fbpx

እውነት ድግምት ይሰራል? በYona Bir

ኃይሌ ገብረስላሴ ስለ ጌጤ ዋሚ ቪዲዮ የሰጠውን አስተያየት አደመጥኩ። እንደተለመደው አስተያየቱ ከብዙ ሰዎች ውግዘትን አስከትሎበታል። ኃይሌ እንደሆነ አይሞቀው አይበርደው። ፈረንጆቹ እንደሚሉት “he speaks his mind”… ይቻመው!!!

በፌስቡክ የተለቀቀው ቪድዮ አትሌት ጌጤ ዋሚ በመምህር ግርማ መቁጥሪያ እየተደበደብች ድግምት ተድረገብኝ ብላ ስትለፈልፍ ያሳያል። ቪዲዮው እንደ ብዙዎቹ የሰይጣን ማስወጣት ድራማዎች እጅግ ያሳዝናል።

ኃይሌ ግን እንደ ብዙዎቻችን አዝኖ ዝም አላለም። ለሸገር ስፖርት በሰጠው ቃለ ምልልስ ለጌጤ የሚያስፈልጋት አጥማቂ ወይም ጸላዪ ሳይሆን ሳይኪያትሪስት መሆኑን፤ በሰይጣን መያዝ የሚባል ነገር አለመኖሩን፤ ድግምት ተደርጎብኝ በስፖርት ተሸነፍኩ ማለት የትም አለም ላይ የሌለ ኋላቀር ምክኒያት መሆኑን ተናገረ።

ኢትዮጵያውያን ውጤት ስናጣ በሰይጣን ላይ ማመኻኘት ይቀናናል። ነጋዴው ሲከስር ሰይጣን አከሰረኝ፤ ተማሪው ሲወድቅ መተት ተደረገብኝ፤ ሯጩ ማሸነፍ ሲያቅተው ድግምት ተሰራብኝ …

ኃይሌ ግን በድፍረት አጋንት (ድግምት) የሚባል ነገር የለም ይልሃል። ጠንክረህ ከሰራህ ታሸንፋለህ፤ ጠንክረህ ካልሰራህ ወይም ካንተ የተሻለ ተወዳዳሪ ሲመጣ ደግሞ ትሸነፋለህ። ይህ የማይለወጥ ሃቅ ነው።

ሆኖም ግን ብዙዎቹ አትሌቶቻችን ድግምትና መተት ሊሰራባቸው እንደሚችል በማሰብ ይጨንቃሉ። ከነዚህ አትሌቶች ስሟ በተደጋጋሚ ይጠራ የነበረችው አትሌት መሰረት ደፋር ናት። መሲ ምንም እንኳን ታላቅ አትሌት ብትሆንም ከጥሩነሽ ዲባባ ብርቱ ፉክክር ያጋጥማት ነበር። ሁለቱ ታላላቅ አትሌቶች በአንድ ዘመን መጥተው ለረጅም ዘመን ሲፎካከሩ ቆይተዋል። ሁለቱም ጎበዞች ናቸው። ሆኖም ግን ጥሩነሽ ደጋግማ ስታሸንፍ የተለመደው ሃሜት ይናፈስ ጀመር።

መሰረት ደፋር ጥብቅ የኦርቶዶክስ አማኝ በመሆኗ ጥሩነሽ ዲባባ መተት አሰርታባት ነው የምታሸንፋት የሚል ሃሜት በስፋት ይወራ ነበር። ይህ ሃሜት ተራ ወሬ እንዳልሆነ ያወቅኩት አትሌት መሰረት ደፋር ለንደን ኦሎምፒክ ላይ ጥሩነሽ ዲባባ 10ሺ ሜትር ካሸነፈች በኋላ 5ሺ ሜትር ላይ ደግማ ብትሰለፍ ወርቅ ልታሸንፍ ትችላለች በሚል ባልተዘጋጀችበት ውድ ድር እንድትገባ ተደርጋ መቶ ሜትር እስኪቀር ስትመራ ቆይታ መጨረሻ ላይ መሲ ተፈትልካ በመውጣት ካሸነፈቻት በኋላ ደብቃ የያዘችውን የማርያም ስእል መዥረጥ አድርጋ አውጥታ እያለቀሰች ለአለም ካሜራ ያሳየች ጊዜ ነበር።

አብዛኛው አማኝም ማርያም መተቱን ሰበረችው ብሎ ጉድ አለ።

ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ሰሞኑን እስራኤል ዳንሳ የተባለ ኮሜዲያን ነብይ አንዱን ወጠምሻ ጎረምሳ አስነስቶ በእግር ኳስ ተጫዋችነት እግዜር እንደቀባው፤ ፕሪሚየር ሊግ ላይ እንደሚጫወት፤ ወደ ተቃራና አቅጣጫ እንኳን ቢመታ ተጠማዞ ጎል እንደሚቆጠርለት፤ ደሞዙ በሳምንት በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር እንደሆነና የዚያን ጊዜ ለእስራኤል ዳንሳ ቤተክርስቲያን አስራት መስጠት እንዳይረሳ ትንቢት ሲናገር አየሁ።

Getty Images

እንግዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ ስፖርት በሰዎች ችሎታና ጥረት የሚደረስበት ሳይሆን በእግዜር ቅባት የሚገኝ ውጤት እንዲሁም በሰይጣን ድግምት የሚጠፋ መንፈሳዊ ውጊያ ሆኗል።

ብዙዎቻችን ኃያሌ የተናገረው ከማውገዝ በፊት የሚከተሉትን ጥያቄዎች መጠየቅ መልካም ነው

ሌላው አለም ላይ ሊጠፋ የተቃረበው <ሰይጣን ይዞኛል እያሉ መለፍለፍ> እኛ አገር ለምን እንዲህ ገነነ?

ሳይንስ እንደሚለው በሰይጣን ተይዣለሁ ብሎ መጮህ የአይምሮ በሽታ ምልክት ነው?

አንድ ሰው ድግምት ከተሰራበት ውጤት ሊያጣ ይችላል?

ድግምት፤ መተት፤ ሟርት በቀሳውስት (ፓስተሮች) የሚሰበር (የሚመክን) ድርጊት ነው?

ሌላው አለም ይሄን ችግር እንዴት ሊፈታው ቻለ?

ከረጅም ጊዜ በኋላ በዚህ ደፋር አስተያየቱ ኃይሌን ሳላደንቀው ማለፍ አላቻልኩም።

Getty Images

 

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram