fbpx

አወዛጋቢው የእግር ኳስ ዳኞች ማስመሪያ

ወፍራም የሳሙና አረፋ ይመስላል። የእግር ኳስ ዳኞች እንደ አንድ የመኪና ጥገና ባለሙያ ወገባቸው ላይ ይታጠቁታል። በእግር ኳስ ታሪክ ትልቅ ከሚባሉት ግኝቶች መካከል ይህ መስመር ማስመሪያ ፈሳሽ ይጠቀሳል።

ነገር ግን ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ የበላይ አካል ፊፋ እና ይህን ፈሳሽ ፈጠረ የሚባለው ብራዚላዊው ሄይኔ አለማዥን ከባለቤትነት እና ከክፍያ ጋር በተያያዘ መስማማት አልቻሉም።

ይህም የዳዊት እና የጎልያድ ፍልሚያ እንደሆነ አለማዥን ለቢቢሲ ተናግሯል። “እነሱ (ፊፋ) በጣም ትልቅ ናቸው። ይሄ ማለት ግን ከህግ እና ከእውነት በላይ ናቸው ማለት አይደሉም።”

ፊፋ በበኩሉ ጉዳዩ በሂደት ላይ ያለ ስለሆነ አስተያየት መስጠት አልፈልግም ብሏል።

ኤሮሳል የተባለው ፈሳሽ በአርባ አራት ሃገራት ፈቃድ ያገኘው በብራዚላዊው አለማዥን እና አርጀንቲናዊው የሥራ ፈጠራ ባለሙያ እና ጋዜጠኛ ፓብሎ ሲልቫ ስም ነው።

ምንም እንኳን ፈሳሹ በተለያዩ ውድድሮች ላይ ጥቅም ላይ ቢውልም፤ ከአራት ዓመት በፊት በብራዚሉ የዓለም ዋንጫ ወቅት 300 ቆርቆሮዎች ጥቅም ላይ መዋላቸው ህጋዊ እንዳደረገው ይታሰባል።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በሁሉም ፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ውድድሮች ላይ በብዛት ዳኞች እየተጠቀሙበት ነው።

አለማዥን እና ሲልቫ ከፊፋ ጋር ውይይት ከጀመሩ ሰነባብተዋል፤ መጀመሪያ እንደ ተባባሪ ከዚያም እንደ የድርሻ ተጋሪ። በመጨረሻ ግን በብራዚል ፍርድ ቤት ክርክር ጀምረዋል።

ከአንድ ወር በፊት የሃገሪቱ ሁለተኛ ደረጃ ፍርድ ቤት ፈሳሹን የመጠቀም መብት የማን እንደሆነ እስኪወሰን ድረስ ፊፋ እንዳይጠቀምበት ወስኖ ነበር።

ሄይኔ አለማዥን
አጭር የምስል መግለጫሄይኔ አለማዥን

አሁን ደግሞ የሦስተኛ ደረጃ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ እየተጠበቀ ነው። ፊፋ ግን ፈሳሽ ማስመሪያውን ዛሬ (ሰኔ ሰባት) በሚጀምረው የሩሲያው የዓለም ዋንጫ ይጠቀመው አይጠቀመው አልገለጸም።

ውሳኔው በዓለም ዋንጫ ጅማሮ ላይ ሊታወቅ ይችላል፤ ስለዚህ ትልቅ ዓለም አቀፍ ቅሌት ሊሆን ይችላል ብሏል አለማዥን።

ከፍርዱ በኋላ ምን ያህል ገንዘብ እንደሚወሰን ባይታወቅም፤ አለማዥን ግን 35 ሚሊዮን ዶላር ለካሳ ጠይቋል። ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት አንዴ ስለቀረበ እና ፈሳሹ መጀመሪያም ጥቅም ላይ ስለዋለ ገንዘቡ ወደ 100 ሚሊዮን ዶላር ከፍ ሊል ይችላል የሚለው ደግሞ ሲልቫ ፓብሎ ነው።

በትንሿ ኡበርላንዲያ ከተማ የሚኖረው የ47 ዓመቱ ጎልማሳ ሄይኔ አለማዥን በዚህ ግኝት ላይ በትጋት ሰርቷል። በአንድ የቡና ማሳ ላይ የማሽን ዘዋሪ ሆኖ ነው የሚሰራው።

”በትንሽ ከተማ ውስጥ የምኖር ትንሽ ሰው ነኝ” የሚለውአለማዥን፤ ህይወት ሁሌም ቢሆን አስቸጋሪ እንደነበረ ይናገራል።

አሁን እንደዚህ ፍርድ ቤት ቆሞ መከራከር ሳይጀምሩ በፊት እሱ እና ፊፋ ጥሩ የሚባል ግንኙነት ነበራቸው።

የእግር ኳስ ዳኛImage copyrightAFP

የቀድሞው የአርጀንቲና እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንትና በፊፋ ትልቅ ቦታ የነበራቸው ኢቫን ሁሊዮ ግሮንዶና የዚህ ፈጠራ ዋነኛ አቀንቃኝ ነበሩ።

ህጎችን የሚያወጣው የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ቦርድ በ2012 ኤሮሳል የተባለውን ፈሳሽ ጥቅም ላይ እንዲውል ፈቀደ።

በዚህ ጊዜ ነበር ፊፋ የባለቤትነት መብቱን በ500 ሺ ዶላር ለመግዛት የወሰነው። “ነገር ግን ገንዘቡ በጣም ትንሽ እንደሆነና የመብት ማስከበር ሂደቱን ለማከናወን እነኳን በቂ ስላልሆነ 40 ሚሊየን ዶላር እንድንጠይቅ ሲለቫ ነግሮኝ ነበር” ይላል አለማዥን።

የቀድሞው የአርጀንቲና እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ሁሊዮ ግሮንዶና ህይወታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኋላ ኤሮሳል ጥቅም ላይ መዋል የጀመረ ሲሆን፤ ፊፋም ፈቃድ ከሌላቸው አምራቾች ጋር ስምምነት አድርጎ ሌላ ውል ተፈራረመ ይላል አለማዥን።

ለጥያቄው መልስ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ስላልተሳካለት፤ አለማዥን ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ ፊፋን በእምነት ማጉደል፣ በንግድ ኢ-ተአማኒነት እና ፈቃዱን ያለአግባብ በመጠቀም በሚሉ ዝርዝሮች ክስ አቅርቧል።

BBC Amharic

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram