fbpx

ኢሕአዴግ ከግንባርነት ወደ ውህድ ፓርቲነት መሸጋገሩ በመጪው ነሐሴ እንደሚታወቅ ተገለጸ

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ከብሔራዊ ድርጅቶች ግንባርነት ወደ ተዋሀደ አንድ ፓርቲነት ለመሸጋገር ከበርካታ ዓመታት በፊት በያዘው ዕቅድ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚሰጥ፣ የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ አስታወቁ፡፡

አቶ ሽፈራው ሰኞ መጋቢት 3 ቀን 2010 ዓ.ም. ለታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ኢሕአዴግን ውህድ ፓርቲ ለማድረግ በተያዘው ዕቅድ ላይ፣ እንዲሁም ከአጋር ፓርቲዎች ጋር የሚኖረውን ግንኙነት በተመለከተም የመጨረሻ ውሳኔ በነሐሴው የኢሕአዴግ ጉባዔ እንደሚወሰን ተናግረዋል፡፡ በዚህ ጉባዔ ይወሰናል ሲባል ግን ወዲያውኑ ኢሕአዴግ ውህድ ፓርቲ ይሆናል ማለት እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡

ኢሕአዴግ ከግንባርነት ወደ ውህድ ፓርቲነት ለማሸጋገር በተለያዩ ስብሰባዎች ሐሳቦች ተነስተው የነበሩ ቢሆንም፣ ከሐሳብነት የዘለለ እንቅስቃሴ እምብዛም አልተደረገም፡፡ በ1999 ዓ.ም. ተሻሽሎ የፀደቀው የኢሕአዴግ መተዳደሪያ ደንብ፣ ኢሕአዴግ የሚመራባቸው አጠቃላይ የአደረጃጀት መርሆዎች ብሔረሰባዊ አደረጃጀት ብቻ የኢሕአዴግን ዓላማ ለማሳካት እንደሚመች ይገልጻል፡፡ ‹‹ኅብረ ብሔራዊ አገር እንደ መሆኗ የተለያዩ ብሔሮቿንና ሕዝቦቿን በአንድነት አሰባስቦ ለማታገል የሚቻለው፣ ግለሰቦችን በተናጠል በሚያሰባስብ ኅብረ ብሔር ድርጅት ሳይሆን የድርጅቶች በተለይ ደግሞ የብሔር ብሔረሰብ ድርጅቶች፣ በተለይ ደግሞ የብሔር ብሔረሰብ ድርጅቶች ግንባር በሆነ አደረጃጀት አማካይነት ነው፤›› በማለት ምርጫው መሆኑን ይገልጻል፡፡

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ሕዝቦች የብሔር የብሔረሰብ ድርጅት በመመሥረት መብታቸውንና ጥቅማቸውን በተሻለ ሁኔታ ለማስጠበቅ እንደሚፈልጉና እንደሚችሉ በተግባር እየታየ በመሆኑ፣ ብሔር ብሔረሰቦች የተሻለ ድርጅታዊ አመራር ማግኘትና በፖለቲካ ሒደቱ በበለጠ መሳተፍ የሚችሉት በብሔር ብሔረሰብ ድርጅቶቻቸው አማካይነት ሲታገሉ እንደሆነም አሁን ያለው ተጨባጭ ሁኔታ እንደሚያሳይ ይገልጻል፡፡

‹‹በመሆኑም እያንዳንዱ ብሔር መብቱንና ጥቅሙን በብሔራዊ ድርጅቶቹ አማካይነት ለማስጠበቅ ያለውን ፍላጎት በተሻለ ደረጃ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ ይፈጥራል፤›› በማለት የመተዳደሪያ ደንቡ ይገልጻል፡፡

አቶ ሽፈራው እንዳሉት ኢሕአዴግ ከአጋር ድርጅቶች ጋር ያለውን ግንኙነት በተመለከተ በነሐሴ ወር እንደሚወስን ተናግረዋል፡፡ ላለፉት 26 ዓመታት ከኢሕአዴግ ጋር እየሠሩ የቆዩት የታዳጊ ክልል ብሔራዊ ድርጅቶች ግንባሩን ይቀላቀሉ? ወይስ ምን ዓይነት ግንኙነት ይኑራቸው? በሚለው ላይ ለመወሰን እንደሆነ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ይናገራሉ፡፡

የኢሕአዴግ መተዳደሪያ ደንብ ግን አጋር ድርጅቶችም ሆኑ ማንኛውም ሌላ ብሔራዊ ድርጅት ኢሕአዴግ የሚጠይቃቸውን መሥፈርቶች አሟልቶ አባል ለመሆን እንደሚችል ይገልጻል፡፡ ከመመዘኛ መሥፈርቶቹ መካከል አንዱ የብሔረሰብ ድርጅት ሲሆን፣ በአንድ ብሔረሰብ ውስጥ ሁለት የብሔረሰብ ድርጅቶች ካሉ መዋሀድ እንዳለባቸው ይገልጻል፡፡ የግንባሩ አባል ከመሆን በፊትም ለአንድ ዓመት ያህል የሙከራ ጊዜ አባል ሆኖ የመቆየት ግዴታ መኖሩንም ያስረዳል፡፡

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram