fbpx

HT

ሐበሻ ታይምስ ሚዲያ

AMHARIC

አዲስ የተሾሙት ስምንት አምባሳደሮች ሰሞኑን ቃለ መሃላ ይፈፅማሉ

አዲስ የተሾሙት ስምንት አምባሳደሮች ሰሞኑን ቃለ መሃላ እንደሚፈፅሙ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም እንደገለፁት፥ አምባሳደሮቹ የተመደቡባቸው ሀገራት ይሁንታ ከተገኘ በኋላም የተመደቡበት ሀገራት ይፋ ይደረጋል።

ቃል አቀባዩ በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫው ላይ የአምባሳደሮቹ ቃለ መሃላ ለነገ ቀጠሮ የተያዘለት እንደነበር የተገለፀ ቢሆንም፥ በዕለቱ ሌላ ብሄራዊ ሁነት ያለ በመሆኑ በሌላ ቀን ይከናወናል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኘሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ኢትዮጵያን በውጭ ሀገሮች ለሚወክሉ አምባሳደሮች በቅርቡ ሹመት መስጠታቸው ይታወሳል።

በባለሙሉ ስልጣን አምባሳደርነት የተሾሙትም፥ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ አቶ አለማየሁ ተገኑ፣ አቶ እሸቱ ደሴ፣ አቶ አዛናው ታደሰ፣ አቶ ዮናስ ዮሴፍ፣ ቶ ድሪባ ኩማ፣ አቶ ያለው አባተ እና አቶ አብዱልፈታ አብዱላሂ ናቸው።

ሚኒስቴሩ በመግለጫው መንግስት ከዳያስፖራው ጋር መልካም ግንኙነት በጀመረ ማግስት የተሾሙት እነዚህ አምባሳደሮች፥ በቀጣይነት ይህን ሁኔታ የማስቀጠል ስራ እንደሚጠበቅባቸው ነው ያመለከተው።

ከሹመቱ ጋር ተያይዞ አንዳንድ ወገኖች የአምባሳደርነት ምድባ በጡረታ ወቅት ለእረፍት የሚሰጥ አድርገው መውሰዳቸው ስህተት መሆኑን ያነሱት አቶ መለስ፥ አምባሳደሮቹ ለእረፍት ሳይሆነ ለከፍተኛ ሀገራዊ ስራና ኃላፊነት ተመድበው የሚሰሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም በኤርትራና በጅቡቲ መካከል ያለው ግንኙነት እንዲሻሻል ኢትዮጵያ ፍላጎት እንዳላት ቃል አቀባዩ አቶ መለስ ዓለም አስታውቀዋል።

የእነዚህ ሁለት ጎረቤት ሀገራት ግንኙነት እንዲሻሻልም ኢትዮጵያ ትልቅ ኃላፊነት ወስዳ እንደምትንቀሳቀስም ነው ያመለከቱት።

ኢትዮጵያ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ችግር ለመፍታት የአሸማጋይነት ኃላፊነቱን ወስዳ ለመስራት እንደምትፈልግም ለጅቡቲ መንግስት ማሳወቋን አቶ መለስ አስታውቀዋል።

የኢፌዴሬ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሰሞኑ የአሜሪካ ቆይታቸው በዚያ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን የሙስሊም ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች “እስልምናን ጥላለች” ብለዋል በሚል የወጡት ዘገባዎች ፍፁም ከእውነት የራቁ እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመድረኩ ላይ ያልተናገሩት መሆኑን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በመንግስትም ሆነ በመሪዎች ደረጃ ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው አስታውቀዋል።

በማህበራዊ ትስስር ገፆች ላይ በተሰራጨው የተሳሳተ መረጃ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት የሚበላሽ አይደለም፤ ምንም የተለወጠ ነገር የለም ነው ያሉት።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም በመግለጫቸው፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአሜሪካ ያደረጉት ጉብኝት ስኬታማ እንደነበረም አስታውቀዋል።

ከተገኙት ስኬቶች ውስጥም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ስለ ኢትዮጵያ ያላቸው አስተሳሰብ እንዲለወጥና ለሀገራቸው ባሉበት ቦታ አምባሳደር እንዲሆኑ ያስቻለ መሆኑን አንስተዋል።

እንዲሁም በዳያስፖራዎች መካከል እርስ በእርስ ልዩነቶች ነበሩ ያሉት አቶ መለስ፥ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ልዩነቱን መቅረፍ የቻለ መሆኑንም በስኬትነት አንስተዋል።

ግንቦት 7ን ጨምሮ ከ26 በላይ በውጭ ሀገራት የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ ሀገር ለመግባት መወሰናቸውና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶሶች መካከል የተፈጠረው እቅር ከጉብኝቱ የተገኘ ስኬት ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአሜሪካ ጉብኝታቸው የአሜሪካውን ምክትል ፕሬዚዳንት ማይክ ፔንስን ጨምሮ ከዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት እና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ዋና ዳይሬክተር ጋር መወያየታቸውም ከጉብኝቱ የተገኘ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአጠቃላይ ከሃምሌ 19 እስከ ሃምሌ 23 2010 ዓ.ም በሶስት የአሜሪካ ከተሞች በተካሄደው ጉብኝትም 20 የተለያዩ መድረኮች መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።

መድረኮቹም በ100 ሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን፣ 70 የሚሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና በ100 የሚቆጠሩ ምሁራን የተካፈሉበት እንደነበረም አስታውቀዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጉብኝትም በ118 ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን መንገዶች እንደተከታተሉትም አቶ መለስ ገልፀዋል።

እንዲሁም በአሜሪካ የሚገኙ 63 የመገናኛ ብዙሃንም የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የአሜሪካ ጉብኝትን በተለያዩ አውታሮች ሽፋን መስጠታቸውንም አስታውቀዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የአሜሪካ ጉብኝት እንዲሳካ ላዳረጉ አካላት በሙሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምስጋናውን ማቅረቡንም አቶ መለስ ገልፀዋል።

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram