“ኢትዮጵያ አገሬ ናት” የሚል ሁሉ ለሠላም መስፈን በአንድነት ሊቆም ይገባል
‘ኢትዮጵያ አገሬ ናት’ የሚል ሁሉ ለሰላም መስፈንና ለአንድነት በጋራ ሊቆም እንደሚገባ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተናገሩ፡፡
ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነው ያለችው ተማሪ ኤልሳቤጥ ፈቃደ ተማሪው፣ ተመራማሪው፣ አርሶ አደሩ፣ ሁሉም በአንድነት አገርን ተረባርቦ ማሳደግና ሰላምን መጠበቅ ይኖረበታል ብላለች፡፡
ይሁን እንጂ አሁን እየተስተዋለ ያለው ተማሪው ተረጋግቶ ትምህርቱን እንዳይማር ፣ ነጋዴው በሰላም ወጥቶ እንዳይገባ እሆነ መሆኑንም ትናገራለች ፡፡
በመሆኑም ስለተሰማራበት ስራ ሳይሆን ስለ ሰላም እጦትና ወጥቶ ስለመግባቱ እንዲያስብ መገደዱን ነው የምትናገረው ተማሪዋ፡፡
“ሰላም ካለ የምታስበው ስለ ማደግ ነው” የምትለው ተማሪዋ “ሰላም ከሌለ ግን የምታስበው ስለ ግል ህይወትህ ብቻ ይሆናል” ትላለች።
አገር የምታድገው በመግባባትና በመመካከር በመሆኑ መንግስት ህዝቡን ሊያዳምጥ፤ ህዝቡም መንግስትን ሊገነዘብ እንደሚገባም ገልጻለች።
“ሰላም ሁሉ ነገር ነው፣ እዚህ ተረጋግተን ብዙ ሆነን በጋራ እየኖርን የምንማረው ሰላም ስላለ ነው፣ የምንሰማቸው አንዳንድ ነገሮች በመጠኑም ቢሆን እየረበሹን ነው” ያለው ደግሞ ተማሪ አዲሱ አለሙ ነው።
አገርን እመራለሁ የሚል ማንኛውም የፖለቲካ አካል በመግባባትና በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንጂ ህዝብን በመከፋፈል መሆን የለበትም፤ አሁን የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጋራ መስራት ይጠበቅበታል ብሏል።
ተማሪ ዘሪሁን ሰቦቃ በበኩሉ ለአገር አንድነት ሁሉም ሰው ሃላፊነት ስላለበት ሰላማዊ ከመሆን ጀምሮ ሌሎችን ለሰላም ዘብ እንዲቆሙ ማድረግ ይኖርበታል ይላል።
ለአገር አንድነትና እድገት መሰረቱ መግባባት ስለሆነ የፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ሲደረግ በመግባባትና ለአገር በሚጠቅም መልኩ ሊሆን እንደሚገባውም ነው የተናገረው፡፡
ለኢትዮጵያ አንድነትና እድገት ቀና አስተሳሰብ ያለው አካል ሁሉ ቅድሚያ ለአገራዊ አንድነትና ሰላም ሊሰጥ እንደሚገባም ነው ተማሪዎቹ በአስተያየታቸው የገለጹት።