዋለ በሁለትና በሦስት ቀናት ልዩነት ውስጥ የዜጎች ሕይወት አልፏል፡፡ ይህ የአድማ እንቅስቃሴ የቀለም አብዮት መልክ እንደነበረው የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያት ኃላፊና የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ባለፈው ሳምንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ጠቁመዋል፡፡ በአገሪቱ አንፃራዊ የሆነ ሰላምና መረጋጋት መታየቱንም አክለው ገልጸው ነበር፡፡
አቶ ሲራጅ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኋላ በአገሪቱ በአንፃራዊነት ሰላምና መረጋጋት እንደተፈጠረ ቢገልጹም፣ ቅዳሜ መጋቢት 1 ቀን 2010 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ሞያሌ ከተማን በተመከለከተ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ሴክሬታሪያት ባወጣው መግለጫ፣ የዘጠኝ ሰዎች ሕይወት እንዳለፈና በአሥራ ሁለት ሰዎች ላይ ደግሞ የመቁሰል አደጋ እንደ ደረሰ አስታውቋል፡፡ ይህን ድርጊት ፈጽመዋል ተብለው በተጠረጠሩ አምስት የሠራዊቱ አባላትም ትጥቃቸውን እንዲፈቱና በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ መደረጉን፣ የኮማንድ ፖስቱ ጽሕፈት ቤት ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል፡፡
‹‹በአገሪቱ የተፈጠረውን ሁከትና ግርግር እንደ ምቹ አጋጣሚ በመቁጠር ሁኔታውን ለማባባስና ለራሳቸው የጥፋት ሴራ ለማዋል በሞያሌ አካባቢ የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግረው የገቡ የኦነግ ታጣቂዎችን ለመቆጣጠርና ለመደምሰስ አንድ የሻለቃ ጦር በሥፍራው ላይ በግዳጅ ተሠማርቶ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ የሠራዊቱ አባላት የተሳሳተ መረጃ ይዘው ባደረጉት እንቅስቃሴ በአካባቢው ኅብረተሰብ ላይ ጉዳት ደርሷል፤›› ሲል የኮማንድ ፖስቱ መግለጫ አስታውቋል፡፡
በማግሥቱ እሑድ መጋቢት 2 ቀን 2010 ዓ.ም. የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አዛዦችን ያካተተ አጣሪ ቡድን ወደ ሞያሌ እንደተላከ፣ የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያት ተወካይ ሌተና ጄኔራል ሐሰን ኢብራሂም ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡ ቡድኑ የተጎጂ ቤተሰቦችንና ኅብረተሰቡን በማነጋገር የማፅናናት ሥራ እንደሚከናወን አክለው ጠቁመዋል፡፡
‹‹በአገሪቱ የተፈጠረውን ሁኔታ ለማባባስ ያለመ የኦነግ ኃይል በሦስት አቅጣጫ ወደ አገሪቷ ሰርጎ ለመግባት ያደረገውን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ወደ ሞያሌ የተጓዘው አንድ የሻለቃ ጦር የተሳሳተ መረጃ በመያዝ በተፈጠረ ግጭት፣ የግዳጅ አፈጻጸም ደንቡን ባልተከተለ አኳኃን ዕርምጃ በመወሰዱ የሰው ሕይወት ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ በዚህ ተግባር ላይ በተሳተፉ የመከላከያ ሠራዊቱ አባላት ትጥቅ የማስፈታትና በቁጥጥር ሥር የማዋል ዕርምጃ ተወስዷል፡፡ የማጣራቱና የምርመራ ሥራው እንደተጠናቀቀም ወደ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ተወስደው ፍርድ ያገኛሉ፤›› ብለዋል፡፡
በዚህም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የሟቾች ቁጥር ወደ ሃያ ከፍ እንዳለ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
የኮማንድ ፖስቱ ተወካይ ዘጠኙ ዜጎች የተገደሉት በስህተት እንደሆነና የተወሰኑ የሠራዊቱ አባላት በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ ቢገልጹም፣ ይህ በራሱ በቂ አይደለም ሲሉ የሚከራከሩ ወገኖች እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡
አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ዕርምጃው ስህትት ነው ተብሎ ብቻ የሚታለፍ ጉዳይ አይደለም፡፡ ‹‹ይህ የሻለቃውን አመራሮች ብቻ ሳይሆን የመከላከያ ሚኒስቴር ኃላፊዎችን ጨምሮ ከሥልጣን የሚያስነሳ ጉዳይ ነው፤›› ሲሉ አክለው ገልጸዋል፡፡ መምህሩ አገርን በወታደራዊ ኃይል ወደ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ማምጣት እንደማይቻል ጠቁመው፣ መንግሥት አሁንም የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ከማክርና ከማስከበር አኳያ ጥንቃቄ የተሞላበት ሥራ ማከናወን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
በሞያሌ በደረሰው ችግር ሳቢያም በርካታ ዜጎች ወደ ኬንያ መሰደዳቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሪፖርተር ከአካባቢው ነዋሪዎች ለማረጋገጥ እንደቻለው የተፈጠረውን ችግር በመፍራት በርካቶች ሸሽተዋል፡፡ ችግሩ በምን ምክንያት እንደደረሰ የሚያውቁት ነገር እንደሌለም ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹በከተማዋ ከዚህ በፊት ከነበረው የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የተለየ ነገር አልነበረም፡፡ ነገር ግን ሳይጠበቅ የመከላከያ ኃይል ዜጎችን ገድሏል፤›› ሲሉ አክለው ገልጸዋል፡፡
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣን በበኩላቸው በንፁኃን ዜጎች ላይ የተወሰደው ኢሰብዓዊ ድርጊት በማንኛውም መሥፈርት ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡ ‹‹በአንድ አገር ንፁኃን ዜጎች ላይ በአሰቃቂ ሁኔታ የመግደል ዕርምጃ ተወስዷል፡፡ ችግሩ ስህተት ነው ተብሎ የሚታለፍ አይደለም፡፡ የክልሉ መንግሥት አጥፊዎች ለሕግ እንዲቀርቡና ለክልሉ መንግሥት ተላልፈው እንዲሰጡ ይሠራል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ ሃያ ስድስት ቀናት ቢሆኑም፣ እስካሁን በአገሪቱ አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት ማረጋገጥ አልተቻለም ሲሉ የሚከራከሩ አሉ፡፡ 2010 ዓ.ም. ከገባ ማግሥት ጀምሮ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠረ ግጭት ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ዜጎች ለሕልፈተ ሕይወት ከመዳረጋቸው ባሻገር፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ከቀዬአቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ካምፕ ውስጥ ለመኖር ተገድደዋል፡፡ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ የማቋቋም ሥራ ባልተጀመረበት ወቅት፣ አሁንም እየተከሰተ ያለውን ቀውስ በመፍራት ከአገር የወጡ ዜጎች እንዳሉ ታውቋል፡፡
የሞያሌ ከተማ ከንቲባ ለአሜሪካ ድምፅ የአማርኛው ፕሮግራም እንደተናገሩት፣ ቁጥራቸው ሃምሳ ሺሕ የሚደርሱ ዜጎች ወደ ጎረቤት አገር ኬንያ ተሰደዋል፡፡ በአገሪቱ መረጋጋት ባለመኖሩ ምክንያት ለዜጎች ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚያሳስብ ጉዳይ እየሆነ እንደመጣ፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) እሑድ መጋቢት 2 ቀን 2010 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ ጠቁመዋል፡፡ የዜጎችን በሕይወት የመኖርና የአካል ደኅንነት መብቶች የማክበርና የማስከበር ኃላፊነት መውጣት፣ ዘላቂ ሰላምና ልማት ማረጋገጥ አማራጭ የሌለው መፍትሔ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ሚኒስትሩ በሕገ መንግሥቱ ከተካተቱ ጠቅላላ ድንጋጌዎች መካከል አንድ ሦስተኛው የሰብዓዊ መብቶችን የሚመለከቱ መሆናቸውን አስታውሰው፣ ‹‹ከተደነገጉት ሰብዓዊ መብቶች መካከልም አንዱ ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሰስ በሕይወት የመኖርና የአካል ደኅንነት መብት አለው፤›› ሲሉ ጠቁመዋል፡፡ እነዚህን መብቶች በማክበርና በማስከበር ረገድም ሕገ መንግሥቱ ከፍተኛውን ኃላፊነት የጣለው በዋነኝነት በመንግሥት ላይ እንደሆነ አክለው ገልጸዋል፡፡
በአገሪቱ የተፈጠሩትን ችግሮች ለመፍታትና የሕዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስ መንግሥት የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ቀይሶ የተለያዩ ዕርምጃዎችን እየወሰደ እንደሚገኝ፣ በዚህ ወቅት አልፎ አልፎ በዜጎች ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ሲደርስ እንደሚስተዋል ገልጸዋል፡፡ ‹‹ይህ ሁኔታ ሕዝባችን በመንግሥት ላይ ያለውን አመኔታ የሚሸረሽር ብቻ ሳይሆን፣ በሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ዙሪያ የአገራችንን ገጽታ እየጎዳው ነው፤›› ብለዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል በቦረና ዞን ሞያሌ ከተማ በዜጎች ላይ የደረሰውን የሞትና የመቁሰል አደጋ አስመልክተው ሲናገሩም፣ ‹‹በየትኛውም መሥፈርት ቢሆን ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ ጥፋቱን በፈጸሙት ላይ አስተማሪ ሊሆን የሚችል ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚወሰድ፣ በኮማንድ ፖስቱ እንደተገለጸው መንግሥት ከሕዝቡ ጋር ሆኖ እንደሚሠራ እያረጋገጥን ሕይወታቸውን ላጡና የአካል ጉዳት በደረሰባቸው ወገኖቻችን የተሰማንን ጥልቅ ሐዘን ለመግለጽ እወዳለሁ፤›› ብለዋል፡፡ በዜጎች ላይ ይህን መሰል ስህተት እንዳይደገምም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ የሚገባቸውን መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡
በተለይ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ቀውስ በመከሰቱ በርካታ ዜጎች ለሞትና ለአካል ጉዳት እንደተዳረጉ፣ እንዲሁም ከመኖሪያ ቀዬአቸው እንደተፈናቀሉ ይታወቃል፡፡ ይህ ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመምጣቱ ሳቢያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከኢሕአዴግ ሊቀመንበርነትና ከአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ለመልቀቅ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
የእሳቸውን ከኃላፊነት ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረብ ተከትሎ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ አሁንም በአገሪቱ አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት መፍጠር ጥረት ቢደረግም ችግሮች ግን እያጋጠሙ መሆናቸው ይነገራል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምን ከሥልጣን መልቀቅ ጥያቄ ተከትሎ የፓርቲውን ሊቀመንበር ለመምረጥ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከእሑድ መጋቢት 2 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በዝግ እየመከረ ነው፡፡ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ዋነኛ መወያያ በግልጽ ምን እንደሆነ ባይታወቅም፣ የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ባለፈው ሳምንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በዋናነት አገሪቱ ስላለችበት ወቅታዊ ሁኔታና በብሔራዊ ፓርቲዎች በቀረቡ አጀንዳዎች ላይ ውይይት ይደረጋል ብለው ነበር፡፡ በዝግ እየተካሄደ ያለው ስብሰባ መቼ እንደሚጠናቀቅ ባይታወቅም፣ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ስብሰባ እንደተጠናቀቀ የብሔራዊ ምክር ቤት ስብሰባ በማድረግ፣ ተተኪውን የግንባሩን ሊቀመንበር ይመርጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አራቱም የኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች ረዘም ላለ ጊዜ በማዕከላዊ ኮሚቴ ደረጃ አገሪቱ ስላለችበት ሁኔታ፣ በተለይም በተጨባጭ በየክልሎቻቸው እያጋጠሙ ስላሉ ችግሮች ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ስብሰባ ያካሄደው የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ሲሆን፣ ለ35 ቀናት ባደረገው ስብሰባ የአመራር ሽግሽግ አድርጎ ነበር፡፡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና የድርጅቱ ሊቀመንበር የነበሩትን አቶ ዓባይ ወልዱ ከሁለቱም የኃላፊነት ቦታቸው በማንሳት፣ በምትካቸው ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤልን (ዶ/ር) የፓርቲው ሊቀመንበርና የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ መምረጡ አይዘነጋም፡፡
የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባም ለአንድ ወር ያህል መካሄዱ የሚታወስ ሲሆን፣ የአመራር ሽግሽግ ሳያደርግ ስብሰባውን አጠናቋል፡፡ በዚህም አቶ ደመቀ መኮንን የድርጅቱ ሊቀመንበር ሆነው እንዲቀጥሉ ወስኗል፡፡
የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ድንገተኛ ስብሰባ በማድረግ ሊቀመንበር የነበሩትን አቶ ለማ መገርሳ አንድ ደረጃ ዝቅ በማድረግ፣ በምትካቸው ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) በአቶ ኃይለ ማርያም ምትክ አቶ ሽፈራው ሽጉጤን የድርጅቱ ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል፡፡
የአገሪቱ የፖለቲካ ቀውስ መቋጫ ባያገኝም ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትር ማን ይሆናል የሚለው ጥያቄ አሁንም መነጋገሪያ አጀንዳ እንደሆነ ነው፡፡ ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትር አገሪቱ ካለችበት ቀውስ በማውጣት የተሻለ ሰላምና መረጋጋት ይፈጥራል? ወይስ አገሪቱ በቀጣይም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር ሆና እንድትተዳደር ያደርጋል? የሚለው ጥያቄ አሁንም መልስ የሚሻው ጉዳይ ሆኖ እያነጋገረ ነው፡፡
ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል የተጠራው ቤት ውስጥ የመዋል አድማ ተጠናቆ ባለፉት ሦስትና አራት ቀናት በአገሪቱ የነበረው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የተሻለ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ነገር ግን አሁንም በኦሮሚያና በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ነዳጅ የጫኑ ቦታዎች እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ የሚገልጹ የአድማ ጥሪዎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ሲነገሩ እየተስተዋለ ነው፡፡
የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አሁንም ድረስ በዝግ እየመከረ ቢሆንም፣ አገሪቷ ወደ ቀድሞ ሰላምና መረጋጋቷ እንድትመለስ ኃላፊነት የተሰጠው ኮማንድ ፖስት በሥራ ላይ ነው፡፡ በዚህም ሁከትና ግርግር ይፈጥራሉ ተብለው የተጠረጠሩ ዜጎችን ኮማንድ ፖስቱ በቁጥጥር ሥር እያዋለ እንደሆነ ሌተና ጄኔራል ሐሰን ኢብራሂም ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በፊት በጥርጣሬ ተይዘው የነበሩ ዜጎችም እየተለዩና እየተለቀቁ መሆናቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡
በዚህም በአገሪቱ አንፃራዊ የሆነ ሰላምና መረጋጋት መፍጠር እንደተቻለ ጠቁመው፣ በቀጣይ ኮማንድ ፖስቱ የዜጎችን መብቶች በማክበር ተልዕኮውን የመወጣትና የአገሪቱን ሰላምና ደኅንነት የማረጋጥ ሥራ እንደሚያከናውን ገልጸዋል፡፡