fbpx

‹አንበሳ አውቶብስ› መስሎን ጅብ ስንጋለብ መኖራችንን ሰማን

‹አንበሳ አውቶብስ› መስሎን ጅብ ስንጋለብ መኖራችንን ሰማን› | አሳዬ ደርቤ በድሬ ቲዩብ

በቀን ጅቦች ዘመን ያልተሰራነው ነገር የለም፡፡

‹እንጀራ› እያልን ጀሶ ስንበላ ኖረናል፡፡

‹ዘይት› እያልን በኬሚካል ስናበስል ኖረናል፡፡

‹ስኳር ፋብሪካ› እየጠበቅን በጨው ስንጠጣ ከርመናል፡፡

የራሳችንን መኖሪያ ቤት እየጠበቅን የኪራይ ቤት ውስጥ ከፍሎ መኖር አቅቶን ከአንዱ ሰፈር ወደ ሌላው ሰፈር ስንዞር ኖረናል፡፡

በሁለት አሃዝ የሚለካ የወረቀት ሪፖርት እየሰማን በቢሊዮን ብር የሚከሰሱ ሙሰኞችን ለማየት ችለናል፡፡

አሁን ደግሞ ‹አንበሳ ባስ› እያልን ጅብ ስንጋልብ መክረማችንን ሰማን፡፡

ነገሩ የሆነው እንዲህ ነው፡፡

የቀን ጅቦቹ 120 አሮጌ አውቶብሶችን ገዙ፡፡ ከዚያም የገዟቸውን አሮጌ መኪኖች የአንበሳ አውቶብስን ቀለም በመቀባትና አርማውን በመለጠፍ በአዲስ አበባ አስፓልት ሲያስፏልሉ መክረማቸውን ከሪፖርተር ላይ አነበብን፡፡

ታዲያ የሚገርመው ነገር ፎርጅድ መኪኖቹን በአንበሳ አውቶብስ ስም እንዲሸቅሉ ማድረጋቸው አይደለም፡፡ አስገራሚው ነገር እነዚህ መኪኖች ሰርቪስ የሚደረጉት በመንግስት በጀት መሆኑ ነው፡፡

ሹፌሮቹም በመንግስት በጄት የተቀጠሩ ነበሩ፡፡ ምናልባትም አደጋ በሚያደርሱበትም ሰዓት የአደጋውን ወጭ ሲሸፍን የኖረውም በቀን ጆቡቹ የተወረረው ድርጅት ሊሆን ይችላል፡፡

እናም እነዚህ የግለሰብ አውቶብሶች ከአንበሳ አውቶብስ የሚለያቸው ነገር…. የአዲስ አበባን ህዝብ በገፍ እየጫኑ የሚሰበስቡትን ገንዘብ ለድርጅት ሳይሆን ለቀን ጅቦቹ የሚሰጡ መሆናቸውን ነው፡፡

በአንበሳ አውቶብስ ስም እየተንቀሳቀሱ፣ በአንበሳ አውቶብስ ስም እየታደሱ፣ በአንበሳ አውቶብስ ስም በመንግስት ሹፌር እየተነዱ፣ በአንበሳ አውቶብስ ስም ጥበቃና የመቆሚያ ቦታ እየተሰጣቸው………. ሰርተው የሚያገኙትን ገንዘብ ግን የሚያስረክቡት ለግለሰቦች ነበር፡፡

ይሄንን መረጃ ይፋ ያደረገው የአዲስ አበባው ዋና ኦዲተር የ2010 ዓ.ም የግማሽ ዓመት ሪፖርቱን ሲያቀርብ ሲሆን….. መስሪያ ቤቱ ለኦዲት ስራ ወደ አንበሳ ድርጅት በሄደበት ወቅት ሊብሬና የባለቤትነት ሰነድ የሌላቸው 120 አውቶብሶች ማግኘቱን ገልጧል፡፡

ከዚህም ጋር ተያይዞ ድርጅቱ ለቀረበለት ጥያቄ የሰነድ ማስረጃ ቀርቶ በቂ ማብራሪያ መስጠት እንዳልቻለ በሪፖርቱ ተካቷል፡፡

ከዚህ ባለፈ ደግሞ ያለምንም አገልግሎት ከ15 ዓመት በላይ በመቀመጡ የተነሳ የተበላሸ ከ29 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የመለዋወጫ እቃ በድርጅቱ መጋዘን ውስጥ ማግኘቱን ይፋ አድርጓል፡፡

የአዲስ አበባ ዋና ኦዲተር ሪፖርት በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ ከግብጽ አገር ለ21 ዳፍ አውቶብሶች በ14.2 ሚሊዮን ብር የተገዛ መለዋወጫ ስድስት ወር እንኳን ሳያስጠቅም ከጥቅም ውጭ እንደሆነና ድርጅቱም በኪሳራ የሚንቀሳቀስ መሆኑን ተናግሯል፡፡
እናም ከሪፖርቱ ተነስተን እንዲህ ለማለት ወደድን፡፡

ከድርጅቱ ባሶች ጋር የቀን ጅቦችን አሮጌ መኪና ቀላቅሎ ሲዘርፍና ሲያዘርፍ የኖረ ድርጅት ከተሳፋሪዎች የሚሰበስበውን ገንዘብ ለመንግስት ገቢ ያደርጋል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ምክንያቱም ፎርጅድ መኪና ያሰራ ተቋም ፎርጅድ ትኬት ማሳተም የሚያቅተው አይደለም፡፡

ስለሆነም ለባለፉት ዓመታት ድርጅቱን ሲመሩ የኖሩ ኃላፊዎችና በድርጅቱ ስም ሲበዘብዙ የነበሩ ግለሰቦች ተለይተው ያደረሱትን ኪሳራ እንዲከፍሉ መደረግ አለበት፡፡ ህጋዊ እርምጃም ሊወሰድባቸው ይገባል፡፡

ከዚህ ውጭ ግን በኪሳራ የሚንቀሳቀስና ያሉትን አሮጌ ባሶች ማስተዳደር ያልቻለ ‹ቀሽም ድርጅት› ሌሎች አዳዲስ ‹ባለፎቅ ባሶችን› አስገብቶ እንድሰራ መፍቀድ በአገር ሃብት ላይ የሚደረግ ምዝበራን ማበረታታት ነው፡፡ ስለሆነም ከተቻለ ድርጅቱን ለግለሰቦች መሸጥ ካልሆነም ደግሞ ድርጅቱን አፍርሶ እንደ አዲስ ማዋቀር ግድ ይላል እላለሁ፡፡

በመጨረሻም…. በአንበሳ አውቶብስ ላይ የተደረገው ኦዲት በሁሉም ድርጅቶችና መስሪያ ቤቶች ላይ ተፋፍሞ ቢቀጥል የቀን ጅቦቹ ዝርፊያና ምዝበራ ያልገባበት ተቋም ይገኛል ብሎ ማሰብ ዘበት ነው፡፡ DireTube

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram