fbpx

አክም ብሎ መግደል – ኪዳኔ መካሻ

– በህክምና ላይ በሚፈፀም ቸልተኝነት ወይም የሙያ ስህተት ታካሚው ላይ ለሚደርስ ጉዳት ተጠያቂው ማን ነው?

– የህክምና ባለሙያውና የጤና ተቋሙ ላደረሱት ጉዳት ያለባቸው ኃላፊነት ምንድን ነው?

– የተሰጠው ህክምና ሙያዊ ጥራቱ እንዴት ይመዘናል?

ሰሞኑን በድንገት ያጣነው የተወዳጁ ድምፃዊ ታምራት ደስታ ህልፈትን ከድንገተኛነቱ በላይ የአሟሟቱ ሁኔታም አሳዛኝና አስደንጋጭ አድርጎታል።

የተረጋገጠ መግለጫ ባይሰጥም የሞተው በሕክምና ስህተት እንደሆነ ተሰምቷል።

ምክንያቱ ባግባቡ ተጣርቶ በህክምና ስህተት ከሆነ አጥፊዎች ተገቢውን አስተማሪ ቅጣት ማግኘት አለባቸው።

በተለያዩ ጊዜያት ጉዳት ብሎም ሞት ያስከተሉ የህክምና ስህተቶች የመከሰታቸው ነገር እየተባባሰ የመጣ ይመስላል።
እስቲ በሕጋችን የህክምና ሙያ ጥፋቶች እንዴት እንደሚታዩ እናንሳ።

– ‘ዋናው ነገር ጤና’ ነውና ጤናችን ሲታወክ ወደ ህክምና እንደሄዳለን። ፍላጎታችን ህክምና ባለሙያዎቹ ባላቸው እውቀት አክመው እንዲያድኑን ነው።

አንዳንድ ጊዜ ግን በጤና ባለሙያው ቸልተኝነት ወይም ስህተት ለመዳን የሄደ ሰው ይብሱኑ ታሞ ወይም ለሌላ ጉዳት ተጋልጦ
ይመለሳል።

ሕክምና ጥፋትና ቸልተኝነት

ሕክምና የሚካሄደው ለአዎንታዊ ውጤቶች ቢሆንም ታካሚው ከሕክምናው በኋላ ይጠብቅ ከነበረው የጤና ሁኔታው የባሰበት
ደረጃ ላይ ሊደርስ ይችላል። በሌላ አነጋገር ታካሚውን ለማዳን የታሰበው ህክምና በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው በህመሙ
ላይ ሌላ ችግር ሊያስከትሉበት ይችላል።

በህክምና ጥፋት ወይም ቸልተኝነት ታካሚው ላይ የደረሰ ጉዳትን ለመካስ የተለያዩ ሀገራት ሁለት አይነት የተለመዱ መለኪያዎችን
ይጠቀሳሉ።

የመጀመሪያው ‘የጥፋተኝነት’ መለኪያ ሲሆን የተጎዳውን ህመምተኛ ለመካስ የሀኪሙ ወይም የጤና ተቋሙ
ህክምናውን ሲሰጥ የፈፀመው ጥፋት መኖር አለበት የሚል መርህ ላይ የተመስረተ ነው።

ሁለተኛው ደግሞ ያለ ጥፋትም ቢሆን በህክምናው ምክንያት ጉዳት የደረሰበት ታካሚ፤ ሀኪሙ ወይም የጤና ተቋሙ ጥፋት መፈፀሙን
ማሳየት ሳይጠበቅበት ተመጣጣኝ ካሳ ማግኘት ይገባዋል የሚል ነው።

ቸልተኝነትና ጥፋት በአጠቃላይ ከውል ውጭ የሚፈጠሩ ግንኙነቶችን ተከትለው፤ አንድ ሰው በሌላው ሰው ላይ ወይም በንብረቱ
ላይ ጉዳት በማድረስ የሚፈፅመው የሕግ ስህተት ውስጥ የሚካተቱ ናቸው።

ከሕክምና እና ከማስታመም ውል አንፃር ስናየው ፤ሀኪሙም ሆነ የጤና ተቋሙ ተገቢውን እንክብካቤና ሙያዊ ጥረት እንዲያደርጉ ይጠበቅባቸዋል።

ስለዚህ የሕክምና ሙያ ጥፋት ወይም ቸልተኝነት ይህን የውል ግዴታቸውን እንደመጣስ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። በመሆኑም
የህክምና ሙያዊ ጥፋቶች እና ቸልተኝነቶች፤ በውል ግንኙነት ወይም ከውል ውጪ በሚደርስ ጉዳት የሚፈጠሩ ኃላፊነቶች ሊሆኑ
ይችላሉ።

ይህ የሚወሰነው የሀገሩ ህግ እና ፖሊሲ የህክምና ጥፋት እና ቸልተኝነት ኃላፊነት በየትኛው አግባብ ይከሰታል ብሎ ባስቀመጠው መለኪያ መሰረት ነው።

በውልም ሆነ ከውል ውጪ በሚደርስ ጉዳት ‘ቸልተኝነት’ እና ‘ጥፋት’ ልዩነታቸውን እንመልከት።

የህክምና ሙያዊ ቸልተኝነት ፡- ቸልተኝነት ተገቢውን ጥንቃቄ አለማድረግ ሲሆን አንድን ነገር ለማድረግ የሚያስፈልገውን
ተገቢውን ጥንቃቄ ያለምክንያት በመተው የሚፈፀም ድርጊት ነው።

የድርጊቱ ምክንያታዊነት የሚመዘነው በተመሳሳይ ሁኔታ ላይ የነበረ ሰው ምን ጥንቃቄ ያደርግ ነበር በሚለው መመዘኛ ነው።

ከጤና ባለሙያዎችና ተቋማት አንጻር ስናየው ደግሞ፥ ቸልተኝነት ማለት የጤና ባለሙያው ከትምህርቱ ከእውቀቱ እና ከልምዱ
ማወቅ የነበረበትን ነገር በመተው የሰራው ጥሩ ያልሆነ ነገር ሲሆን፤ ሀኪሙ ድርጊቱን የፈፀመው ግን ሆን ብሎ ወይም አውቆ
ላይሆን ይችላል ማለት አይደለም።

የህክምና ሙያዊ ጥፋት ፡-  የሙያ ጥፋት በባለሙያው በኩል ቸልተኝነት ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል አንድ ባለሙያ ቅድሚያ
ሊሰጣቸው የሚገቡትን ሙያዊ መመዘኛዎች ባለመከተል ወይም እንደባለሙያ ሊያስከትሉ የሚችሉትን ነገሮች እንዳለው እውቀትና ክህሎት ባለማስተዋል የሚሰራው ሙያዊ ሥራ ነው።

በመሆኑም ሙያዊ ጥፋት የሚባለው ሙያዊ የህክምና አገልግሎት መለኪያዎችን እና አገልግሎቱን የሚሰጠውን ሰው የሙያ ደረጃ
የሚመለከት ነው። ድርጊቱ በባለሙያው ወይም ያለባለሙያው ሊፈፀም የሚችል ቢሆንም፤ የህክምና ባለሙያው በሙያ ጥፋት ወይም በቸልተኝነት ድርጊቱን ሲፈፅም ባለሙያው ያልሆነው ሰው ደግሞ ጥፋት ሊፈፅም የሚችለው በቸልተኝነት ብቻ ነው።

የህክምና ሙያዊ ጥፋት በኢትዮጵያ ሕግ፦ የህክምና ሙያዊ ጥፋት በአጠቃላይ ፍትሃ ብሔራዊ ጉዳይ ነው። በህክምና ሙያዊ ጥፋት
ተጠያቂነት በውል ወይም ከውል ውጭ ከሚፈጠር ግንኙነት ሊነሳ ይችላል። የኮመን ሎውን ስርዓት ሚከተሉ ሀገራት ውስጥ፤ ጉዳዩ ከውል ውጭ በሚደርስ ኃላፊነት በሚመለከቱ ሕጎች ውስጥ የሚወድቅ ነው።

በኢትዮጵያችን የህክምና ሙያዊ ጥፋት ክስ ከውል ወይም ከውል ውጭ ከሚደርስ ኃላፊነት ሊመነጭ ይችላል።

አብዛኛውን ጊዜ ህመምተኛው ከጤና ተቋሙ ጋር ውል ይገባል። ከታካሚውም ከጤና ተቋሙም የሚጠበቀው ተቋሙ የህክምና አገልግሎቱን ለመስጠት መፍቀዱ እና ታካሚው ደግሞ ህክምናውን ለማድረግ መስማማቱ ነው። የጤና ተቋማቱ ለታካሚው
ያለባቸው ግዴታ የሚመነጨውም በዋነኝነት ከገቡት የህክምና መስጠት ውል ነው።

ህመምተኛው ህክምናውን ሲወስድ ጉዳት ከደረሰበት የጤና ተቋሙ የገባውን የውል ግዴታ በመጣሱ ለፈፀመው ስህተት ክስ ሊያቀርብበት ይችላል።

በህክምና ውል ውስጥ የውል ግዴታን መጣስ ምን ማለት ነው የሚለው ጥያቄ እዚህ ጋር ይነሳል። በ1960 በወጣው የፍትሃብሔር ሕጋችን የህክምና የማከም ውል በአገልግሎት ውል ውስጥ ተካቷል። በዚህ አይነት ውሎች ውስጥ አንድ የተለየ ውጤትና እንደሚገኝ ማስተማመን ከባድ በመሆኑ በምትኩ ተዋዋዩ በገባው ግዴታ መሰረት ተገቢውን ጥንቃቄና የሙያ ብቃት አገልግሎቱን መስጠት
ይጠበቅበታል።

በሌላ በኩል የህክምና ሙያዊ ጥፋት ክስ በጤና ተቋማት ላይ ከውል ውጭ በሚደርስ የጉዳት ካሳም ሊጠየቅ ይችላል፤ ሆኖም አብዛኛውን ጊዜ የታካሚውና የጤና ተቋሙ ግንኙነት በውል ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ከውል ውጭ በሚደርስ ኃላፊነት የሚነሳው ጥያቄ
በሁለተኛ ደረጃ የሚቀመጥ ነው።

በአጠቃላይ በሀገራችን የህክምና ሙያዊ ጥፋት የሚዳኘው ጥፋቱን የፈፀመውን በመለየት ነው። ሆኖም ለከሳሹም ሆነ ለፍ/ቤቶች ጉዳቱ
በማን ጥፋት እንደተከሰተ መለየቱ ቀላል አይደለም። የህክምና ሙያዊ ጥፋት የካሳ ጥያቄም ከተራ የጉዳት ካሳ ጥያቄዎች ብዙም
ልዩነት ስለሌለው ዳኛውን ወይም ከሳሹን ምክንያታዊ የሆነ የህክምና ስራ ተሰርቷል ወይ የሚለውን በቅጡ የማያውቁትን መመዘኛ
እንዲጠቀሙ ያስገድዳቸዋል።

በተጨማሪም ከፍ/ቤቱም ሆነ ከከሳሹ ይልቅ በጤና ተቋሙ የተሰጠው አንድ የህክምና አገልግሎት  ተገቢውን ደረጃ የጠበቀ ነው ወይ
የሚለውን መለየት የሚችለው የህክምና ባለሙያው ነው።

የአንድ የህክምና አገልግሎት በቂና ደረጃውን የጠበቀ ነው የሚለው፤ የሕግ እውቀት ባለመሆኑ በተገቢው የሙያ መስክ የባለሙያ ምስክርነት ማስፈለጉ እሙን ነው።

በሀገራችን የባለሙያ ምስክሮች አብዛኛውን ጊዜ ለተከሳሹ ስለሚያደሉ በከሳሽ ወገን ለመመሰከር ዳተኝነት ይታይባቸዋል።

ሆኖም በመንግስት የተቋቋሙ ሌሎች የህክምና አሰጣጥ ደረጃን የሚመዝኑና ሙያዊ ጥፋት መኖር አለመኖሩን የሚመሰክሩ ተቋማት
አሉ።

የኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎች ም/ቤት በሚኒስትሮች ም/ቤት ደንብ ቁ 76/1994 የተቋቋመ ሲሆን ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። የሙያዊ ስነምግባር ንኡስ ኮሚቴው የተሰጠው ህክምና ደረጃውን የጠበቀ ነው ወይ ? የሚለውን ታካሚው አቤቱታ ሲያቀርብ መዝኖ
አስያየት ይሰጣል።

የአቶ ሀብታሙ ስማቸው በ2004 ዓ.ም በሰሩት ያልታተመ የጥናት ፅሁፍ፤በሀላፊነቱ ላይ  ነጥቦችን አንስቷል። ራሳቸውን ችለው የጤና ተቋሙ ተቀጣሪ ሳይሆኑ በህክምና ሙያዊ ጥፋት ጉዳት የሚያደርሱ የጤና ባለሙያዎችን በተመለከተ፤ የሀገራችን ሕግ የጤና ተቋሙ
ያለበትን ተጠያቂነት የሚመለከት ሲሆን፤ አሁን ያሉት ሕጎች በውልም ሆነ ከውል ውጭ በሚደርስ ጉዳት የጤና ተቋማቱን ከኃላፊነት
ሊያስመልጥ የሚችል ክፍተት ስላለበቸው፤ ሕግ አውጭው የጤና ተቋማቱን በኃላፊነት የሚያሳትፍ ሕግ ማውጣት እንዳለበትና በህክምና ሙያ ጥፋት የሚደርስ ኃላፊነት እንደሌሎች የጉዳት ኃላፊነቶች ሳይሆን በተፈጥሮውም በእጅጉ አሳሳቢ በመሆኑ ራሱን የቻለ ሕግ ሊወጣለት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የወንጀል ሀላፊነትን በተመለከተ ደግሞ ተገቢውን የህክምና አገልግሎት ለታካሚው በቸልተኝነት ወይም ሆን ብሎ ባለመስጠት የአካል ጉዳት ወይም ሞት ያደረሰ ሀኪም እንደየጥፋቱ ክብደት በእስራት እና በሌሎችም ከሙያ ስራው ጋር በተያያዙ የክልከላ ቅጣቶች እንደሚቀጣ የወንጀል ሕጋችን ይደነግጋል።

ከበደልም በደል
አክም ብሎ መግደል!

DireTube

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram