fbpx

አዲስ አበባ የሰነበቱት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከኃላፊነታቸው ተነሱ

ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ የሥራ ጉብኝት ሲያደርጉ የነበሩት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን፣ በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ማክሰኞ መጋቢት 4 ቀን 2010 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ተሰናበቱ፡፡

ፕሬዚዳንቱ በትዊተር ገጻቸው ላይ የሲአይኤ ዋና ዳይሬክተር ሆነው በማገልገል ላይ የነበሩት ማይክ ፖምፒዮ እንደሚተኳቸው፣ በፖምፒዮ ቦታ ደግሞ ጊና ሃስፔልን መሾማቸውን አስታውቋል፡፡

‹‹የሲአይኤ ዳይሬክተር ማይክ ፖምፒዮ አዲሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራችን ይሆናሉ፡፡ የሚያስደንቅ ሥራ ይሠራሉም፡፡ ሬክስ ቲለርሰንን ለአገልግሎታቸው ምሥጋና ይግባቸው፡፡ የመጀመሪያዋ ሴት በመሆን ጂና ሃስፔል የሲአይኤ ዳይሬክተር በመሆን ያገለግላሉ፡፡ ሁላችሁም እንኳን ደስ ላችሁ፤›› በማለት ዶናልድ ትራምፕ በትዊተር ገጻቸው ላይ ጽፈዋል፡፡

ሬክስ ቲለርሰን ለአንድ ሳምንት የቆየ የአፍሪካ ጉብኝታቸውን በአንድ ቀን አሳጥረው እንዲመለሱ የተጠሩ ሲሆን፣ የሰሜን ኮሪያን የኑክሌር ጦር መሣሪያን ለማስወገድና ከአሜሪካ ጋር ውይይት ለማድረግ ባሳየችው የአቋም ለውጥ ምክንያት ሊሆን ይችላልም ሲባል ነበር፡፡

ከዚህ በፊት ዶናልድ ትራምፕ ቲለርሰን ከኃላፊነታቸው ይነሱ እንደሆን ሲጠየቁ፣ ‹‹ጊዜ የሚያሳየንን እንጠብቃለን፤›› ሲሉ ጥያቄውን አደባብሰው አልፈውት ነበር፡፡ ልክ ያልሆነ መረጃ ነውም ብለው ተችተውት ነበር፡፡

ቲለርሰን በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) እና ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር መወያየታቸው ይታወሳል፡፡

የሬክስ ቲለርሰን የሥልጣን ቆይታ ከዓመት ያልዘለለ መሆኑ በአሜሪካ ዘመናዊ ታሪክ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ለአጭር ጊዜ የቆዩ ናቸው፡፡ ሆኖም ቆይታቸው ድንቅ ሊባል የሚችል እንዳልሆነ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡

የማሳቹሴትስ ዩኒቨርሲቲ የአሜሪካ የውጭ ፖሊሲ ተመራማሪ ፖል ሙስግሬቭ፣ ‹‹ሬክስ ቲለርሰን ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወዲህ ካሉት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ብቻ ሳይሆን፣ ከአጠቃላይ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ሲነፃፀሩ የዝርዝሩ ታችኛው ረድፍ ላይ ያርፋሉ፤›› ሲሉ ሚኒስትሩን ተችተዋቸዋል፡፡ የቀድሞ የኤክሶን ሞቢል ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት ቲለርሰን ያለምንም ውጤታማ ቆይታ ኋይት ሀውስን የሚለቁ መሆናቸውም ተወስቷል፡፡

ከቲለርሰን ዋነኛ ድክመቶች መካከል ለደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ለመሾም ረጅም ጊዜ የፈጀባቸው መሆኑ፣ በአካባቢው ለሚታዩ ችግሮች አፋጣኝ መፍትሔ ለመስጠት እንዳይቻል አድርገዋል እየተባሉም ይተቻሉ፡፡

በጆርጅ ቡሽ የፕሬዚዳንትነት ጊዜ አማካሪ የነበሩት ኢሊየት ኮኸን፣ ‹‹እስከ ዛሬ ከነበሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ዝቅተኛ ደረጃ በመያዝ ከሥልጣን የሚወርዱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይሆናሉ፤›› ብለዋል፡፡

ሬክስ ቲለርሰን ዶናልድ ትራምፕን በመውቀስ የሚታወቁ ሲሆን፣ ለፕሬዚዳንትነት ብቁ አዕምሮ የሌላቸው ናቸው ሲሉም ተደምጠዋል፡፡ ቲለርሰን የአሜሪካ 69ኛው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነበሩ፡፡

ምንጭ፡- ሪፖርተር

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram