fbpx

ኦቦ ዳውድ ያዘጋጁት የዶ/ር ዓብይ ፈተና!

ኦቦ ዳውድ ያዘጋጁት የዶ/ር ዓብይ ፈተና ! | ሬሞንድ ኃይሉ

ኤርትራ መቀመጫቸውን አድረገው ከታገሉ የኢትዮጵያ መንግሰት ተቃዋሚዎች ውስጥ ለፕሬዘዳንት ኢሳይያስ ቅርብ የነበሩ ሰው ናቸው፡፡ በአሰመራ ጎዳናዎች ላይ ከሚታዩ ቅንጡ መኪኖች መካከል አንዱን የሚነዱት ኦቦ ዳወድ የወዲ አፎም ጥሩ ወዳጅም ሁነው ነበር፡፡ በዚህ የተነሳም የኢትዮጵያን ፖለቲካ በወፍ በረር ሳሆን በውሉ ይረዱታል፡፡

ኦቦ ዳውድ ጠቅላይ ሚንሰትር ዓብይ ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ለተቃዋሚዎች የስላማዊ ትግል አማራጭ ሲቀርብ ለዘብተኛ አቋም ካሳዩት መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ኦነግ ኢህአዴግን ማመን ቀብሮ ነው የሚል ብሂል የሚከትል ፓርቲ ነው፡፡ እንዲህ ያለው እሳቤው ደግሞ ህወሓት መሩ ኢህአዴግ ከስልጣን ተወገዶም በቀላሉ የሚለቅ አልነበረም፡፡ እናም በርካታ ተቃዋሚዎች ጠቅላይ ሚንሰትሩ ኑ ካለን ምን ቸገረን እያሉ ወደ አዲስ አበባ ሲተሙ የኦቦ ዳውዱ ኦነግ ግን በቀላሉ ለመምጣት አልፈለገም፡፡

አቶ ለማና ዶ/ር ወርቅነህ ኤርትራ ድረስ ሂደው ደጅ ጠንተውትም ግንባሩ አልተፈታም፡፡ እንደውም የፕሬዘዳንት ኢሳያስ ትዕዛዝ ባይጨመርበት ኑሮ ድርድሩም አይሳካም ነበር ብለው የሚናገሩ ፖለቲከኞች ብዙ ናቸው፡፡

ኦነግ በዚህ መንገድ ተደራድሮ ወደ ሀገር ውስጥ ለመግባት መዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት መገናኛ ብዙሃንም ወሬውን ትልቅ ድል አድርገው አሰተጋቡት፡፡ በዚህ ፍጥነት ግን የኦነጉ ቃላ አቀባይ ከፍራንስ ኢንተርናሽናል ራድዮ ጋር በነበራቸው ቆይታ የመጀመሪያውን ጥይት ተኮሱ፡፡ እኛ ሀገር ውስጥ የምነገባው የምንታገልለተን የኦሮሞን ህዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እስከመገንጠል የሚል ዓለማ ወደ ጎን አድርገን አይደለም አሉ፡፡

የፓርቲው ሊቀመንበር ኦቦ ዳውድም ሀገር ቤት ከገቡ በኋላ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ የራስን ዕድል በራስ የመወስን መብት እስከ መገንጠል የሚለው ዓላማችንን እሰከ ምርጫው ድረስ እናዘገየው ይሆናል እንጅ ሙሉ በሙሉ አልተውነውም ሲሉ ተደመጡ፡፡ የኦቦ ዳውድ አስተያየት በምርጫ ከተሸነፍን ዋናውን አላማችንን ይፋ እናደርጋለን የሚል ውስጠ ወይራ ንግግር የያዘ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡

ኦነግ ወደ ሀገር ውስጥ ከመግባቱ በፊት የጀመረው ውዝግብ አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ባሰለፍነው ሳምንት መገባደጃ ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ጋር ቆይታ ያደረጉት ኦቦ ዳውድ ሰራዊታቸው ትጥቅ የሚፈታበት ምክንያት እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

ሌላው የፓርቲያቸው ሰው እንደውም መንግስት አባላቶቻችንን በሽብር ወንጀል እያሳዳደ ክስ እየመሰረተባቸው ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ለመንግስት ተደጋጋሚ መልዕክት ብንልክም ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎናል ሲሉም አስተውቀዋል፡፡ የኦነግ አባል መሆን ብቻውን ለዕስር የሚዳርግ ከሆነ ከቀደመው የተሸለ ስርዓት እንዴት ሊመጣ ይችላል ሲሉም የጠቅላይ ሚንትር ዓብይን አስተዳደር ወንጅለዋል፡፡

ከዚህ በተቃራኒው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የገጠር ዴክራሰሲ ዘርፍ ሀላፊው አቶ አዲሱ አረጋ በአንጻሩ ኦነግ ትጥቁን በፍጥንት ይፍታ ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡

መንግስትና ኦነግ አሁን ከሁለት አስርታት በፊት ወደነበረው ዕሰጣ ገባቸው ተመልሰዋል፡፡ በርካቶችም የየራሳቸውን ፍረድ ዕያሰቀመጡ ይገኛሉ፡፡ ከፊሉ ወገን ኢህአዴግ ብልጣ ብልጥ የፖለቲካ ስሌትን ሊከተል ቢያስብም ኦቦ ዳውድ አክሽፈውበታል ሲል ይናገራል፡፡ የዚህ ጎራ አባላት የመንግስትና ኦነግ ስምምነትን ሳናውቅ እንዴት ኦነግ ትጥቅ አልፈታም ማለቱን እንደነውር እንቆጥራለን የሚል አስተያየትም ይሰነዝራሉ፡፡

ከዚህ በተቃራኒው ያሉ አሰተያት ሰጭዎች ደግሞ ኦነግ መንግስትን እንደ ተራ ታጣቂ ቡድን አይቶ ማን ነው ማንን የሚያስፈታ ማለቱ ታላቅ ንቀት ነው ይላሉ፡፡ የሁለቱ ወገን እሰጣ ገባ ለጠቅላይ ሚንትር ዓብይ መንግስት የራሱን የቤት ስራ የሚሰጥ መሆኑ አያከራክርም፡፡ ጠቅላይ ሚንትር ዓብይ የሚመሩት ኢህአዴግ ከአቶ መለሱ ኢህአዴግ የሚለይበት አንዱ መንግድም አሁን የገባባትን ዕሰጣ ገባ የሚፈታበት ሂደት ይሆናል፡፡

አቶ መለስ በኦነግ የተሰጣቸውን ፈተና ወድቀውበታል፡፡ የድርጅቱን ዓባላት ጠራርገው ከሀገር ቢያባርሩም የቀሩትን ወደ ዘብጥያ ቢወረውሩም ኦነግን ግን ከሚሊዮኖች ልብ ውስጥ ለማጥፋት አልተቻላቸውም፡፡ ጠቅላይ ሚንሰትር ዓብይ አቶ መለስ የወደቁበትን ይህን ፈተና መውሰዳቸው የሚቀር አይመስልም፡፡ ጥያቄው ምርጫ አለው፡፡ በአንድ ሀገር ሁለት መንግስት እንዲኖር መፍቀድ አልያም አቶ መለስ የወደቁበትን መንገድ መከተል? ኦቦ ዳውድ ፈተናውን ይዘው ከዶ/ር አብይ ደጃፍ ደርሰዋል፡፡

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram