”ኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንድታወጅ ያደረጋትን ፈታኝ ሁኔታ አሜሪካ ትረዳለች”- ሬክስ ቲለርሰን
የአፍሪካ ጉብኝታቸውን ትናንት ከኢትዮጵያ የጀመሩት የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን ዛሬ ከኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።
ከውይይታቸው በኋላ ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫም፥ በውይይታቸው ላይ ከሁለትዮሽ ጉዳዮች በተጨማሪም የደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያን ጉዳይ ማንሳታቸው ተመልክቷል።
በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ እንደተሰጣቸው ዶክተር ወርቅነህ በመግለጫው ላይ አንስተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን በበኩላቸው ኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንድታወጅ ያደረጋትን ፈታኝ ሁኔታ አሜሪካ እንደምትረዳ ተናግረዋል።
ወጣት በሆነው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ውስጥ እየተከናወነ ያለው በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የስልጣን ሽግግር አወንታዊ ምልክት መሆኑን ገልፀዋል።
የሀገሪቱን ሁኔታ አሜሪካ እየተከታተለች መሆኑን የገለፁት ሬክስ ቲለርሰን መነግሰት የተለያዩ እስረኞችን ከእስር መፍታቱ ለዴሞክራሲ ግንባታ ያለውን ጠቀሜታ አንስተዋል።
ዴሞክራሲ ጊዜ የሚወስድ እንደመሆኑም የሀገሪቱ ህዝቦችም ከረብሽ በመታቀብ ሂደቱን በትእግስት እንዲጠባበቁ ነው ያሳሰቡት።
በካሳዬ ወልዴ
Share your thoughts on this post