fbpx

ኢትዮጵያ የአልጀርሱን ስምምነት ለመተግበር መስማማቷ ሀገራዊ ጠቀሜታ አለው – ምሁራን

በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለውን የድንበር አለመግባባት ለመፍታት ኢትዮጵያ የአልጀርሱን ስምምነት ለመተግበር መስማማቷ ተገቢ እርምጃ መሆኑን የአለም አቀፍ ህግ ጉዳዮች ምሁራን ተናገሩ።

የኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት በአፍሪካ ከተከሰቱ የድንበር ጦርነቶች ሁሉ ደም አፋሳሹ ሲሆን፥ ከሁለቱም ወገን በርካታ ሺህ የሰው ህይወት በማጥፋት በርካቶችን ደግሞ አፈናቅሏል።

ከዚህ ጦርነት በኋላ ሃገራቱ በአልጀሪያ ተደራድረው የአልጀርስ ስምምነትን ተፈራርመዋል፤ ከመፈራረም ባለፈ ግን ስምምነቱ በተለያዩ ክምንያቶች ሳይተገበር ቆይቷል።

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴም ባለፈው ማክሰኞ ባካሄደው ስብሰባ የኢትዮ-ኤርትራ ወቅታዊ ሁኔታን በጥልቀት በመገምገም፥ አለመግባባቱ እንዲያበቃና ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር ጥሪ አቅርቧል።

በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለውን የድንበር አለመግባባት ለመፍታት ኢትዮጵያ የአልጀርሱን ስምምነት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ለመተግበር መወሰኗንም ኮሚቴው መግለጹ ይታወሳል።

የአለም አቀፍ ህግ ጉዳይ ምሁሩ ዶክተር ያዕቆብ ሃይለማርያም ከጣቢያችን ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ የአልጀርሱ ስምምነት በካርታ ላይ ወሰን የመለየትና በቦታው ተገኝቶ ችካል መትከልን በዋናነት ማንሳቱን ይናገራሉ።

ዶክተር ያዕቆብ የአልጀርሱ ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ኢትዮጵያ ወደ ኋላ ማፈግፈግ እንደማትችል ጠቅሰው፥ በአለም አቀፍ ህግ ሲታይም ጉዳዩ እውነታ መሆኑን ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ እና አስተዳደር መምህሩ እና በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የጥናት ቡድን አባል አቶ አባይ ይመር በበኩላቸው፥ ውሳኔውን ስትራቴጅካዊ እና ወደፊት የሚመለከት ብለውታል።

እንደ እርሳቸው ገለጻ ባድመ ለኤርትራ መንግስት የህልውና ጉዳይ ሆኖ የቆየ ነው፤ ምክንያቱም የኤርትራ መንግስት ኢትዮጵያ ቦታ ይዛብኛለች የሚል አጀንዳን በመያዝ ህዝቡን ሲገዛበት ቆይቷልም ነው የሚሉት።

ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያን ውሳኔ የዘገየ ነው የሚሉት እርሳቸው፥ ስምምነቱ በፍጥነት መተግበር ነበረነበት ብለዋል።

ዶክተር ያዕቆብ ደግሞ በሁለቱ ወገኖች የደረሰው ጉዳት ተሰልቶ የካሳ ኮሚሽኑ ለኢትዮጵያ በተጨማሪ 10 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር መፍቀዱን ያነሳሉ።

ኢትዮጵያ የአልጀርሱን ስምምነት እንደምትቀበል ብትገልጽም የኤርትራ መንግስት ግን በጉዳዩ ዙሪያ ፈጣን ምላሽ ከመስጠት ታቅቧል።

ለዚህ ደግሞ ህዝቡን ለመግዣነት ይጠቀምበት የነበረው የባድመ ጉዳይ እልባት ለማግኘት መቃረቡ አጀንዳ ስላሳጣው መሆኑን አቶ አባይ ይመር ይገልጻሉ።

ከካሳ ኮሚሽኑ ጉዳይ ባለፈ የአልጀርሱ ስምምነት ገቢር ሲሆን የሚነሳ ሌላ ጥያቄ አለ የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ ይግባኝ የሌለው ጉዳይ ነው፤ ኢትዮጵያ ደግሞ ውሳኔውን ያለ ቅድመ ሁኔታ ተግባራዊ እንዲደረግ ወስናለች።

ምሁራኑ ያለ ቅድመ ሁኔታ የሚል መግለጫ የሚለው ግን መሬት ላይ ተግባራዊ ሲሆን የሚገነዘባቸው ነጥቦች ይኖራሉ ስለዚህ የራሳችን ልዩነት አለን ነው የሚሉት።

አቶ አባይ ያለ ቅድመ ሁኔታ የሚለውን ጉዳይ ላይ ጥቅምን ሊያስከብር በሚችል መንገድ ማስፈጸም ይቻላል ይላሉ።

ደክተር ያዕቆብ በበኩላቸው ተግባራዊነቱ በተለይም በድንበር ወሰን አከላለልና ችካል ተከላ ላይ ትልቅ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፥ ሃገራቱ በአግባቡ ሊደራደሩ እንደሚገባ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ የአልጀርሱን ስምምነት ተግባራዊ ማድረጓ ግን የሁለቱን ሀገራት የጋራ ትብብር በማሳደግ ምጣኔ ሀብታዊ ተጠቃሚነታቸውን የሚያጎላ መሆኑንም አንስተዋል።

አቶ አባይ ይመር ደግሞ ለጋራ ተጠቃሚነት ሊሰራ እንደሚገባ በመጥቀስ፥ ቀጣይ ጉዟችን እንዲያምር ራዕያችን ሰፋ ማለት ይገባዋል ባይ ናቸው።

 

 

 

 

በስላባት ማናዬ – ኤፍ ቢ ሲ

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram