fbpx

‹‹እኛ በራችንን ዘግተን ስንቀመጥ በዓለም ላይ ግን መሄጃ ያጣ የገንዘብ ውቅያኖስ አለ›› አቶ ኤርሚያስ አመልጋ፣ የፋይናንስና የኢኮኖሚ ባለሙያ

በአሥራት ሥዩም

አቶ ኤርሚያስ አመልጋ አክሰስ ሪል ስቴት ኩባንያን በማቋቋምና በቦርድ አመራር ሥራ አስፈጻሚነት  በመምራት እስከ ቅርብ ጊዜ ድርስ መርተውታል፡፡ በርካቶች አዳዲስ የኢንቨስትመንት ሐሳቦችን በኢትዮጵያ የተገበሩ፣ የፋይናንስ ኢንዲስትሪው ውስጥ ባለአንድ ቅርንጫፍ ባንክ የሚል መነሻም ዘመን ባንክን ያደራጁ እየተባሉም ይጠቀሳሉ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ የተወለዱት አቶ ኤርሚያስ ያደጉትና አፋቸውን የፈቱት ግብፅ ውስጥ በዓረብኛ ቋንቋ ነው፡፡ ከግብፅ ወደ ኬንያናይሮቢ በማቅናትም የእንግሊዝኛና የስዋህሊ ቋንቋዎችን አቀላጥፈው ለመናገር ያስቻሏቸውን ጊዜያት በኬንያ አሳልፈዋል፡፡ በታዳጊነታቸው ወቅትም ወደኢትዮጵያ በመመለስ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአሜሪካ ኢንተርናሽናል ኮሙዩኒቲ ስኩል በማጠናቀቅ፣ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ለአንድዓመት ከተማሩ በኋላ ወደ አሜሪካ በማቅናት ኑሯቸውን በዚያው መሥርተው ቆይተዋል፡፡ ከ22 ዓመታት በፊት ዳግመኛ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት አቶ ኤርሚያስ፣ በአሜሪካ ዎልስትሪት የካፒታል ገበያ ውስጥ በመሥራት ልምድ እንዳካበቱ፣ ወደ ኢትዮጵያ የመጡትም ይህንኑ ልምድና ዕውቃተቸውን መነሻ በማድረግ በልዩ ልዩ ኢንቨስትመንት መስኮች ለመሰማራት እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ ይሁንና በርካታ ውጣ ውረዶችን ዓይተዋል፡፡ አሁንም ድረስ ያልተቋጨው የአክሰስ ሪል ስቴት ቤት ገዥዎች ጉዳይ ትልቁና ምናልባትም የኢንዱስትሪውን አካሄድ በእጅጉ የቀየረ ክስተት መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ከሰሞኑ በተስተዋሉት መሠረታዊ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ እንደ ኢኮኖሚ ባለሙያነታቸው የአገሪቱን ኢኮኖሚ ከየት ወዴት እንደሆነ በቅርቡ ባወጡት ጽሑፍ ተንትነተዋል፡፡ መንግሥት ሙሉ በሙሉና በከፊል ለግል ባለሀብቶች ለማስላለፍ ስለወሰናቸው ድርጅቶች፣ አገሪቱ ስለምትገኝበት የብድርና የውጭ ምንዛሪ ቀውስ ብሎም ስለውጭ ኢንቨስተሮች አስፈላጊነት ያላቸውን ምልከታ አሥራት ሥዩም ከአቶ ኤርሚያስ ጋር ቆይታ በማድረግ የሚከተለውን አጠናቅሯል፡፡

 

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በዋጋ ግሽበት፣ እንዲሁም በኢንቨስትመንትና በሌሎችም ኢኮኖሚያዊ ሁነቶች መቀዛቀዝ ሳቢያ የሚከሰተው ‹‹ስታግፍሌሽን›› እየተባለ በሚጠራው የኢኮኖሚ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ በጽሑፍዎ አሥፍረዋል፡፡ ወደዚህ ድምዳሜ እንዴት ሊያመሩ ቻሉ?

 

አቶ ኤርሚያስ፡- ከመረጃ በመነሳት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ መንግሥትም ሆነ የውጭ ድርጅቶች ስምንት፣ ዘጠኝ ወይም አሥር በመቶ የሚገመት ዕድገት እንደሚኖር እየተነበዩ በመጣንበት ወቅት እንዴት እዚህ ሁኔታ ውስጥ ልንደርስ ቻልን? የሚለው መታየት አለበት፡፡ እንደ የዓለም ባንክ፣ የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እና በውስጣቸው ያሉ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንዴት ነው ሊሳሳቱ የሚችሉት? እኔ እንደሚገባኝ የመረጃ መጓተት ያመጣው ሊሆን እንደሚችል ነው፡፡ ኢኮኖሚክስ እንደ ፊዚክስ ያለ ሳይንስ አይደለም፡፡ የማኅበራዊ ሳይንስ አካል ነው፡፡ በጣም በርካታና እርስ በርሳቸው የተያያዙ ተለዋዋጭ ግብዓቶች ያሉት ሳይንስ ነው፡፡ ንድፈ ሐሳቡ እንደ ነባራዊው ሁኔታ የተለያየ ውጤት ሊያስገኝ የሚችል፣ በይሆናል ወይም በመላምት ላይ የተመሠረተ ሳይንስ ነው፡፡ የእኛ አገር ኢኮኖሚ ትንበያም እነዚህ ተቋማት የሠሩትና ሌሎች መላ ምቶችን አካትቼ በጽሑፉ ያስቀመጥኩት ችግር ሊኖር ይችላል ብዬ ነው፡፡ እንዲያውም መሬት ላይ ከማየው መረጃ አኳያ ችግር አለ ብያለሁ፡፡ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ስንት ፋብሪካ ተዘጋ ብዬ ብጠይቅህ አታውቅም፡፡ እኔም አላውቅም፡፡ ነገር ግን ሥራ ላይ ስላለሁ፣ በርካታ ፋብሪካ ያላቸው ሰዎችም ስለማውቅ ሁሉም የሚናገሩት አንድ ቋንቋ ነው፡፡ ሠራተኞች እየቀነሱ ነው፡፡ በትንሹ አሥር ያህል ልቆጥርልህ እችላለሁ፡፡ ይህ ግን መረጃው ውስጥ የለም፡፡ ለምንድን ነው የሚዘጉት ያልን እንደሆነ ግን ጥሬ ዕቃ እያጡ ነው፡፡ ኢኮኖሚው በከፍተኛ የገቢ ንግድ እንቅስቃሴ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ፍጆታችንም ሆነ ኢንቨስትመንታችን በከባድ የገቢ ንግድ ላይ የተንጠለጠለ ነው፡፡ ፍላጎታችን ከአቅማችን በላይ መሆኑ አይደለም፡፡ የመጀመርያውም ሆነ ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶች ከሚዘረዝሩት በላይ የመንቀሳቀስ አቅም አለን፡፡ ነገር ግን አቅማችንን አላወቅነውም፡፡ ብዙ ገንዘብ ባንክ ውስጥ አስቀምጦ በውጭ ምንዛሪ ከባንክ መበደር አንድ ችግር ነው፡፡

 

ከሥር ጀምረን ብናይ በንጉሠ ነገሥቱ ጊዜ የስቶክ ወይም የካፒታል ገበያ ነበረን፡፡ ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ያላት አገር ነበረች፡፡ ይህንን ግን የሚያስበውም የሚያውቀውም የለም፡፡ የሕዝቡ ቁጥር ትንሽ ነበር፡፡ ኢኮኖሚው እየተነሳና በለውጥ ሒደት ላይ ነበር፡፡ የወጪ ንግዱ ከገቢ ንግዱ በሰፊው ይበልጥ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ብር በዶላር የሚመነዘረው በሁለት ብር ብቻ ነበር፡፡ በቋሚነት ነበር ይህ የሚሆነው፡፡ ዶላር ከፈለግክ ዶላሩ፣ ብርም ከፈለግክ ብሩ ነበር፡፡ ኢንዱስትሪን ካየን አብዛኛው የመንግሥት ድርጅቶች የሚባሉት ከየት መጡ? በሁለት የሚከፈሉ ናቸው፡፡ አንደኛው ደርግ ሲመጣ በአዋጅከእንግዲህ የእኔ ናቸው በማለት የወረሳቸው ናቸው፡፡ እነዚህ መመለስ አለባቸው፡፡ ሁለተኛው በሶሻሊስት ሥርዓት የግሉን ዘርፍ በማጥፋት ፋብሪካ የሚገነባው፣ እርሻ የሚያስፋፋው መንግሥት ነው አለ፡፡ የመንግሥት ድርጅቶች የሚባሉት በዚህ መንገድ የመጡ ናቸው፡፡ የግሉ ዘርፍ አሁን ያልፈጠራቸው ነገር ግን ከ50 ዓመታት በፊት የተፈጠሩ ትልልቅ ፋብሪካዎች በወቅቱ እንዴት ሊፈጠሩ ቻሉ? አሁንስ እነሱን እንዴት መፍጠር አቃተን? አሁን ካለው የቴክኖሎጂ ምጥቀት አኳያ የእነዚያን አሥር እጅ ብልጫ ያላቸው ድርጅቶችን መፍጠር ነበረብን፡፡ ነገር ግን በኢኮኖሚው ሥርዓት ምክንያት ነው እንዲህ ያለውን ለውጥ ያላመጣነው፡፡

 

በንጉሠ ነገሥቱ ጊዜ 16 የውጭ የመድን ድርጅቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንሹራንስ ይሸጡ ነበር፡፡ ትርፍ ሲኖራቸው ገንዘባቸውን ወደ አገራቸው ይልካሉ፡፡ ስለውጭ ምንዛሪ የሚያስብ አልነበረም፡፡ ባንክም ብናይ እንደዚሁ ነው፡፡ በርካታ የውጭ ባንኮች ነበሩ፡፡ የጣሊያን፣ የህንድና ሌሎችም ነበሩ፡፡ መንግሥት ከወረሳቸው ፋብሪካዎች ውስጥ በርካቶቹ የውጭ ነበሩ፡፡ አርመኖች፣ ግሪኮች፣ ጣሊያኖች፣ የመኖች፣ ህንዶችና ሌሎችም ነበሩ፡፡ በዚህ ሥርዓት ውስጥ በኢትዮጵያ ፕራይቬታይዜሽን ፕሮግራም መሠረት የመንግሥት ድርጅት ከገዙ የመጀመርያዎቹ ሰዎች አንዱ ነኝ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1996 ማለትም የዛሬ 22 ዓመታት ገደማ ማለት ነው፡፡ ወደ ኢትየጵያ ለመመለስ ስለወሰንኩ ድርጅቱን ሳላየው ነው የገዛሁት፡፡ ቦታ ነበር የምፈልገው፡፡ የፋብሪካው ባለቤት ሚስተር ፔትራቶስ የተባሉ ግሪካዊ ነበሩ፡፡ እሳቸው የተከሉትን ፋብሪካ ነው የገዛሁት፡፡ ብዙዎቹ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በንጉሡ ጊዜ የተተከሉ መሣሪያዎች ነው ያሏቸው፡፡ እንደ ፋብሪካ ብዙም ዋጋ የላቸውም፡፡ መሬቶቹ ናቸው ዋጋ ያላቸው፡፡ ነጥቡ ግን ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ነበራት፡፡ የምንፈራውና የመቆጣጠር አቅም የለንም ብለን በሩን ዘግተንበት ቁጭ ባልነው የፋይናንስ ዘርፋችን ግን፣ እነ ኬንያ በግኝ ግዛት ውስጥ በነበሩ ጊዜ ጀምሮ እኛ የስቶክ ኤክስቼንጅ ገበያዎች ነበሩን፡፡ ከንጉሡ ጀምሮ ፋብሪካዎች ውስጥ ኢንቨስት ያደርጉ ነበር፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ትልቅ ኢንቨስተር ስለነበር በስቶክ ገበያው ውስጥ ትልቅ ድርሻ ይጫወት ነበር፡፡ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት በሚፈለገው ዘርፍ ውስጥ የአክሲዮን ድርጅት በሚቋቋምበት ወቅት የመንግሥት ተቆጣጣሪው ብሔራዊ ባንክ 30 ወይም 40 በመቶ የአክሲዮን ድርሻ ይገዛ ነበር፡፡ ግብፅና ደቡብ አፍሪካ ትንሽ ቢቀድሙን እንጂ አፍሪካን እየመራን ነበርን፡፡ አሁን ግን እነ ሶማሊያ ቀድመውን የመጨረሻዎቹ ሆነናል፡፡

 

ሰው ከተማውን እየለቀቀ ገጠር በመግባት የግብርና ሥራ ላይ መሰማራት በመጀመሩ የሰፋፊ እርሻ ሥራ መነሳት ጀምሮ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ለፍጆታዋ የሚስፈልጓትን ነገሮች ታመርት ነበር፡፡ የዘይት ችግርን እንደ ምሳሌ ብናነሳ እንኳ እኔ በወቅቱ የገዛሁት የዘይት ፋብሪካ የገበያ ችግር ስለነበር ጭምር ነው፡፡ የማምረት ሳይሆን የገበያ ችግር ነበር የነበረው፡፡ ዘይት ሁሉ ቦታ ስለሚፈለግ በየሠፈሩና በየቀበሌው አነስተኛ የዘይት መጭመቂያ ተከፍቶ ነበር፡፡ የቅባት እህል እንደ ልብ ነበር፡፡ ዛሬ ግን ዘይት ችግር በመሆኑ መንግሥት ታች ወርዶ ዘይት እየገዛ ማከፋፈል ውስጥ ሲገባ ማየት የገበያ ሥርዓታችን ማሳያ ምሳሌ ነው፡፡ ስኳሩም እንዲሁ የሚታይ ነው፡፡ አሁን እኮ ሱፐርማርኬት ገብተህ የምትፈልገውን አታገኝም፡፡ መኪና ሲበላሽ መለዋወጫ አታገኝም፡፡ ፋብሪካ ውስጥ ማሽን ሲበላሽ አንዲት ተራ ነገር ለመተካት ሳምንት ለመቆም ትገደዳለህ፡፡ ከዚህም በላይ ችግሩ ተባብሷል፡፡ የኢኮኖሚው መዋቅር፣ የገበያ ሥርዓቱና ትስስሩ፣ ሸማችና አቅራቢ የተላለፉበት የዘፈቀደ ሥርዓት ተፈጥሯል፡፡ ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ሲመጣ የወረሰው ኢኮኖሚ ባዶ ነበር፡፡ ሆኖም የኢሕአዴግ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሦስት ጊዜ ተቀይሮ ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ሲገባ አገሪቱ መሣሪያ የተገዛበት ብዙ ዕዳ ተሸክማ ነበር፡፡ ለረሃብና ለሌላውም ተብሎ በመጣው ብድር ሳቢያ ሊከፈል የማይችል ዕዳ ተቆልሎባት ነበር፡፡ ይህንን ነው ኢሕአዴግ የተረከበው፡፡ ሶቪዬት ኅብረት በወቅቱ ተዳክሞ ስለነበር ገንዘብ ለማግኘት የነበረው አማራጭ ወደ አይኤምኤፍ መሄድ ነበር፡፡ አይኤምኤፍ ግን ኢኮኖሚውን ነፃ አድርጉ ይል ነበር፡፡ ክፍት አድርጉት ይል ነበር፡፡ አገር ተረክበዋል፡፡ አገሩን ማንቀሳቀስ አለባቸው፡፡ ነገር ግን ኢኮኖሚው ባዶ ነው፡፡

 

በዚያን ወቅት በርካታ ድርጅቶች ወደ ግል ተዛውረዋል፡፡ በወቅቱ የፕራይቬታይዜሽን መሥሪያ ቤት ኃላፊ በነበሩት በአቶ አሰፋ አብረሃ ጊዜ በርካታ ተቋማት ወደ ግል ተዛውረዋል፡፡ በወቅቱ ከዓለም ባንክ በተገኘ ድጋፍ የፕራይቬታይዜሽን አካሄድ ምን ይመስላል የሚለውን የመጀመርያ ግምገማ ጥናት የሠራነው እኔና አቶ ታዴዎስ ሐረገወይን በመሠረትነተው ኢስት አፍሪካን ኢንቨስትመንት ሴኩሪቲስ በሚባል ድርጅት አማካይነት ነበር፡፡ ድርጅቱን የመሠረትነት የስቶክ ገበያ ለማቋቋም፣ ፕራይቬታይዜሽንና ሌሎችም ነገሮች ላይ ጥናት ለማድረግ ነበር፡፡ 500 ሺሕ ዶላር ከዓለም ባንክ ተገኝቶ ነበር፡፡ እኔ በተለይ በሠራሁት ክፍል እነዚህን ድርጅቶች ወደ ግል ይዛወሩ ብንል ማነው ሊገዛቸው የሚችለው የሚለውን አጥንቼ ነበር፡፡ በወቅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው የውጭ ባለሀብት ኢትዮጵያዊት አግብቶ ወይም በሌላ መንገድ ካልሆነ በቀር፣ ይህ ነው የሚባል የውጭ ባለሀብት አልነበረም፡፡ ኢትዮጵያዊውና የውጭው ባለሀብት በምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ? የሚለውን ሁሉ አጥንቼ ነበር፡፡ ይህ ተደርጎ ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተዘርግቶ፣ የደከመውን ኢንዱስትሪ በማንሳት ከውጭ የሚገባውን ዕቃ የሚተካና የሚደግፍ ሥራ ስንሠራ ጊዜ የነበረው ዕዳ በሙሉ ተሰረዘ፡፡ ከዚያ በኋላ ለመደበርም ያበቃን ይኸው ነው፡፡ በወቅቱ ባዶ ኢኮኖሚ በመረከባቸው ገንዘብ አልነበረም፡፡ የኢኮኖሚ ፖሊሲም አልነበረም፡፡ መሠረታዊ አካሄዱ ነፃ ገበያ በሚል አካሄድ ነበር የተጀመረው፡፡ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር በመድረክም እየተገናኘን በጽሑፍም እየላኩላቸው ሐሳብ ተለዋውጠናል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያለች አገር ገና ለመነሳት በምትፍጨረጨርበት ወቅት የነፃ ገበያ ፖሊሲ አይሠራም፡፡ የትኛውም አገር ሲጀምር በነፃ ገበያ አልጀመረም፡፡ ልማታዊም ይባል ወይም ሌላ ብቻ አብዛኞቹ የዓለም አገሮች ደሃ ሆነው ነው የጀመሩት፡፡ ቴክኖሎጂም ምርታማነትም ስሌለ ሁሉም ደሃ ነው፡፡ በመሆኑም ልማት ላይ የሚያተኩር ግፊት ማድረግ የሚችል የኢኮኖሚ ሥርዓት እንደሚያስፈልግ በ27 ገጽ ወረቀት ጽፌ ልኬላቸው ነበር፡፡ ነፃ ገበያ በሒደት ነው የሚመጣው፡፡ ሕፃን ልጅ በሒደት ነው የሚራመደው፡፡ ሳይራመድ አይሮጥም፣ አይዘልም፡፡ የአሥር ዓመት ልጅ መቶ ኪሎ አንሳ አይባልም፡፡ ይህ ሁሉ ቢባልም አልሠራም፡፡

 

ኢትዮጵያ የነፃ ገበያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ መከተል በጀመረችባቸው የመጀመርያዎቹ ዓመታት ወቅት የነበረው ኢኮኖሚ ዕድገት ሦስት በመቶ ወይም አምስት በመቶ ብቻ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ምን ዓይነት ተዓምር ነው የተፈጠረው? ለውጡ መምጣት የጀመረው በምን ምክንያት ነው ብንል ገንዘብ መደበር በመቻላችን ነው፡፡ አንደኛ ነገር ልማታዊ መንግሥት የሚለውን አዲስ ስትራቴጂ አመጣን፡፡ አንደኛውና ሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አመጣን፡፡ ከዚያም በፊት መንግሥት ኢኮኖሚው ውስጥ በመደበኛነት ገባበት፡፡ ‹‹ቢግ ፑሽ›› የሚባለው ንድፈ ሐሳብ ምን ይላል? አንድ ኢኮኖሚ ከመሬት እንዲነሳ ካስፈለገ ልክ እንደ ትልቅ ጃምቦ ጄት አውሮፕላን ለአጭር ጊዜ የሚቆይ ፍጥነት በማግኘት መነሳት አለበት ይላል፡፡ ትልቅ ኢንቨስትመንት መደረግ አለበት፡፡ ሥራ መፈጠር አለበት፡፡ እንቅስቃሴ መጀመር አለበት ማለት ነው፡፡ የመንግሥት ሚና ደግሞ መሠረተ ልማት መገንባት ነው፡፡ መንገድ የሌለበት፣ መብራትና ውኃ የሌለበት፣ የተማረና ጤነኛ የሰው ኃይል በሌለበት ዕድገት አይኖርም፡፡ በቢግ ፑሽ ጊዜ የመንግሥት ሚና ኢኮኖሚውን በመግፋትና በፍጥነት በማስነሳት ማስኬድ መቻል ነው፡፡ ቅድም የጠቀስናቸውና በንጉሠ ነገሥቱ ጊዜ የነበሩት ነገሮች ቀጥለው ቢሆን ኖሮ አሁን ላይ የት እንደርስ ነበር? ምን እንሆን ነበር? ግን መሀል ላይ በመቀጨቱ ተመልሶ ከዕዳ የሚነሳበት ችግር ተፈጠረ፡፡ መንግሥት የነበረው አማራጭ መበደር ነበር፡፡ ችግሩ የሚመጣው ግን ገንዘቡን ልማት ላይ አውለህ፣ ልማቱ በሥርዓቱ ካልተሠራበት ብድሩ የሚከፈልበት ገንዘብ አይኖርም፡፡ መንገድ መሠራቱ ተገቢ ሆኖ ሳለ መንገዱ በራሱ ግን ገንዘብ አይከፍልም፡፡ መሠረተ ልማቱ ለማን ነው የሚሠራው? ቢባል ለግሉ ዘርፍ ነው ማለት ነው፡፡ ይህንን ግን ረሱት፡፡ መሠረተ ልማቱ ሲሠራ የግሉ ዘርፍም አብሮ መኮትከት ነበረበት፡፡ መንገዱ ሲሠራ የሚመላለስበት መኪና ከሌለ፣ ወደ ገበያው የሚንቀሳቀስ ነገር ከሌለ አስቸጋሪ ነው፡፡ እስካሁን የመጣንበትን መንገድ በኢኮኖሚክስ ሳይንስ ለማስረዳት የሚያስቸግረው አካሄድ የግል ዘርፉን ወደ ጎን ማለታችን ነው፡፡ መንግሥት እኔው ራሴ አለማለሁ አለ፡፡ የግሉ ዘርፍ የሚችለውን ያድርግ፣ የማለማው ግን እኔ ነኝ አለ፡፡ ሳይንስ ከሚለውና መሠረተ ልማት ከሚለው ጽንሰ ሐሳብ በመውጣት ኢንዱስትሪ እገነባለሁ አለ፡፡ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የሚባል አስፈሪ ተቋም እፈጥራለሁ አለ፡፡ ቢሳካለት ጥሩ ነበር፡፡ ነገር ግን መንግሥት በተፈጥሮ ባህሪውና በማንነቱ እንዲህ ያለውን ሥራ ሊሠራ አይችልም፡፡ በሌለን ገንዘብ ያውም ተበድረን ያመጣነውን የውጭ ምንዛሪ በማይሆን ነገር ጉድጓድ ውስጥ ከተትነው፡፡  ስኳር ልማት ብትል ያው ነው፡፡ መንግሥት ይህንን ትልቅ ድርሻ ይዞ ለግዙ ዘርፍ ትንሽ ቦታ ቢተውለትም መልካም ነበር፡፡ ይህንንም ማድረግ አልቻለም፡፡

 

የባንክ ብድር በሙሉ ተመርጦ ብሔራዊ ባንክ ይገባና ወደ ልማት ባንክ ብድር ስጡ ተብሎ ይላካል፡፡ ልማት ባንክ ብድር መስጠት አይችልበትም፡፡ ከሰጠም የተበላሸ ነው የሚሰጠው፡፡ የግል ባንኮች ተጨቁነውና ተረግጠው ነው የሚንቀሳቀሱት፡፡ ፕሮጀክቶቹ በጣም ትልልቅ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ታላቁ የህዳሴ ግድብ አራት ቢሊዮን ዶላር ይጠይቃል፡፡ ግድቡ እንደሚሠራ በተገለጸበት ወቅት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አንፃር 40 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ያለፋይናንስ ዕቅድ  የኢኮኖሚውን አሥር በመቶ አንድ ፕሮጀክት ይዞት ነበር፡፡ ይህ ሲሆን ታዲያ እንዴት ነው ፕሮጀክቱ የሆነ ቦታ ሄዶ የማይቆመው? ይህ አንድ ምሳሌ ነው፡፡ መንግሥት መግባት በማይገባው ሥራ ውስጥ ገባ፡፡ ሲገባም የፋይናንስ ዕቅድ ሳይኖረው ነው የገባው፡፡ ለዚህ እኮ ነው የዛሬ ስድስትና ሰባት ዓመት ይኼ ነገር አያስኬድም ብለን ተንትነን የጻፍነው፡፡ በግልጽና በሚታይ መንገድ የኢኮኖሚክስ ጽንሰ ሐሳብ የገባው ሰው ሊናገረው የሚችለው ነገር ነበር፡፡ ይህች አገር እንድትለማ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ያስፈልጋታል፡፡ ቢግ ፑሽ ንድፈ ሐሳብም ይህን ይደግፋል፡፡ ትልቅ ግፊት ያስፈልጋል፡፡ መደበርም ካስፈለገ ማምጣት አለብን፡፡ ነገር ግን ውጤት ያለው ሥራ ላይ መዋል አለበት፡፡ ለምን ቢባል ትልቅ ብድር አደጋ ስላለው ነው፡፡ መንግሥት ንግድ ሥራ ውስጥ ገብቷል፡፡ እንደታሰበው ግን ሥራው ላይሄድ ይችላል፡፡

 

ሪፖርተር፡- በቢግ ፑሽ ንድፈ ሐሳብ መሠረት በሌሎች አገሮች ውስጥ የነበረው የግሉ ዘርፍ ሚና ምን ነበር? በእኛስ አገር እንዴት ተስተናግዷል?

 

አቶ ኤርሚያስ፡- ለምሳሌ ቻይናን እንይ፡፡ በግሌ በተወሰነ ደረጃ የቻይና አድናቂ ነኝ፡፡ በተወሰነ ደረጃ ግን አይደለሁም፡፡ መሠረቱ ስንጥቆች አሉት፡፡ ቻይናም እንደ እኛ በብድር ነው ያለችው፡፡ ከአገር ውስጥም ከውጭም ትበደራለች፡፡ የፖለቲካ ጥያቄ አለ፡፡ ሥራ ያስፈልጋል፡፡ ትልልቅ የቻይና የኢኮኖሚ ዘርፎች ኪሳራ አመንጪ ከመሆናቸውም ባሻገር፣ በተለይ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በርካታ በመንግሥት የተያዙ ድርጅቶች መክፈል የማይችሉት ብድር አለባቸው፡፡ ነገር ግን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች አሉዋቸው፡፡ የፖለቲካ ጥያቄ ስለሆነና አቅሙም ስላላቸው ያንቀሳቅሱታል፡፡ የዛሬ 20 ዓመታት ገደማ የግሉ ዘርፍ እንደሚያስፈልጋቸው ገብቷቸዋል፡፡ ነገር ግን ካላቸው የተፈጥሮ ሀብት ይልቅ ለሥራ የሚመች የሕዝብ ብዛት፣ ትልቅና ግዙፍ ገበያ አላቸው፡፡ ነዳጅ ለአንድ አገር የሀብት ምንጭ ነው፡፡ ትልቅ ሕዝብ የሀብት ምንጭ ነው፡፡ ለምን ቢባል ትልቅ የፍጆታ ገበያ ስለሚፈጥር ነው፡፡ እርግጥ ነው ሥራ ፈጥረህለት፣ አምራች አድርገኸው፣ ራሱን ችሎ መኖር እንዲችል ካላደረግከው ግን ትልቅ ዕዳ ስለሚሆን ጎትቶ ወደ ታች ያወርድሃል፡፡ ቻይና ትልቅ አገር ነች፡፡ በዓለም ላይ ካሉት ትልልቅ ገበያዎች ይልቅ ትልቅ ዕድገት እያሳየችና ትልልቅና ግዙፍ የሚባሉ የምዕራቡ ዓለም ፋብሪካዎች፣ በተለይም የውጭ ኢንቨስተሮችና ዳያስፖራው በመግባታቸው የመንግሥት ድርጅቶች ትልቅ ኪሳራ እያስተናገዱም በድጎማ እየተጓዙ ነው፡፡ በዓለም ደረጃ ቢሊየነሮች የተባሉ የቻይና የግል ዘርፍ ተዋናዮች አሏቸው፡፡ ትልቅና ጠንካራ የፋይናንስ ዘርፍ አላቸው፡፡ ትልቁን ግፊት ካደረጉም በኋላ በውጭው የግል ዘርፍ አማካይነት የአገራቸውን የግል ዘርፍ ደረጃ በደረጃ ጠንካራ እንዲሆን አግዘውታል፡፡ ከእኛ ጋር ያለው ልዩነት ይኼው ነው፡፡ ኮሪያና ታይዋንም ብንሄድ ኢኮኖሚያቸው በሁለት እግሩ የቆመው በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ ሚና ነው፡፡

 

እኛ በአንድ እግር እንቆማለን አልን፡፡ አንድ እግር ውሎ አድሮ መድከሙ አይቀርም፡፡ ሚዛንም የለውም፡፡ ሲደክመውም ወደ አንዱ አቅጣጫ ይወድቃል፡፡ መንግሥት እኔው እገነባለሁ አለ፡፡ ተበድሮ ገባበት፡፡ ውጤቱ ያው የመንግሥት ሥራ ውጤት ነው፡፡ አንደኛው እግሩ ማለትም የግሉ ዘርፍ ደም ሥር ሁሉ ተደፋፍኗል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ችግሩ የመንግሥትን ፕሮጀክቶች ከማቆም አልፎ ወደ ግሉም እየመጣ ነው፡፡ የመንግሥትም ሆነ የግሉ ካዝና በብርም በውጭ ምንዛሪም ባዶ ሆኗል፡፡ ይኼ ነገር በሌሎች አገሮች ውስጥም ተከስቷል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1970ዎቹ እስከ 1980ዎቹ በላቲን አሜሪካ ተከስቷል፡፡ ብድር የወሰደ ሰው ብድሩ እስኪያልቅ ድረስ እንደፈለገው ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ በመሆኑም ነው የመንግሥት ፕሮጀክቶችና መሠረተ ልማቶች በብድር መገንባት የለባቸውም ስንል የነበረው፡፡ በኢትዮጵያ በታሪክ አጋጣሚ ደርግ የግሉን ዘርፍ ንብረት ወርሶ ይዞ ስለነበር፣ በግሉ ዘርፍ ይዞታ ውስጥ መሆን የሚገባቸውን የንግድ ተቋማት ፈጥሮም ስለነበር ቀድሞውኑ መሆን ያልነበረበት ነገር መደረጉ እንዳለ ሆኖ፣ አሁንም ድረስ እነዚህ ተቋማት በመንግሥት እጅ ስላሉ ትልቅ ተቀማጭ አለ ማለት ይቻላል፡፡ በጊዜ ሒደት አድጓል፡፡ በግል ቢያዝ ኖሮ ግን ከዚህም በላይ ያድግ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህን ሁሉ በእጃችን ይዘን እንዴት ነው ዶላር የለንም የምንለው? ለብሩ ብቻም ሳይሆን የአገሪቱ ኢኮኖሚ ሚዛኑን እንዲጠብቅ የግሉ ዘርፍም እንደ ልብ መኖር እንዲችል ይደረግ፡፡ ይህ ግን አልተደረገም፡፡ ለምን ብትለኝ ችግር የገጠመው ሰው እኮ ቤቱን፣ መኪናውን፣ ወርቁንና ሌላውንም ንብረቱን ይሸጣል፡፡ የልማት ድርጅቶች ግን መንግሥት አይፈልጋቸውም፡፡ ሊፈልጋቸውም አይገባም፡፡ ሥራው አይደለም፡፡ ቦታው አይደለም፡፡

 

ሰሞኑን ወደ ግል ይዛወራሉ የተባሉት ድርጅቶችን በሚመለከት የተለያዩ ሰዎች ትንተና እየሰጡ ነው፡፡ እኔ የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት ነው ሲባል ይህንን ነገር አስረዳ፣ ግልጽ አድርግልኝ ብትለኝ ለማስረዳት ይቸግረኛል፡፡ በሳይንሱ ውስጥ የሚገኝ ጽንሰ ሐሳብ አይደለም፡፡ መንግሥት ማን ነው? መንግሥት ከሕዝብ የወጡ አገር እንዲያስተዳድሩ የተመደቡ ግለሰቦች የፈጠሩት ነው፡፡ መንግሥት ፋብሪካውንና ሌላውንም የልማት ድርጅት በይዞታው አደረገ ማለት የተወሰነ የኅብረተሰብ ክፍል መጠቀሚያ መሆኑ በታሪክ የታወቀ ነው፡፡ ሰፊው ሕዝብ አገልግሎት በማጣት፣ ውድ ዋጋ በመክፈል፣ የተባለሸና ደካማ አገልግሎት በማግኘት ይቸገራል፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር ቢበላሽብህ በወቅቱ መጥቶ የሚሠራልህ የለም፡፡ የትኛው ገበሬ ነው ኢትዮ ቴሌኮም የሕዝብ በመሆኑ የተጠቀመው? ትርፉን ዓይቷል? አገልግሎቱን ዓይቷል? አላየም፡፡ የሕዝብ ነው ስለተባለ የራሱ የሆነ መስሎት ከሆነ አይደለም፡፡ የሚታለብ ላም የሚባለው እኮ አላቢው ሌላ፣ ታላቢው ሕዝብ በመሆኑ ነው፡፡ የእኔ አቋም ከመሠረቱ እስካሁንም ድረስ ይህንን ሳናደርግ መቆየታችን ለኢኮኖሚው ዘላቂ ዕድገት ጠንቅ ነው፡፡ ለኢኮኖሚው ውጤታማነት ጠንቅ ነው፡፡ የግለሰብ ሀብት የሚያድገው ምርታማነት ሲያድግ ነው፡፡ ትልልቅ የኢኮኖሚ አውታሮችን መንግሥት ይዞ ምርታማ አልሆነም ማለት እኮ፣ ኢኮኖሚው ምርታማ እንዳይሆን አደረግ ማለት ነው፡፡ የመንግሥት የልማት ድርጅት ማለት ማየት የሌለብን ነገር ነው፡፡

 

ሪፖርተር፡- እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ በሐሳብ ደረጃ ልማታዊ መንግሥት ወይም እርስዎ እንደሚገልጹት ‹‹ቢግ ፑሽ›› የሚለውን ሐሳብ ይቀበሉታል? ያምኑበታል?

 

አቶ ኤርሚያስ፡- የእኔ ሐሳብ ሳይሆን በዓለም እንደ አሜሪካ ያሉትን ጨምሮ አውሮፓና እስያ የተነሱት በዚህ አካሄድ ነው፡፡ ማመን አለማመን ሳይሆን፣ የሆነ የተደረገ ነገር ነው፡፡

 

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ክርክርዎ መንግሥት የያዛቸው የኢኮኖሚው ክፍሎች ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ናቸው የሚል ነው?

 

አቶ ኤርሚያስ፡- አዎ፡፡ ለተወሰነ ጊዜ ይዞ ከቆየ በኋላ መውጣት ይገባው ነበር፡፡ የእኔ ነጥብ ግን የግሉ ዘርፍ ሲባል አንዱ በሽታችን እኛ በራችንን ዘግተን ስንቀመጥ በዓለም  ግን መሄጃ ያጣ የገንዘብ ውቅያኖስ አለ፡፡ ኢንቨስት ተደርጎ ጥቅም ሊገኝ የሚችልበትን ቦታ እያፈላለገ ያለ ዶላርም ዩሮም አለ፡፡ ቻይና የለማችው በአገር ውስጥ ባለሀብቶች አይደለም፡፡ በውጭ ኩባንያዎች ነው፡፡ ኢትዮጵያ ገበያዋን ብትከፋፍተው በአፍሪካ ቀዳሚዋ የኢንቨስትመንት ሳቢ አገር ትሆናለች፡፡ ዘጋግተን ሞኖፖል ይዘን ቁጭ ባንል ኖሮ የውጭ የቀጥታ ኢንቨስትመንት ትልቅ ድርሻ ይኖረው ነበር፡፡ ቴሌኮም ሞኖፖል ነው፡፡ የመንግሥት መሠረተ ልማት በሙሉ በሞኖፖል ነው፡፡ ቢፈለግማ ኖሮ መንግሥት አንድም ፕሮጀክት መሥራት አይጠበቅበትም ነበር፡፡ ለአንድ ፕሮጀክት አምስት ሳንቲም ማውጣት አይጠቅበትም ነበር፡፡ ለስኳር ልማት በዓለም ላይ ትልቅ ሚና ይዘው የሚንቀሳቀሱ ትልልቅ ፋብሪካዎች አሉ፡፡ ልክ እንደ አበባው ሁሉ ኢትዮጵያ ለስኳር ተስማሚ ሁኔታዎች አሏት፡፡ ንግድ ተስማሚ፣ ለግሉ ዘርፍ ተስማሚ የሆነ፣ የፋይናንስ መሠረተ ልማት ያለው ነገር ቢዘረጋ ኖሮ የውጮቹ በሙሉ ይገቡበታል፡፡ ከአሁን በኋላም መንግሥት በትልልቅ ፕሮጀክቶች ውስጥ እጁን መክተት የለበትም፡፡ መውጣት አለበት፡፡ የግሉ ዘርፍ ሲባል ሁሌም የዘጋብን አስተሳሰብ ስላለ የኢትዮጵያ የግል ዘርፍ ካልሆነ ሌላውን እንደ ጠላት ነው የምናየው፡፡ የጣሊያን ወረራ ይመስለናል፡፡ ይህ ኋላ ቀርነት ነው፡፡ ዓለም በሙሉ ተከፍቶ እየተሳሰረ ነው፡፡ ሁሉም በተሻለ ሁኔታ ሠርቶ የተሻለ ውጤት የሚያገኝበትን የተቀረውን አንዱ ከሌላው በመነገድ ያገኛል፡፡ ራሳችንን ለመዝጋትና ለመቆላለፍ የሚቻለንን ሁሉ አድርገናል፡፡ ወደ ግል ይዛወራሉ የተባሉት ድርጅቶችም ላይ ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች የሚል ነገር ሰምተናል፡፡ ቆም ብለን ማሰብ አለብን፡፡ የኢትዮጵያ የግል ዘርፍ በጣም አዋጭ በሆነው የባንክ አክሲዮን ግዥ ውስጥ ነው አብዛኛው ሰው የሚሳተፈው፡፡ 50 ብርም 100 ሺሕ ብርም ይኑረው የባንክ አክሲዮን በመግዛት 30 ብርም፣ 40 በመቶ ትርፍ ማግኘት እንደሚችል ነው የሚያስበው፡፡ እውነቱን ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ኢንቨስትመንት የት ይገኛል? ኢትዮ ቴሌኮም ወደ ግል ከተዛወረ በኋላ በዓመት 30 እና 40 በመቶ ትርፍ እንደማይከፍል ማወቅ አለብን፡፡ ለምን ቢባል የሚሸጥበት ዋጋ የገበያ ዋጋ ስለሆነ በእንደዚህ ዓይነት ትርፍ ታስቦ የንብረትና የሀብት ግመታው ከትርፉ አኳያ አይሠራም፡፡ የሆነ ኢንቨስተር 100 ሺሕ ዶላር ወይም ሌላ የገንዘብ መጠን ኢንቨስት ቢያደርግ፣ በዓመት 30 ሺሕ ብር ወይም 40 ሺሕ ብር ትርፍ ሊያገኝ ነው፡፡ ቴሌ ላይ ኢንቨስት ያደረገ ግን በዓመት 10 ሺሕ ብር ላያገኝ ይችላል፡፡ ለውጭ ኢንቨስተር ግን ይኼ ትልቅ ገንዘብ ስለሆነ በጣም ያስደስተዋል፡፡ በመሆኑም በብዛት ሊመጣ ይችላል፡፡ አሥራ ስድስቱ የግል ባንኮች በ20 ዓመታት ውስጥ አክሲዮን በመሸጥ የሰበሰቡት ካፒታል አሥር ቢሊዮን ብር ነው፡፡ በዶላር ሲመነዘር 300 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ብዙ ባንኮች አክሲዮኖቻቸውን መሸጥ እየፈለጉ መሸጥ አልቻሉም፡፡ ገዥ የለም፡፡ ባለአክሲዮኖቹ በቅቷቸዋል፡፡ ካፒታላችሁን አሳድጉ ስለተባሉ፣ ባንኮች በአሻሻጭ ወኪሎቻቸው በኩል አክሲዮን ግዙን እያሉ እየዞሩ ነው፡፡ መሸጥ የፈለጉት ያህል ግን መሸጥ አልቻሉም፡፡ 500 ሚሊዮን ብር የአክሲዮን ካፒታል ለመሰብሰብ ተነስቶ 50 ሚሊዮን ብር ላይ ቆሞ ጭቅጭቅ ውስጥ የገባ ስንት አለ? እኔ ራሴም ይህ ዕጣ ገጥሞኛል፡፡

 

ስለዚህ ከቁጥሮቹ አንፃር ለኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ እንሽጥ የሚል ሰው ስለአገሪቱ የግል ዘርፍ አቅም ግንዛቤ የሌለው ነው፡፡ ሌሎቹም ወደ ግል ተዛውረው አምስት ወይም ሰባት ወይም አሥር ቢሊዮን ዶላር ማግኘት እንፈልጋለን፡፡ ይህ በአገር ውስጥ ባለሀብት ሊሆን አይችልም፡፡ በአሜሪካ ኒውዮርክ ዎል ስትሪት ውስጥ ለረዥም ጊዜ ሠርቻለሁ፡፡ እንደ ጉግል ወይም ፌስቡክና ሌላው ኩባንያ ከሚሸጡት የአክሲዮን ድርሻ ውስጥ ግለሰቦች ሲገዙ የሚሸጥላቸው ድርሻ ከ10 እስከ 20 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ሌላውን የሚገዙት ግን ተቋማት ናቸው፡፡ እነዚህ ኢንቨስተሮች ደግሞ የፋይናንስ መሠረተ ልማት ሲፈጠር አብረው የሚመጡና የሚፈጠሩ ናቸው፡፡ ብሔራዊ ባንክ የግል አክሲዮኖችን ይገዛ ነበር፡፡ ይኼ አሁን የለም፡፡ እኔ የማላውቀው ነገር ከሌለ በስተቀር በፋይናንስ መስኩ የውጭ ባለሀብት አይግባ እየተባለ ለእኛ አገር ባለሀብቶች የሚሰጠው ሽፋን ሁለት ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክ የመቆጣጠር አቅም የለኝም ይላል፡፡ ከ27 ዓመታት በኋላ እንዴት አሁንም አቅም የለም እንደሚባል አላውቅም፡፡ አክሲዮን ገበያ ለምን አይኖርም ሲባል የመቆጣጠር አቅም የለም ስለሚባል ነው፡፡ ኢትዮጵያ ትልቅ ገበያ ነች፡፡ ከ40 ዓመታት በኋላ 200 ሚሊዮን የሚደርስ የሕዝብ ብዛት ይኖረናል፡፡ በዓለም ላይ ከአሥር ትልልቅ የሕዝብ ቁጥር ካላቸው አገሮች ውስጥ እንገኛለን፡፡ በአፍሪካም ትልቅና እያደገች ያለች፣ የአፍሪካ ትንሿ ቻይና የምትባል አገር አለችን፡፡ ይህንን የሚያህል አገር ውስጥ፣ እያደገ ያለ አገር ውስጥ ግን ተወዳዳሪዎች የሉም፡፡ ስቶክ ገበያ የለንም፡፡ የውጭ ባንኮች ባለመኖራቸው የውጭ ኢንቨስተሮች ለመምጣት ይቸገራሉ፡፡ ሲመጡም ያሉት ባንኮች በቅጡ አያናግሯቸውም፡፡ መረጃም እንደ ልብ አይገኝም፡፡ እኛ ስናወጣው የነበረውን መረጃ ሁሉም ይሻማበት ነበር፡፡ መንግሥት ራሱ ይጠቀምበት ነበር፡፡ ትልቅ ዕድል ዓይተው ቢመጡም አባጣ ጎርባጣው ያስቸግራቸዋል፡፡ እየጎመጁ መጥተው በቢሮክራሲውና በሌላውም ጣጣ ምክንያት ይቀራሉ፡፡ በተፈጠሩት ችግሮችና ሚዛናቸውን በሳቱ አካሄዶች የተነሳ ሁሉም ነገር ተዘጋግቷል፡፡ መረጃ እንደ ልብ በማያገኙበት አገር ውስጥ ቀርቶ አሜሪካ በተፈጠረው የፋይናንስ ቀውስ እንኳ የዓለም ባንክና የዓለም ገንዘብ ድርጅትም ግራ ተጋብተው ነበር፡፡ እኛ ግን የማይሳሳቱ ይመስለናል፡፡ ይሳሳታሉ፡፡ መሬት ላይ የሚታይ ምናልባትም ከዓመት በኋላ በይፋ የሚወጣ መረጃ የሚያረጋግጠው ብዙ ችግር አለ፡፡

 

ጽሑፉን ስጽፈው ‹‹ኮድ ብሉ›› ነበር ያልኩት፡፡ ይህም ማለት አንድ አደጋ የደረሰበት ሕመምተኛ ልቡ መምታት አቁሞ ድንገተኛ ክፍል እየገፉ እያስገቡት ሰማያዊ መብራት አብርተው ሲጣደፉ፣ ሰው ሁሉ መንገዱን እየለቀቀላቸው በፍጥነት አስገብተው ልቡ ላይ የአሌክትሪክ ንዝረት ይለቁበታል፡፡ የእኛ ኢኮኖሚም ልቡ እየቆመ ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ችግር እያቆመው ነው፡፡ ለአገር ውስጥ ባለሀብት ለውጭ ይሰጥ እያለ ሐሳብ የሚሰጥ ሰው፣ ምን ዓይነት አደጋ ውስጥ እንዳለን ስለማያውቅ ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ችግር የኢኮኖሚያችን የህልውና ጥያቄ ነው፡፡ አሁን ብድር የሚሰጠን የለም፡፡ ቻይናውያን እንኳ እያቆሙ ነው፡፡ የሚሰጠን እንኳ ብናገኝ የማንወጣበት ጉድጓድ ውስጥ ነው የምንቆፍረው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ያስፈልገናል ግን ደግሞ መበደር አንችልም፡፡ እኛ ዘንድ መሆን የማይገባው አገር የሚጎዳ ንብረት ተቀምጧል፡፡ መሸጥ እያለበት ያልተሸጠ ነገር አለ፡፡ በጽሑፌ ‹‹ፕራይቬታይዜሽን ማጂክ ቡሌት›› ብዬ ነው ያስቀመጥኩት፡፡ በርካታ አገሮች ተተኩሰዋል፡፡ ማጂክ ቡሌት የላቸውም፡፡ እኛን ግን ጥሎን አልፏል፡፡ ሆኖም በሌላ አፍሪካ አገር እንኳ የሌለ ለችግር ጊዜ መውጫ የሚሆነን ተቀማጭ ይዘን ተገኝተናል፡፡ መሸጥ አለብን፡፡ የአገር ውስጥ ይግዛው የውጭም ይግዛው መሸጥ አለብን፡፡ የውጭ ሰው ዘመድ ነው፡፡ ጠላት አይደለም፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ የጋራ ማኅበሰረብን እኛ ነበርን መምራት የነበረብን፡፡ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ኬንያና ታንዛንያ ናቸው የመሠረቱት፡፡ እነዚህን ጨፍልቀህ እኛን አታወጣም፡፡ ግን ደግሞ ጥለውን ሄደዋል፡፡ እነሱን ልንከተል ነው፡፡ የዕይታ ችግር አለብን፡፡ ማንነታችን አልገነባንም፡፡ ምናልባት አሁን እየተገለጽልን ነው፡፡ አይኤምኤፍ ዶላር ሰጠን አልሰጠን፣ ደረታችንን ነፍተን አሁን ያሉትን ብቻም ሳይሆን ካስፈለገንም ሌላ ተጨማሪ ፕሮጀክት የምናስኬድበት ኢንቨስትመንት ማምጣት ይቻላል፡፡ አሁን ኢኮሚሚው የ80 ቢሊዮን ዶላር አቅም አለው፡፡ የኢኮኖሚው ዕድገት እንዲቀጥል በየዓመቱ የዚህን የ25 በመቶ ኢንቨስት እናድርግ ብንል እንኳ 25 እና 26 ቢሊዮን ዶላር በየዓመቱ ያስፈልገናል፡፡ ይኼ ገንዘብ ከየት ይመጣል? ኢንቨስትመንት ሲቆም ደግሞ ኢኮኖሚው ማደጉን ያቆማል፡፡

 

በሌላ በኩል ደግሞ ትልቅ ሀብት እጃችን ውስጥ አለ፡፡ ስለዚህ ይህንን ሀብት ወደ ግል ማዛወር ይኖርብናል፡፡ ጥሩ ገንዘብ የሚከፍልና ሥራውን ቀጥ አድርጎ የሚያስኬድ እስኪመጣ ድረስ፣ የአገር ውስጥ የውጭ እያልን መነታረክ አያስፈልገንም፡፡ ድሆች ነን፡፡ ብር ሳይሆን ዶላር ነው የምንፈልገው፡፡ እንደ መርህ ካየነውም የአገር ውስጥ ገንዘብ ለቴሌኮም መግዣ መዋል የለበትም፡፡ ምንም የሚጨምረው ነገር የለም፡፡ ዶላር ግን ያስፈልገናል፡፡ የአገር ውስጥ ባለሀብት ገንዘቡን ባንክና ኢንሹራንስ ውስጥ ጨርሷል፡፡ ባለሀብት የምንለው ሁሉ ባለዕዳ ነው፡፡ ከባንክ ውጪ ያለው ባለሀብት ከውጭ ሁሉን ነገር እያስመጣ 30 እና 40 በመቶ ያተርፋል፡፡ የራሱን ገንዘብ አገላብጦና ተቆጣጥሮ እየሠራ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በዓመት አሥር በመቶ ትርፍ ወደሚያገኝ ድርጅት ብርህን አምጣና አክሲዮን ግዛ ብትለው ለምን ብሎ ያመጣል? ስለዚህ የአገር ውስጥ፣ የውጭ ይግዛ ማለት የለብንም፡፡ ከፈለግክ ግዛ መባሉ ጥሩ ነው፡፡ ግን የውጮቹ ናቸው የሚገዙት፡፡ ውጤቱን ታዩታላችሁ፡፡ እነሱ ቢገዙ ነው ጥሩ የሚሆነው፡፡ ድሮ እኮ ጣሊያን ሠፈር፣ ግሪክ ሠፈር የሚባሉ አካባቢዎች እኮ ዓለም አቀፍ ከተማ እንዲኖረን ያስቻሉ ነበሩ፡፡ ተጋብተው ተዋልደው ይኖሩ ነበር፡፡ ችግር አልተፈጠረም፡፡ ሆኖም ሥነ ልቦናችን በመበላሸቱ ይመስለኛል ችግር የሚታየው፡፡

 

ሪፖርተር፡- በጽሑፉ ውስጥ በርካታ የኢኮኖሚ ስትራቴጂዎች በርዕዮተ ዓለም ምክንያት እጃቸው እንደሚጠመዘዝ አሥፍረዋል፡፡ ኢሕአዴግ ደርግ ይመራው የነበረውን ኢኮኖሚ ሲረከብ ወና ሆኖ ነው ያገኘው፡፡ በዚህ ምክንያት ትልቅ ግፊት በማድረግ ኢኮኖሚውን ማስነሳት ነበረበት ብለዋል፡፡ አሁን ለሚታየው ችግር ግፊቱ ያለወቅቱ የመጣ በመሆኑ የተፈጠረ ችግር ነው ሊባል ይችላል?

 

አቶ ኤርሚያስ፡- አይደለም፡፡ መንግሥት ወላጅ ነው እንበል፡፡ የግሉ ዘርፍ ልጅ እንደሆነ እናስብ፡፡ ልጅ ተወልዶ ጡት ካልጠባ ቀጭጮ ይቀራል፡፡ በተለይም ሳይንሱ እንደሚለው እስከ አምስት ዓመቱ ባለው ጊዜ ውስጥ የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት አለበት፡፡ ከዚያ ደግሞ ማስተማር ይጠበቅብሃል፡፡ ለግሉ ዘርፍ ይህን ሁሉ ሳታደርግ ስትገርፍና ስትቀጠቅጠው ቆይተህ፣ መልሰህ ደግሞ በል እንግዲህ ተነስ እንዴት ትለዋለህ? መንግሥት ታላቁን ግፊት ሲከተል ምናልባት ስትራቴጂውን ሲቀይሰው በርዕዮተ ዓለም ምክንያት የግሉ ዘርፍ አይረባም ከሚል መነሻ መጥፎ አመለካከት ነበረው፡፡ ይህ መጥፎ አመለካከት እንዲሁ ከመሬት አልመጣም፡፡ ደርግ የፈጠራቸው የግሉ ዘርፍ ተዋንያን ምን ዓይነት ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ ካልን ኢመደበኛ በሆነ አካሄድ፣ በጨለማ ውስጥ በድብቅ የሚሠሩ ናቸው፡፡ አንድ ሰው የገቢ ንግድ ፈቃድ ስለወጣ ብቻ ሚሊየነር ነው ይባላል፡፡ ብር ሳይኖረው ፈቃድ በማውጣቱ ብቻ እከሌ እኮ ሀብታም ሆነ፣ አለፈለት ተብሎ ይደገሳል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ሲፈቀድ አንድ ዶላር በአሥር ብር እየገዛ ብዙ ሥራ መሥራት ይቻላል፡፡ ኮንትሮባንድና ሌላውም ሥራ ይጧጧፋል፡፡ ደርግ ወድቆ ኢሕአዴግ ሲገባ የነበረው የግል ዘርፍ በእንዲህ ያለ ሁኔታ ሲንቀሳቀስ የነበረ ነው፡፡ እንዲያውም ኢኮኖሚው ሲከፈትለት ተንፈስ አለ፡፡ ያኔ መንግሥት ዓይቶ የሚረባ የግል ዘርፍ በማጣቱ ራሴ እሄድበታለሁ ያስባለው ችግር ይኼ ነው፡፡ የግሉ ዘርፍ እንደ ጠላት የታየው በዚህ ምክንያት ቢሆንም ሁሉንም ጨፍልቆ ማየት አይገባም ነበር፡፡ ሌላው የሶሻሊስታዊ አስተሳሰቡ ገና አልረገበም ነበር፡፡ ከዚህ ሌላ ግን እስካሁንም ያለው ኢሕአዴግ የመቆጣጠር አባዜ ያልለቀቀው መሆኑ ነው፡፡ የፖለቲካው አካል፣ የፓርቲው አካል ያልሆኑ ሰዎች ማደግና መጠንከር እንደ ፖለቲካ ሥጋት ይታይ ስለነበር፣ ይህ ሁሉ ተደማምሮ የግሉ ዘርፍ ዜሮ ገባ፡፡ የግሉ ዘርፍ ውጤታማ ያልሆነው በሳይንሱ ስህተት ሳይሆን የአገሪቱ አመራር ያለ ግሉ ዘርፍ ኢኮኖሚውን እኔው ራሴ እመራዋለሁ ብሎ በመነሳቱ የፈጠረው ችግር ነው፡፡ ስኬታማ ቢሆን ኖሮ ባልተወቀሰም ነበር፡፡ ነገር ግን ስኬታማ እንደማይሆን ሲጀመርም ያስታውቅ ነበር፡፡

 

አንዱ የልማታዊ መንግሥት ትልቁ መጠይቅና ሰዎችም ብዙ ጊዜ የማያተኩሩበት ነገር ቢኖር ወደ ፍፁም የበላይነት የሚጠጋ፣ ጠንካራ የፖለቲካ አመራር ጠባይ እንዳለው ነው፡፡ አውሮፓ ተቀጥቅጦ ሲነሳ ታላቅ ግፊት አስፈልጎት ነበር፡፡ ነገር ግን ዴሞክራሲያዊ ማኅበሰረሰብ ነበር፡፡ ጃፓንም እንደዚያው፡፡ የእኛ ግን እንደ እነሱ አልነበረም፡፡ ልማታዊው መንግሥት አገሪቱን ወደሚፈልገው መንገድ እያስገባና መስመር እያስያዘ የመውሰድ ባህሪ አለው፡፡ ያየነው ልምድ ይኼው ነው፡፡ ዓለም ላይ የታው ልምድ ይኼ ነው፡፡ ነገር ግን ብቃት መኖር አለበት፡፡ አንድ ፋብሪካ ለማስተዳደር ብቃት ያስፈልጋል፡፡ አምራች ዘርፉን ራሴው እያመረትኩ እመራለሁ ስትል እኮ የአመራር፣ የስትራቴጂና የቢዝነስ፣ ወዘተ. ብቃት ሊኖርህ ይገባል፡፡ ይህንን ብቃት ለማግኘት የውጭ መንግሥታትም ይፈተናሉ፡፡ ከምንም የሚነሱ የመንግሥት ኃላፊዎች በእንዲህ ያለው አካሄድ ለመሄድ ሲነሱ ፈተና ይጠብቃቸዋል፡፡ ስለዚህ ቁጭ ብለን ሒሳቡን ስንሠራው የማይሆን አካሄድ ነበር፡፡ የዚያ ሁሉ ድምር አሁን ላይ አደረሰን፡፡ መግባት በማይገባው ዘርፍ ውስጥ ደፍሮና ብድር ስላገኘም ጭምር የገባው መንግሥት ተውጦ ቀረ፡፡ ኢንቨስት የተደረገው ገንዘብ በብዙ ቢሊዮኖች ዶላሮች ቢሆንም፣ አብዛኞቹ ፕሮጀክቶች ግን ወይ ቆመዋል፣ ወይ ደግሞ ሀብት እያጠፉ ነው፡፡ እየተዘረፉ ነው፡፡ ተዘርፈውም ሥራው ቢሠራ አንድ ነገር ነበር፡፡ ኪሳራ ብቻ ነው፡፡ ከተማውን ዞረህ ብታይ አብዛኛው የፎቅ ግንባታ እየቆመ ነው፡፡ ከስንት አንድ ነው ሲሠራ የምታየው፡፡ ብር አልነበረንም፡፡ ግን ብዙ ተበድረን አምጥተን በተንነው፡፡ የፈሰሰውን ሀብት በቶሎ ውጤት እንዲያስገኝ መሥራት አለብን፡፡ መቆም አንችልም፡፡

 

አንድ ወር ባለፈ ቁጥር ስንት ፋብሪካ እንደሚዘጋ አላውቅም፡፡ ግንባታው እስከ 85 በመቶ በሚገመት ደረጃ ቆሟል፡፡ ይህ ማለት ስንት መቶ ሺሕ ሠራተኛ ሥራ እንደሚፈታ ማሰብ ይገባል፡፡ ያጠራቀመው ገንዘብ ስሌለው የቤት ኪራይ የሚከፍለውና የሚበላው እያጣ ነው፡፡ ተቋራጭ ከስሯል፡፡ ማሽነሪ ያከራየ ከስሯል፡፡ ባንኮችም እንዴት እንደሆነ አላውቅም እንጂ መክሰር ነበረባቸው፡፡ የትኛው ተበዳሪ ነው ብድሩን የሚከፍለው? ፋብሪካ ከተዘጋና ሠራተኛ ከተበተነ በኋላ ሐራጅ ቢወጣበት አሁን ማን ነው የሚገዛው? ኢኮኖሚው የሚገኝበትን ደረጃ መረዳት አለብን፡፡ ሕዝብ መጠየቅ አለበት፡፡ ለምንድን ነው የኮንዶሚኒየም ቤቶች የቆሙት? ለምንድን ነው የስኳር ሕሙማን መድኃኒት ያጡት? ለምንድን ነው ዳቦ ሦስት ብር፣ እንቁላል ስድስት ብር የገባው? ብሎ ሕዝቡ መንግሥትን በመጠየቅ ኢኮኖሚውን በቶሎ እንዲያክመው መወትወት አለበት፡፡ በእንግሊዝኛ አንድ አባባል አለ፡፡ ‹‹ቤገርስ ካንት ቢ ቹዘርስ›› ይባላል፡፡ ካልበላህ ትሞታለህ፡፡ አልጫ አልወድም ዶሮ ወጥ ስጡኝ አትልም፡፡ ሽሮ አልወድም አትልም፡፡ ያገኘኸውን ትበላለህ፡፡ ትንሽ ጨፍገግ ያለ ሊመስል ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህንን የሚያነብ ሰው የራሱን ሕይወት ዞር ብሎ ሲያየው ሊገነዘበው የሚችለው ነገር ነው፡፡ አንድ ሰው ለመታመሙ ትልቁ ምልክት ራስ ምታት እንደሆነው ሁሉ፣ የአንድ ኢኮኖሚ መታመሙ ትልቁ ምልክትም የዋጋ ግሽበት ነው፡፡ ግሽበቱ እየነደደ ነው፡፡ ግሽበቱ በገጠርና በከተማ ያለው ጫና የተለያየ ነው፡፡ በገጠሩ ዝናብ እየነዘበ በመሆኑ የተሻለ ነገር ሊኖር ይችላል፡፡ ምርት አለ፡፡ ዋጋ ጨምሯል፡፡ አርብቶ አደሩ ግን ሌላ ጫፍ ላይ ነው ያለው፡፡ በድጋፍ ነው የሚኖረው፡፡ ከተማ የሚኖረው 20 ሚሊዮን ሕዝብ ግን እየተለበለበ ነው፡፡ እንደ ምንም ተሟሙቶ በቀን ሁለቴም እየበላ ሊጣጣር ይችላል፡፡ አዲስ አበባ ያለው የቤት ኪራይ ዋጋ ከባድ በመሆኑ አንዳንዶች ላስቲክ ቤት ውስጥ ለመኖር እየተገደዱ ነው፡፡ ኢኮኖሚያችን እዚህ ላይ ነው ያለው፡፡ እየራበን የምንፎክረው ነገር አለ፡፡ ይኼ መቆም አለበት፡፡ ደሃ ሆነን በባዶ ሆዳችን ስለትልቅነታችን ከመፎከር ይልቅ በተግባር ማሳየት አለብን፡፡ የዚህ ሁሉ መድኃኒቱ ፕራይቬታይዜሽን ስለመሆኑ የሚያነጋግር ነገር አይደለም፡፡

 

ሪፖርተር፡- የልማታዊ መንግሥት አካሄድ ካመጣቸው መልካም ነገሮች መካከል እንደ መንገድ፣ ባቡር፣ ወዘተ. ያሉትን መሠረተ ልማቶች ማስፋፋቱ እንደሆነ በጽሑፍዎ ጠቅሰዋል፡፡ ጥራት ላይ በተለይም በፋይናንስ ረገድ ትልቅ ችግር እንደሚታይ አሥፍረዋል፡፡ ይህ ጉዳይ እንዴት እንደሆነ ቢያብራሩ?

 

አቶ ኤርሚያስ፡- ታስቦና ታቅዶ የሆነ ጉዳይ ነው፡፡ በጽሑፉ ውስጥ ስለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የሚጠቅስ አንድ ክፍል አለ፡፡ ይኸውም ልማታዊ መንግሥት በፋይናንስ ዘርፉ ላይ ስላለው አቋም ግልጽ በሆነ ቋንቋ የተቀመጠ ነው፡፡ አንድ አገር ውሱን አቅም ሊኖራት ይችላል፡፡ የአገሪቱን ኢኮኖሚ የሚመራው መንግሥት ለወደፊቱ የአገሪቱ ዕድገት የሚበጀው መንገድ የትኛው ነው? መንገዱን ፋይናንስ ለማድረግም የአገሪቱን የኢንቨስትመንት ሀብት እንዴት ላሰማራው? ማን ይሰማራ? ማለት መቻል አለበት፡፡ ለዚህ ሁለት አካሄድ አለው፡፡ አንደኛው የሚታይ የመሠረተ ልማት ወይም ‹‹ሀርድ ኢንፍራስትራክቸር›› የሚባለው ግንባታ ነው፡፡ ይህንን በሰው የአካል ክፍል ምሳሌነት ላስረዳ፡፡ የሚታየው መሠረተ ልማት ማለት የአካላችን አጥንት እንደ ማለት ነው፡፡ ከላይ እስከ ታች ያለውን ሰውነታችንን የሚሸከመው አጥንታችን ማለት መንገድ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ ውኃ፣ ወዘተ. ያሉት ናቸው፡፡ ይህንን ካደረግን በኋላ ግን የሰውነታችን ጡንቻ ማለትም የተማረና ጤነኛ የሰው ኃይል ሲፈጠር፣ ትክክለኛ የንግድ ሥርዓት፣ የፍትሕ ሥርዓት፣ የአስተዳደር ሥርዓትና ሌሎችም የዕለት ተዕለት ኑሯችንን የሚመለከቱት መሠረተ ልማቶች ‹‹ሶፍት ኢንፍራስትራክቸር›› ይባላሉ፡፡ ከአጥንት ጋር የተጣመረ የፈረጠመ ሰውነት ቢኖርህም መንቀሳቀስ ግን አልቻለም፡፡ ሕይወት የለውም፡፡ ኦክሲጅንም የተመጣጠነ ምግብም ማግኘት አልቻለም፡፡ ይህንን ማግኘት የሚችለው የደም ሥሩና ልቡ ሥርዓተ መዘውራቸውን ሲያከናውኑ ነው፡፡ ሦስት መሠረቶች ያስፈልጉናል፡፡ ሶፍት፣ ሐርድ እንዲሁም የፋይናንስ መሠረተ ልማት አውታሮች ያስፈልጋሉ፡፡ አንዱ ከሌለ ውጤታማ መሆን አይቻልም፡፡ ሁለተኛ አማራጭ ሳይንሱም የማይደግፈው፣ በታሪክም ውጤታማ ያልሆነው ይብሱንም ብቃት በሌለው ኢኮኖሚ ውስጥ መንግሥት እኔው ቁጠባ እሰባስባለሁ፣ እኔው አሰራጨዋለሁ፣ ወዘተ. ማለቱ ነው፡፡ በመሆኑም ባንኮች ብዙም አቅም ኖሯቸው ቁጠባ ሰብስበው ብድር እንዳይሰጡ፣ ከእያንዳንዱ ብድራቸው 27 በመቶ እየተወሰደ ወደ ብሔራዊ ባንክ ይገባል፡፡ ከዚህ በላይ ብድር እንዳይሰጡ ተቆላልፈዋል፡፡ ይህንን ገንዘብ መንግሥት ወሰደው፡፡ ውጤታማ ቢሆንበት ግን ችግር አልነበረውም፡፡ ግን አልሆነም፡፡ ይህ አካሄድ እንደ ስትራቴጂ ተመረጠ፡፡ ስትራቴጂው ግን ስህተት ነበር፡፡ እዚህ ለደረስንበት ደረጃ ያበቃንም ይኸው ነው፡፡ በጽሑፍ የተቀመጠና ፖሊሲያችን ይህ ነው ተብሎ የሠፈረ ነው፡፡

 

ሪፖርተር፡- ‹ዓይናችን እያየ ፋይናንስ የሌለው ዕቅድ አዘጋጀን› በማለት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን በተመለከተ በጽሑፍዎ አሥፍረዋል፡፡ የመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ሲዘጋጅ የተለጠጠ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ይነሳ ነበር፡፡ ትልልቅ ፕሮጀክቶች እንዲገነቡ የታቀዱበት ከመሆኑ አኳያ ምን ያህል ዋጋ አስከፍሏል ይላሉ?

 

አቶ ኤርሚያስ፡- እውነቱን ለመናገር የምለው አላጣም፡፡ እዚህ ላይ ግን የምለውን አጣለሁ፡፡ በምን ዓይነት አመክንዮ ለማስረዳት ይቸግረኛል፡፡ እያወቁ ማጥፋት ነው፡፡ በሌላ በኩል እንደ ቀልድ እንጥቀሰው ከተባለ ‹ጉረኛ ጣሊያን ፎርሳ እያለ ይሞታል› ይባላል፡፡ በወኔ ኢኮኖሚ አይንቀሳቀስም፡፡ በወኔ ወደ ጦርነት መግባት ይቻል ይሆናል፡፡ እሱም ቢሆን ግን ተደራጅተህ ነው እንጂ በባዶ ወኔ ደረትህን ነፍተህ አትገባበትም፡፡ በቴሌቪዥን ያየሁት ነገር በጣም እያሳዘነኘኝ ነው፡፡ ሕዝቡ ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ገንዘብ እያዋጣ ነው፡፡ በሌላ በኩል ኢትዮጵያን በሚያህል አገር ውስጥ ስንዴ፣ ስኳር፣ መድኃኒትና ሌላውም ነገር የለም፡፡ ወጣቱ ወጥቶ ረበሸ፣ አቃጠለ፡፡ የከተማው ሰው መኖር እያቃተው ነው፡፡ ከተሜውን ማስራብ ከባድ ነው፡፡ የእኛ አገር አብዛኛው ሰው ወጣት ነው፡፡ ሌላው ዓለም እንዴት እንደሚኖር ያያል፡፡ ከዚያም የራሱን ሕይወት ያያል፡፡ በእኛ አገር ያየነው ቀውስ ጥቂቷን ቅምሻ ነው፡፡ የዓረብ አብዮት መነሻው የአንድ ወጣት የኑሮ ሁኔታ አሟሟት ነው፡፡ ራሱ ላይ የለኮሰው እሳት የዓረቡን ዓለም አቀጣጥሎታል፡፡ ሰሞኑን ዮርዳኖስ ውስጥ የተከሰተው ተቃውሞ የተዳፈነው፣ የተረጋጋው መንግሥት በገጠመው የኢኮኖሚ ችግር ሳቢያ ሊከሰት የነበረውን ቀውስ እነ ሳዑዲ ዓረቢያ ተረባርበው ሦስት ቢሊዮን ዶላር እንደሚሰጡ ቃል በመግባታቸው ነው፡፡ በነደደው አካባቢ ውስጥ ቤንዚን አታርከፈክፍም፡፡ ለእነዚህ የተመቻቸ ነገር እንዳለ እኛ ዘንድ እያየን ነው፡፡ በመሆኑም በፕራይቬታይዜሽኑ ሒደት አካሄዳችንን ቀይረን፣ የውጭ ምንዛሪ ማመንጨት ካልቻልን ከአምስት ወይም ከስድስት ዓመታት በኋላ የማንወጣበት ችግር ውስጥ እንገባለን፡፡ ከፕራይቬታይዜሽኑ እኩል መደረግ ያለባቸው ነገሮች አሉ፡፡ ኢኮኖሚው ውስጥ ያለው የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ሚዛን መስተካከል አለበት፡፡ የልማታዊ መንግሥት የኢኮኖሚ መጨረሻው ሄዶ ሄዶ ራሱን ማጥፋትና ለግሉ ዘርፍ ቦታውን መልቀቅ ነው፡፡ መንግሥት ወደ ኋላ በማፈግፈግ ኢኮኖሚው እንዲታከም ማድረግ አለበት፡፡ ብዙ ዕዳ አለብን፡፡ ጠጨማሪ ብድር የሚሰጠን የለም፡፡ ካገኘኋቸው ግርድፍ ቁጥሮች በመነሳት የሠራሁት ግመታ እንደሚያሳየው ኢትዮ ቴሌኮም ብቻውን እስከ 20 ቢሊዮን ዶላር ያወጣል፡፡ ትልቁን ድርሻ መንግሥት ይዞ አነስተኛውን ድርሻ ለግሉ ዘርፍ እንሽጥ የሚለው ነገር፣ አብዛኛውን ድርሻ መሸጥ ለብዙ ሰው አገር እንደ መሸጥ እየመሰለው ነው፡፡

 

ሪፖርተር፡- ፕራይቬታይዜሽንን በሚመለከት ያስቀመጧቸው አኃዞች አሉ፡፡ በመጀመርያው ዓመትና በተከታታይ ባሉት ጊዜያት ምን ያህል የውጭ ምንዛሪ ገቢ ሊገኝ እንደሚቻል ካስመጧቸው ነጥቦች አኳያ፣ ሒደቱን እንዴት ማስተዳደር እንደሚቻል ይነግሩናል?

 

አቶ ኤርሚያስ፡- የውጭ ምንዛሪ በማጣት የደም ዝውውራችን ላይ ችግር ተፈጥሮ ከፍተኛ ኮማ ውስጥ ገብተናል፡፡ ስለረዥሙ ልማታችን ከማሰባችን በፊት ከሞት አልጋችን መነሳት አለብን፡፡ ከብድር ሳይሆን ከራስህ ሀብት የውጭ ምንዛሪ ወደ ኢኮኖሚው ማስገባት አለብህ፡፡ ነገር ግን እንደ በፊቱ ይኼኛውም ችግር ውስጥ እንዳይገባ ቁልፍልፍ ያደረግነውን ቁጥጥር ማሻሻል አለብን፡፡ የውጭ ምንዛሪ በየትኛውም መንግሥት ውስጥ እንደሚታየው አየር የመጨበጥ ያህል ነው፡፡ ገንዘብ ነው፡፡ ሰው በየትኛውም መንገድ ያወጣል፡፡ ቁጥጥሩ አይሠራም፡፡ የገንዘብ ሥርዓቱ ሳይቀየር ከፕራይቬታይዜሽን የሚገኘው ገንዘብ ወደ ሥርዓቱ ገባ ማለት መልሰን እዚያው ችግር ውስጥ ልንኳትን ነው ማለት ነው፡፡ ከባድ ካንሰር ውስጥ ስላለን አድቪልም ስለማያስታግሰን ትንሽ ሞርፊን እንደ መውሰድ ነው፡፡ አንደኛው ዕርምጃ ልቡ መምታት ያቆመውን ኢኮኖሚ ልቡ እንዲነሳ ማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ልቡ ከተነሳ በኋላ ደም ሥሩ ተደፋፍኖ ባለበት ሌላ የልብ ሕመም ከሚመታው፣ የተዘጋጋውን ደም ሥሩን ከፋፍተው፡፡ የቆላለፍከውን ከፋፍተው፡፡ የውጭ ምንዛሪ የሚፈልግ ካለ ይውሰድ በል፡፡ ገንዘብ እንደ ማንኛውም ዕቃ ዋጋ አለው፡፡ ዋጋውንም ገበያው ይተምነዋል፡፡ ዋጋውን ገበያ ተመነው ማለት ሚዛን አለው፣ ዘላቂ ሆኖ ይቀጥላል ማለት ነው፡፡ አንተ ግን እወዳደራለሁ ብለህ አጉል ስትዘጋው፣ ገበያው በጎን በኩል የራሱን ገበያ ይፈጥራል፡፡ ጥቁር ገበያው ይስፋፋል፡፡ በጥቁር ገበያው ከአሥር በመቶ የማይበልጠው፣ አሁን ቀውሱ ከመጣ በኋላ ግን ልዩነቱ እስከ 25 እና 30 በመቶ ደርሷል፡፡ በቬንዙዌላና ከዚህ ቀደምም በዚምባብዌ እንደታየው እንዳይሆን ለወደፊቱ ያሠጋል፡፡ ገበያውን እንቆጣጠራለን ብለው ባመጡት ጣጣ፣ ሕዝቡ ዳቦ ለመግዛት ገንዘብ በከረጢት ሙሉ እያየዘ ለመሠለፍ ተገዷል፡፡

 

የውጭ ምንዛሪና የኢኮኖሚ ሥርዓታችን ሚዛን አብሮ ከተስተካከለ የወደፊቱ ጉዟችን ከእስካሁኑ ጠንካራ መሆን ይችላል፡፡ የሚያስፈልጉት ሪፎርሞች የመጀመርያው ገንዘብ በፕራይቬታይዜሽን ማስገባት ነው፡፡ ችግሩን ያመጣብን የገንዘብ ግብይት ሥርዓቱ በመሆኑ እንደ ኬንያና ኡጋንዳ መከፈት አለበት፡፡ ይህንን ለማድረግ በኢኮኖሚው ውስጥ ምን ያህል ገንዘብ ሊወሰድ ይችላል ብለህ ሥሌቱን ትሠራለህ፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ስንት ብር ኖሮት ስንት ዶላር ሊገዛ ይችላል የሚለውን መሥራት ነው፡፡ በተሠራው የፋይናንስ ትንበያ መሠረት በመጀመርያው ዓመት ግፋ ቢል አራት ቢሊዮን ዶላር ሊወጣ እንደሚችል ተገምቷል፡፡ በሁለተኛው ዓመት ድንገት ሊወጣ ይችላል ተብሎ የሚገመተው ሁለት ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ የገበያ ሥርዓቱን ከለቀቅኸውና ካመቻቸኸው ምንዛሪው ሊወጣም ሊወርድም ቢችል፣ በገበያው ስለሚመራ ሁሉንም የኢኮኖሚ ትኩሳት ያጠፋል፡፡ ይህ ሲደረግ ምን ይሆናል? የሚለው ይታያል፡፡ የምንዛሪ ለውጡ ሲደረግ የወጪ ንግዱን ለማሻሻል ነው የሚል ነበር፡፡ አሁን የሚገባው ዶላርም ወደ ሥራ እስኪገባና ውጤት እስኪያመጣ ድረስ ሁለት ዓመት ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ እስከዚያ ድረስ ምን ልትሆን ነው? በዚህ ጊዜ ውስጥ ቢያንስ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል፡፡ ግብፆች ይህ ተሞክሮ ነበራቸው፡፡ እስካሁን የጠቃቀስኳቸውን ነገሮች በመፈጸም ዕዳቸውን ከፋፍለው የውጭ ክምችት አላቸው፡፡ ሶማሊያ ከከብት የወጪ ንግድ 300 ዶላር ሚሊዮን አግኝታለች፡፡ እኛ ግን 60 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ አላገኘንም፡፡ አንድ ከብት ሸጬ እዚህ በመደበኛው መንገድ 27 ሺሕ ብር ብቻ የማገኝ ከሆነና በሌላው መንገድ 35 ሺሕ ብር የማገኝ ከሆነ፣ የሃይማኖት ጉዳይ አይደለም፡፡ በ27 ሺሕ ብር ለመሸጥ አልሞክርም፡፡ ወርቅን እንይ፡፡ በአንድ ወቅት 600 ሚሊዮን ዶላር አስገኝቶ ነበር፡፡ አሁን 150 ሚሊዮን ዶላር ነው ያመጣው፡፡ ገንዘቡ የቀነሰው ወርቅ መመረት ስለቆመ ግን አይደለም፡፡ በ35 ብር ስለሚሸጡት አብዛኛው ሾልኮ ይወጣል፡፡ የውጭ ሐዋላ ገቢ በባንክ ከሚገባው ይልቅ በሌላ መንገድ የሚገባው ይበልጣል፡፡ መንገዱን ካላጣ በቀር በ35 ብር መመንዘር እየቻለ በ27 ብር አይልክም፡፡ መንገዱን ስታስተካክለው ግን ይህ ሁሉ ይስተካከላል፡፡ የሚሸሸው ገንዘብም ይቀንሳል፡፡ የዋጋ ግሽበት እንዳለ የሚገነዘብ ሰው ገንዘቡን በብር ባንክ ከማስቀመጥ ይልቅ ዶላር ገዝቶ ያስቀምጣል፡፡ እንዲህ ባለው አካሄድ የአገሪቱ የክፍያ ሚዛን ይስተካከላል፡፡ በሁለት ዓመት ውስጥ ከኢንቨስትመንቱ ጋር ተያይዞ የሚመጣው ገንዘብ ኢኮኖሚውን ሚዛናዊ እንዲሆን በማድረግ ያረጋጋዋል፡፡ ፕራይቬታይዜሽን ልንደቅ፣ ልንሞት ካልንበት መንገድ እንዲያነሳን፣ የውጭ ምንዛሪ እንዲያመጣ፣ የመጣውን የውጭ ምንዛሪም መክፈል ያለብንን ዕዳ ከፍለን ከዚያ በኋላ ግን በዚህ ችግር ዙሪያ እንዳናወራ የምንዛሪ ሥርዓታችንን በማስተካከል እንድንጓዝ ማድረግ ነው፡፡ የገቢ ንግዱ እኮ እየተደጎመ ነው፡፡ የወጪ ንግዱ ደግሞ እየተቀረጠ ነው፡፡

 

ሪፖርተር፡- ሪፎርሙን በሚመለከት የውጭ ምንዛሪ የማግኘት ጉዳይ የመዋቅራዊ ችግር አካል በመሆኑ እንዲህ ያሉ ማስተካከያዎች በማድረግ ሚዛናዊ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል?

 

አቶ ኤርሚያስ፡- አሁን ለሞት ስንቃረብ የውጭ ምንዛሪ አንድኖናል፡፡ የበሽታው መንስዔ የምንዛሪ ሥርዓቱ ነው፡፡ ይህንን በማስተካከላችን ብቻ ሌላ ምንም ኢንቨስትመንት ሳናካሂድ የሚመጡ የውጭ ምንዛሪ ገቢዎች ይኖራሉ፡፡ ለቀጣዩ ደግሞ ከምርት ዘርፍ፣ ከማኑፋክቸሪንግ፣ ከአገልግሎትና ከግብርና የሚመነጨው ምርት ጥሩ ገበያ አለው፡፡ ዋጋው ደህና ነው፡፡ አምራቾች የገበያው ሁኔታ ስለሚስባቸውና የውጭ ምንዛሪ የማግኘት ችግራቸው ስለተቀረፈ፣ የብድር ችግር ስለተፈታ፣ አክሲዮን መሸጥ ሲፈልጉ ስለሚሸጡና ይህንን የሚያግዙ የምርምር ተቋማትም ስለሚመጡ ሚዛኑ ይጠበቃል፡፡ ኢትዮጵያውያን የተለየ ባህሪና ፍጥረት ያለን ይመስለናል፡፡ እንደ ሰው ጥሩ ስሜት ሊሆን ይችላል፡፡ ኢትዮጵያውያን የተሻልን ነን ስላልን ብቻ ኢትዮጵያ ላይ የመሬት ስበት የለም ልንል አንችልም፡፡ ላለፉት 27 ዓመታት የውጭ ባንክ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት አይችልም ተባለ፡፡ ነገር ግን የፋይናንስ መሠረተ ልማት ከመንገድ፣ ከትምህርትና ከሌላውም እኩል አስፈላጊ ነው፡፡ የሚሰጡት ምክንያቶች ብሔራዊ ባንክ የመቆጣጠር አቅም የለውም የሚል ነው፡፡ ሰዎቹ ብዙ ዓመት በባንኩ እንደመቆየታቸው ጭምር እንዴት ነው ይህን ያህል ጊዜ በቆየ ሥርዓት ውስጥ የመቆጣጠር አቅም የማይኖረው? ጂቡቲና ሶማሊያ የውጭ ባንኮችን መቆጣጠር ችለዋል፣ በጂቡቲ የስቶክ ገበያ አለ፡፡ አፍሪካ ውስጥ የስቶክ ገበያ የሌላቸው አገሮች ዘጠኝ ናቸው፡፡ እነማን ናቸው ካልን ደቡብ ሱዳን፣ ኤርትራ፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎና አንጎላ ምዕራብ አፍሪካ ውስጥ ቤኒን የመሳሰሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ያሉባቸው አገሮች ናቸው፡፡ እኛ ከእነዚህ አገሮች ተርታ ነው የተሠለፍነው፡፡ መንግሥት የለም? የሚስብ ሰው የለም ወይ? የሚያስብሉ ናቸው፡፡ ማወቅና መጨበጥ ያለብን ነገር እነዚህን ነገሮች ለማድረግ የመጨረሻዎቹ ነን፡፡ በተሳሳተ የገንዘብ ፖሊሲ ሳቢያ ነው፡፡ ግድብ ለመሥራት አቅም አለን፡፡ ባንክ ለመቆጣጠር ግን አቅም የለንም፡፡ ከውጭ የሚመጡት ባንኮች እኛም ሳንሆን፣ ራሳቸውን በራሳቸው የሚቆጣጠሩ ናቸው፡፡ መቆጣጠር አንችልም የሚለው ሰበብ ነው፡፡ እውነትም መቆጣጠር የማይቻል ከሆነ ቦታው ላይ ያለው ሰው መነሳት አለበት፡፡

 

ሪፖርተር፡- መዋቅራዊ ችግር አለ በሚለው ላይ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተሞክሯል፡፡ ነገር ግን እንደሚጠበቀው ሊነሳ አልቻለም፡፡ ሌሎች አማራጮችን ማየት አለብን የሚል ሐሳብ በጽሑፍዎ አንስተዋል፡፡ ምንድን ናቸው እነዚህ አማራጮች?

 

አቶ ኤርሚያስ፡- የኢትዮጵያን የዕድገት መንገድ ለመቀየስ ስትራቴጂዋን ስትነድፍ ከምንድነው የምትነሳው? ካፒታል ሳይኖረን ካፒታል በትልቁ የሚጠይቅ ስትራቴጂ ቢኖረን አይሠራም፡፡ ከፍተኛ ቴክኖሎጂ ሳይኖረን የዚህ ስትራቴጂ ቢኖረን አይሠራም፡፡ ስለዚህ የአንድ አገር የልማት ስትራቴጂ መነሳት ያለበት ከመሠረታዊ ብሔራዊ ጉዳዮቿ ነው፡፡ ነዳጅ ያለው ከነዳጁ ተነስቶ ፖሊሲውን ይቀርፃል፡፡ የሠለጠኑት የምዕራብ አገሮች የኢኮኖሚያቸው ዋና ግብዓት ከፍተኛ ዕውቀት ነው፡፡ የዓለም ጥግ የደረሰ ቴክሎጂና ገደብ የሌለው የካፒታል አቅርቦት፣ ገደብ የሌለው የተማረና የሠለጠነ የሰው ኃይል፣ ከፍተኛ የፋይናንስና የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማትና ጥሩ የአስተዳደር ሞዴል ስላላቸው፣ የሚያመርቱት በዓለም ላይ የመጨረሻውንና የረቀቀውን ምርት ነው፡፡ 20 ዓመት ያልሞላቸው ኩባንያዎች ከ100 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ የሚያወጡ እየሆኑ ነው፡፡ ይህንን ያህል ዋጋ ያለው ነገር የተፈጠረው ያላቸው አቅም ስለሚፈቅድላቸው ነው፡፡ የእኛ አገር ኢኮኖሚ በሰው ብናየው በደንብ አላሰብኩትም እንጂ የአሥር ዓመት ልጅ ቢሆን ነው፡፡ ኢሕአዴግ ሲገባ የሦስት ወር ጨቅላ ሕፃን ተረክቦ ጤነኛ ያልሆነና የተበደለ የእንጀራ ልጅ አሳድጓል ማለት ይቻላል፡፡ የግል ዘርፉ አቅም ይህ ነው፡፡ ከዚህ ሌላ በቴክኖሎጂ ላይ እንዴት ነን ብንል ከአፍሪካ እንኳ ትንሹ ሕፃን ልጅ እኛ ነን፡፡ በሠለጠነ የሰው ኃይል ዝቅተኛ ነን፡፡ ካፒታል የለንም፡፡ ኢሕአዴግ እንደገነባ ነበር መለወጥ የነበረብን፡፡ ነገር ግን ይህንን ሁሉ ጊዜ አቃጠልነው፡፡ ሰባቱን ዓመታት እንዲሁ አዲሱ መንግሥት ምን እንደሆነ እስኪገባው ድረስ እንተውለት ብንል 20 ዓመታት ግን አቃጥሏል፡፡ ኢኮኖሚው ወላጅ የለውም ወይ? ምነው ምግብ አይበላም ወይ? የሚባል ዓይነት ልጅ ሆኗል፡፡

 

ነገር ግን ከዚህ ተነስተህ ጎበዝ ራሱን ችሎ የሚኖር ጎልማሳ ሰው መፍጠር አለብህ፡፡ ገና እኮ የገበያ ሥርዓት ውስጥ ያልገባ ደሃ ገበሬ ነው ያለን፡፡

 

የዛሬ 20 ዓመት አዲስ አበባ ስመጣ ትዝ ይለኛል፡፡ ከመስቀል አደባባይ ወደ ብሔራዊ ቦሌ አካባቢ ስትሄድ ገና ነበር፡፡ ገበሬው ዕቃን በዕቃ በመነገድ ውስጥ የነበረ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የግሉ ዘርፍም አቅም ስላልነበረው ይህንን ደካማ ዘርፍ ይዘህ እንዴት ነው ከፍተኛ ካፒታል የሚጠይቅ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ውስጥ የምትገባው፡፡ ይህ ዘርፍ ለውጭ ባለሀብት መሆን ሲገባው ለኢትዮጵያውያን ተደረገ፡፡ በመሆኑም ይህ ዘርፍ ከሚያስፈልገን አምስት በመቶ ላይ ብቻ ነው ድርሻው የተወሰነው፡፡ ወደ አሥር በመቶ ለማደግ የሚፈታተነው ነገር ብዙ ነው፡፡ የሚፈለገው ግብዓት የለውም፡፡ የውጪዎቹም ዝቅተኛ ደመወዝ እንደሚከፍሉ አስበው መጡ፣ ግን ችግር መኖሩን አዩት፡፡ በወጪ ንግድ መወዳደር ከባድ ፈተና ነው፡፡ ሳትቆም አትሮጥም፡፡ በዓመት 16 ቢሊዮን ዶላር የገቢ ዕቃ እናስመጣለን፡፡ ወደ ውጭ የምንለከው ግን ሦስት ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ ነገር ግን ከምናስመጣው ውስጥ እዚሁ እንዲመረትልን ለማድረግ የሚረዳን የኢንዱስትሪ ፓርክ ለምንድነው ያልሠራነው? ዘይት ትልቁ የገቢ ሸቀጥ ነው፡፡ የቅባት እህል በሰፊው እንልካለን፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርክ ከመገንባት ይልቅ ከእኛ ፍላጎት አልፎ ለውጭ የሚያቀርብ ትልቅ ዘይት መጭመቂያ ለምንድነው ያልገነባነው? እንደ ብረቱ ዓይነት በዓመት እስከ ሁለት ቢሊዮን ዶላር እናስገባለን፡፡ ልክ እንደ ድንጋይ ብረት ያላቸው ክልሎች አሉ፡፡ እኛ ራሳችን በአንዱ ድርጅታችን ሰቆጣ ላይ ቁጭ ያለ የኢትዮጵያን የብረት ፍላጎት የሚሸፍን ቦታ ካገኘን ሦስት ዓመታት አልፎናል፡፡ ወደ ሥራ ለመግባት ገንዘብ ይዞ የቆመ ልምድ ያለው ኢንቨስተር አለኝ፡፡ ፈቃድ ለማግኘት አልቻልኩም፡፡ ኧረ ባካችሁ እያልኩ ደብዳቤ እየጻፍኩ ነው፡፡ ኤርሚያስ ማንም ሊሆን ይችላል፣ ብረት ግን ለአገሪቱ ያስፈልጋታል፡፡ የማዕድን ዘርፉ ያልሄደበት ግን ትልቅ ሀብት አለ፡፡ ስለዘርፉ ግንዛቤው ያለው ግን መንግሥት ዘንድ ሳይሆን በመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ በሚሠሩ ባለሙያዎች እጅ ነው፡፡ ቢዝነስ ነው፡፡ የማዕድን ዘርፍ ብዙ የውጭ ባለሀብት ይገኝበት ነበር፡፡ ነገር ግን ትኩረት አልተሰጠውም፡፡ የ16 ቢሊዮን ዶላር ገበያ አለን፡፡ ከዚህ ውስጥ የብረቱ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ እዚህ ማምረት ቢቻል ግን ሦስት ቢሊዮን ዶላር በሚያስገኘው የወጪ ንግድ ገቢ ላይ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ጨመርክበት ማለት ነበር፡፡ የእኛን ገበያ ከሸፈንን በኋላ የጎረቤት አገሮች አሉ፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ የጋራ ገበያ አለ፡፡

 

ስትጀምር ከገጠር ገበሬ ነው ለማኑፋክቸሪንግ የሰው ኃይል የምትመለምለው፡፡ እየቆየ ግን ይህ ገበሬ ነው ውስብስብ ምርት ከማምረትና ከማስተዳደር አልፎ ብዙ ሥራ የሚሠራው፡፡ ኢንቨስተር የሚሆነው እሱ ነው፡፡ በሩን ሳንዘጋ፡፡ ለውጭም ከከፈትነው ደግሞ ባንኩ፣ ቴሌኮሙ ላይና ሌሎቹም ላይ እንዲገባ መፍቀድ የ20 እና የ40 ዓመቱን ጉዞ ማሳጠር እንጂ የገንዘብ ጥያቄ ብቻ አይደለም፡፡ በርን ክፍት ማድረግ የብሔራዊ ማንነት ጥያቄ አይደለም፡፡ እውነተኛው ብሔራዊ ስሜት ልማታችን ነው፡፡ የሚደግፈንና የሚረዳን ወዳጃችን ልማት ነው፡፡ ወረራ እንዳለበት አገር ሁሉን ነገር ዘጋግተን ተቀምጠናል፡፡ እንደ ዕድል ሆኖ መጨረሻ መሆናችን ከአንደኛ ጀምሮ ያሉት አገሮች የሠሩትን ስህተት የማየት ዕድል አለን፡፡ ያገኙትን ውጤትም እናያለን፡፡ ያንን ሁሉ እያየህ አንተም የምታጠፋ ከሆነ መንግሥት አይደለህም፡፡ ልማታዊ መንግሥት የሚያሰኝህ አንዱ መለኪያ ጠንካራ መንግሥት መሆንህ ነው፡፡ ቢሮክራሲው በጣም ውጤታማና ብቁ መሆን አለበት፡፡ የእኛ ቢሮክራሲ ከፖለቲካ ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ ዋናው ታማኝነት ነው ሥራውን ይለምዱታል ሲባል ነበር፡፡ ለ27 ዓመታት ግን ውጤቱን እያየን ነው፡፡ ለ27 ዓመታት ሙሉ የአፈጻጸም ችግር ስንሰማ ኖረናል፡፡ ለምንድነው የማይፈታው? 30ም 40ም ዓመታት ፈጅተን ችግራችንን መፍታት እንችላለን፡፡

 

አሁን የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ለቁርጥ ቀን ደርሰውልናል፡፡ ሌላው የዳያስፖራው ማኅበረሰብ ነው፡፡ የመንግሥትም፣ የአገርም፣ የአፈጻጸም ችግርና የብቃት ጥያቄ መመለሻ ፕራይቬታይዜሽን ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የዳያስፖራው አቅም ነው፡፡ በአንድ በኩል ኢትዮጵያውያን ልዩ ነን የሚሰኘን በዓለም ደረጃ የተማሩ፣ ልምድና ዕውቀት ከማስተዋል የታደሉ የዓለም ቁንጮ ላይ የሚገኙ በርካታ ሰዎች አሉን፡፡ እዚህ ለመምጣት ሥጋታቸው ከሆኑ ነገሮች ውስጥ አንዱ ትልቁ ምሳሌያቸው እኔ ነኝ፡፡ ኤርሚያስን አታዩትም እንዴ ነው የሚባለው፡፡ ግን ደግሞ ልባቸው ያለው እዚህ አገር ነው፡፡ አገራቸውን ይወዳሉ፡፡ ይመጣሉ፣ ይሄዳሉ፡፡ ቤት ይገዛሉ፣ ፋብሪካ አይገነቡም፡፡ ለምን ቢባል የሚሰሙት ሁሉ ስለሌብነትና ስለመጥፎ ፖለቲካችን ነው፡፡ አዲሱ አስተዳደር ያንን እየሰበረ ነው፡፡

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram