fbpx
AMHARIC

“ከመጀመሪያውኑ ስልጣኔን ለቅቄያለሁ ብሎ መናገሩ አስፈላጊነቱ ምኑ ላይ ነው?”

ተሰናባቹ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ሊቀ-መንበር የሆኑት ኃይለማርያም ደሳለኝ የስልጣን ልቀቁኝ ጥያቄያቸውን ይፋ ካደረጉ እነሆ አንድ ወር ሞላቸው።

ለጥቆም በሃገሪቱ እየታየ ያለውን አለመረጋጋት ለመቀልበስ ነው በሚል መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደነገገ። በኢህአዴግ አባል ድርጅቶችም ውስጥ ሹም ሽር ተካነወነ። ቢሆንም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ተክቶ ሃገሪቱን የሚመራ ግለሰብ ማን እንደሚሆን እስካሁን ድረስ አልታወቀም።

ገዢው የኢህአዴግ ፓርቲ እስካሁን ድረስ ተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትር መሾም ያልቻለው ለምን ይሆን ስንል ምሁራንንና ፖለቲከኞችን ጠየቅን።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የታሪክ መምህር የሆኑትን አቶ አበባው አያሌው “እንደኔ ግምት ከሆነ ገዢው ፓርቲ ውስጥ ባሉ ድርጅቶች መሃል አለመስማማት ተፈጥሯል” ይላሉ።

“እስካሁን እኔ እንደማውቀው ከሆነ ፓርቲው ክፍተቶችን ለመሙላት ጊዜ አይፈጅበትም” የሚሉት ምሁሩ “ዘንድሮ በተከታታይ ርዝመት ያላቸው ስብሰባቸው እያከናወነ ያለው ገዢው ፓርቲ ምናልባትም ከወትሮው የተለዩ ጥያቄዎች ከህዝቡ እንዲሁም ከአባል ድርጅቶች መነሳታቸው ሳይፈትነው አልቀረም” ባይ ናቸው።

“እንደእኔ እምነት ከሆነ አንድ መሪ ስልጣኔን በፍቃዴ ለቅቄያለሁ ብሎ ካወጀ ወዲያውኑ ነው ተተኪ መመረጥ ያለበት። ይህ ካልሆነ ግን የስልጣን ክፍተት ይፈጥራል። ይህ ደግሞ በተራው የስልጣን ሽኩቻ ያመጣል። በሕዝቡም በኩልም እከሌ ነው የሚሆነው አይ እከሌ ነው የሚል ክፍፍል ከመፍጠር ውጭ ምንም ዓይነት ፋይዳ አይኖረውም። ለዚህ ነው እኔ ሁኔታዎች በፍጥነት መካሄድ አለባቸው ብዬ ነው የማምነው” ሲሉ ይተንትናሉ።

የቀድሞው የፓርላማ አባል የሆኑትን አቶ ግርማ ሰይፉን በበኩላቸው የሹመቱ መዘግየት ያለውን የስልጣን ሽኩቻ የሚያንፀባርቅ ነው ይሉናል። “በአንድ በኩል ያላቸውን ተቀባይነት ማጣት የፈለጉ አይመስለኝም። በሌላ በኩል የህዝቡ ጥያቄ አለ። በእነዚህ ጉዳዮች ሳቢያ አለመስማማት ውስጥ ያሉ ይመስለኛል።”

በዚህ ወቅት አንዳች ነገር ቢከሰት ኃላፊነቱን መውሰድ ያለበት ማነው? ለእንግዶቻችን ያቀረብነው ጥያቄ ነው። “ኃላፊነቱን መውሰድ ያለበት እራሱ ስልጣን ላይ አካል ነው። ተወዳድሬ አሸንፌያለሁ ብሎ የመንግሥት ሥራ እያስተዳደረ ያለው፤ ወታደሩን የሚያስተዳድረው ኢህአዴግ እስከሆነ ድረስ ለማንኛውነ ነገር ተጠያቂ የሚሆነው ገዢው ፓርቲ እንጂ ህዝቡ አይደለም” የሚሉት የታሪክ ምሁሩ አቶ አበባው አያሌው ናቸው።

የአቶ ግርማ ሃሳብም ከዚህ የተለየ አይደለም። “ስልጣን ያለ አንድ ድርጅት በሃገሪቱ ውስጥ ለሚፈጠር ማንኛውም ዓይነት ክንዋኔ ተጠያቂ ከመሆን አይድንም” ሲሉ ሃሳባቸው ይገልፃሉ።

“እኔ ማይገባኝ ነገር ቢኖር ከመጀመሪያውኑ ስልጣኔን ለቅቄያለሁ ብሎ መናገሩ አስፈላጊነቱ ምኑ ላይ ነው የሚለው ነው” የሚሉት አቶ ግርማ “ኢህአዴግ አቶ ኃይለማርያም ስልጣናቸውን እንደለቀቁ ሊያሳውቀን የፈለገው ምን ዓይነት መልዕክት ሊያስተላለፍ ፈልጎ እንደሆነ አልገባኝም” ሲሉ ይናገራሉ።

“ለእኔ ትክክል የሚሆነው በድርጅቱ ውስጥ ያለውን የስልጣን ሽግሽግ ከጨረሱ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን ቢያሳውቁን ወይም ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እኔ ከዛሬ ጀምሮ ስልጣኔን ለቅቄያለሁ ከዚህ በኋላ ምክትሉ ናቸው የሚያስተዳድሩት ቢሉን ነበር።”

የኢህአዴግ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ትላንት ማምሻውን እንደተናገሩት በሚቀጥለው ሳምንት አጋማሽ የድርጅቱ ምክር ቤት ተሰብስቦ የተፈጠረውን የአመራር ክፍተት ያሟላል ብለዋል።

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram