fbpx

“አቶ ጌታቸው አሰፋን ሜክሲኮ አግኝቻቸው ነበር” ነጋ ዘርዑ

አቶ ነጋ ዘርዑ የህውሃት ታጋይ ነበሩ፤ ከዚያም ከ80ዎቹ መጨረሻ እስከ 90ዎቹ አጋማሽ የወይን ጋዜጣ ጋዜጠኛ ነበሩ። በጋዜጠኝነት ስራቸው ቃለመጠይቅ ካደረጉላቸው ሰዎች መካከል ደግሞ አንዱ አቶ ጌታቸው አሰፋ ናቸው። አቶ ነጋ ከአቶ ጌታቸው አሰፋ ጋር የነበራቸው ቆይታ ምን ይመስል ነበር? አቶ ጌታቸው እንዴት አይነት ሰው ነበሩ?

ቢቢሲ፡ አቶ ጌታቸው አሰፋን ያገኙበት ቅጽበት ምን ይመስላል?

አቶ ነጋ፡ እኔ የ”ወይን” ጋዜጣ ጋዜጠኛ ነበርኩ። ከ1986 እስከ 1996 ዓ. ም. ጀምሮ ጋዜጠኛ ነበርኩ። እኔ የምሠራው “ተጋድሎ” የሚባል አምድ ነው። “ተጋድሎ” የትግራይ ሕዝብ፣ የነባር ታጋዮች ሚሊሺያዎች ገድል ይጽፋል፣ ይተርካል። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ትግራይ ውስጥ ሦስት ልጆች ያሰለፉ የአቦይ ረታ ቤተሰብ አሉ። ከነዛ ውስጥ ሃለፎም ረታ የሚባለውን ታሪክ ለመጻፍ ሰው ሳፈላልግ የሚያውቀው ጌታቸው ነው ተባለ። ቢሮ ሄጄ አነጋገርኩት ማለት ነው።

ቢቢሲ፡ አቶ ጌታቸው ያኔም የደኅንነት ኃላፊ ነበሩ እንዴ?

አቶ ነጋ፡ አይደለም። በኋላ ላይ ነው የሆነው። እኔ ያነጋገርኩት በ1989 ዓ. ም. ግንቦት ወይም ሰኔ አካባቢ ነው። ያኔ እሱ የፌደራል ፖሊስ ውስጥ ነበረ።

ቢቢሲ፡ የያኔ ሥልጣናቸው በውል ይታወቃል?

አቶ ነጋ፡ አዎ። ይታወቃል። ፌደራል ፖሊስ ውስጥ ነው። የሐሰን ሽፋ ምክትል ነበረ።

ቢቢሲ፡ የት ተገናኛችሁ?

አቶ ነጋ፡ ሜክሲኮ አካባቢ ነው የተገናኘነው። አሁን ትልቅ ፎቅ ሆኗል።

ቢቢሲ፡ የአሁኑ የፌደራል ፖሊስ ሕንጻ ማለት ነው?

አቶ ነጋ፡ አዎ። ያኔ ዝም ብሎ [ቢሮ] ነበር። የወዲ ረታ፤ ሐለፎም ረታን ገድል ለመጻፍ ነው የሄድኩት። [ታሪኩን] እሱ ነው የሚያውቀው። በስልክ ተቀጣጥረን ሄድኩና አገኘሁት። አይገኝም ምናምን የሚባለው ነገር አሁን ነው እንጂ እንደ ማንኛውም ታጋይ እኮ ነው የነበረው። ሦስት ልጆች ስለተሰውባቸው ቤተሰብ ነበር እያወራ የነበረው። ሌሎች ታጋዮች እንደሚያደርጉት ሁሉ ቃለ መጠይቁ መሀል ላይ እያለቀሰ እየተቋረጠ ነበር።

ቢቢሲ፡ ‘አቶ ጌታቸው አሰፋ እያለቀሱ ነበር ታሪኩን የሚነግሩኝ’ እያሉኝ ነው?

አቶ ነጋ፡ አዎ። ለተሰዋው ሀለፎም አቶ ጌታቸው የቀጥታ አዛዥ ነበረ። ሀለፎም የወታደራዊ ኢንተለጀንስ ነበር። ጸባዩ እንዴት እንደነበረ፣ አገልጋይነቱ “ዴዲኬሽኑ” (መሰጠቱ)፣ ይነግረኝና መጨረሻ ላይ ውቅሮ ማራይ የተባለ አካባቢ በ79 ዓ. ም. ነበር የተሰዋው። የሱን ጀግንነት እያስታወሰ እንደ ሌሎች ታጋዮች እንባ እየተናነቀው ነበር የሚተርክልኝ። [በዚህም ምክንያት] ቃለ መጠይቁን እያቋረጥኩ ነው ያደረግኩት። በጋዜጣ ላይ ትረካውን ለማጀብ ምን ፎቶ ትሰጠኛለህ? አልኩት። ከዛ በኋላ ፎቶግራፍ ሰጠኝ። የተሰዋውን ሀለፎም ፎቶግራፍ፣ ጌታቸው ደግሞ ቁጭ ብሎ “ሳንድ ሞዴል” የሚባል የጦርነት “እንትን” እያሳያቸው ፎቶ ሰጠኝ።

ቢቢሲ፡ ፎቶው ላይ ባለታሪኩና አቶ ጌታቸው አብረው አሉበት?

አቶ ነጋ፡ አዎ አብረው ናቸው። ባለታሪኩ ቆሞ “ሳንድ ሞዴል” እያሳየ ጌታቸው እየተከታተለው ነው። ወታደራዊ ኢንተለጀንስ ስለነበረ እርምጃ ከማድረጋችን በፊት ገለጻ ይሰጣል። ጠላት የት የት እንዳለ ወታደራዊ ኢንተለጀንስ ናቸው የሚወስኑት፣ የውጊያውን [አካሄድ]። [ጌታቸው] አሁን ነው የተጋነነው እንጂኮ ያኔ እንደዛ አልነበረም። ሌሎች ከሱ በላይ ከባድ ታጋዮች ነበሩ። ብርቅ እኮ አልነበረም። አሁን ነው ብርቅ የተደረገው እንጂ።

ቢቢሲ፡ ያኔ የሰጠዎት ፎቶ ታዲያ አሁን አለ?

አቶ ነጋ፡ ፎቶግራፉ ሜጋ ኅትመት ላይ ጠፍቶብኛል። ‘ፎቶግራፉን እንዳታጠፋው አንድ ብቻ ነው ያለኝ’ ያለኝን አልረሳውም። ለሥራው “አሰርቲቭ” ነው።

ቢቢሲ፡ አሁን አቶ ጌታቸው እኚህ ናቸው የሚሉ የተለያዩ ፎቶዎች በየጊዜው ይወጣሉ። ያ ፎቶ እጄ ላይ በነበረ ብለው ይጸጸታሉ?

አቶ ነጋ፡ ያኔ እኮ [ጌታቸው] የሚካበድ ነገር አልነበረውም። እኔ አሁን ነው ሲካበድ የሰማሁት። እንደ ዕድለኛ አይደለም እራሴን የምቆጥረው። አጋጣሚ ነው። ከሱ የበለጠም ስንት [ታጋዮች] አግኝቻለሁ።

ቢቢሲ፡ አሁን በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን የሚወጡ ፎቶዎች የትኛው ነው ትክክለኛ?

አቶ ነጋ፡ አሁን የሚወጡት ፎቶዎች ይሄ ነው ይሄ ነው ለማለት አልችልም። ልነግርህ የምችለው እሱን በዐይኔ አይቸዋለሁ።

ቢቢሲ፡ ብዙዎች የአቶ ጌታቸው አሰፋ ስም ሲጠራ አዕምሯቸው ውስጥ የሚመጣ ምሥል አለ። የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ ደግሞ እርስዎ አቶ ጌታቸውን አይቻቸዋለሁ ከሚሉ በጣት የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን አንዱ ነዎት። አቶ ጌታቸው አጭር ናቸው ረዥም? ወፍራም ናቸው፣ ቀጭን?

አቶ ነጋ፡ ኧረ እኔ ትዝ አይለኝም ይሄ። ታጋይ መሆኑና ከሕጻንነቱ ጀምሮ በትግል ያሳለፈ፤ ለትግል ሲባል የግል ኑሮውን ራሱ መስዋዕትነት የከፈለ፣ አንድ ቀን እንኳን ራሱን ከትግል [ገሸሽ አድርጎ] የማያውቅ። ጀግና ቆፍጣና፤ እንደ ሁሉም ታጋይ የሚጋራው ባህሪዎች አሉት። አርበኝነት “ዴዲኬሽን” (መሰጠት)፣ መስዋዕትነት መክፈል የመሳሰሉት። መልኩ ይሄ ነው ይሄ ነው አልለውም። ታጋይነቱን ነው።

ቢቢሲ፡ ከወቅቱም አንጻር አሁን ቁመናቸውን ተክለ ሰውነታቸውን መግለጽ ትንሽ አስጊ ሊሆን ይችላል። ግን እንደው ምን ለብሰው ነበር? ዘናጭ ናቸው? ስለርሳቸው ምን ሊነግሩን ይችላሉ? በወቅቱስ እንዴት አስተናገዱዎት?

አቶ ነጋ፡ በቃ እኮ በጣም ነው ያስተናገደኝ አልኩህ። . . . እኔም ታጋይ ነኝ እሱም ታጋይ ነው። ታጋይ ለታጋይ በጣም ይተዋወቃል። ያለምንም “ሪዘርቬሽን” (ገደብ) ነው የምንገናኘው። ስንወያይም እንደዛ ነው። ስንቀራረብም “ሪዘርቬሽን” (ገደብ) የሚባል ነገር የለም። በጣም ትሁት ነው።

ቢቢሲ፡ ሻይ ቡና ጋበዝዎት?

አቶ ነጋ፡ (ረዥም ሳቅ) እንዴት ነው እንዴ? እንደ ሰው አታስበውም እንዴ? ችግሩ እኮ እንደዛ ነው። እኔ እንደ ማንኛውም ታጋይ ነው እያልኩህ ነው። አንተ ግን የሆነ ነገር እያስመሰልከው ነው። አይደለም በቃ። እንደ ታጋይ ቁጠረው። . . . ቁጠረው።

ሌላው ሰው ነው ያካበደው እንጂ ታጋይ ነው በቃ። የትግራይ ሕዝብ ታጋይ ሲባል ማለት ነው። [ምን አይነት ሰው ሊሆን እንደሚችል] ማንም ሰው ይገባዋል። ታጋይ የሆነም ሰው ታጋይ እንደሆነ ይገባዋል። ግልጽ ነው። ታጋይ ሲባል “ቫሊዩዎች” (መርሆች) አሉት። አይሰርቅም። አይዋሽም። 24 ሰአት ሙሉ ይሠራል። የሚሆነው ነገረ እንዳይሆንበት የሚጥር… የማይሆነውን ደግሞ አይሞክረውም። ይሄ ነው ታጋይ ማለት።

ቢቢሲ፡ አሁን የእሰር ማዘዣ ወጥቶባቸዋል ስለሚባሉ ነገሮች ሲሰሙ፣ በማኅበራዊ ሚዲያ በጣም አስፈሪ ሆነው ሲሳሉ እርስዎ ላይ ምን ዓይነት ስሜት ይፈጥርብዎታል?

አቶ ነጋ፡ በቃ. . . ማለት እኔ የማውቀው አይደለም ወይ? እሱ አይደለም ወይ? ሌላ አይነት ተፈጠረ እንዴ? [እያልኩ አስባለሁ]። ከዛ በኋላም እኮ. . . አየዋለሁ። ብዙ ጊዜ ይታያል እኮ። እንደማንኛውም ሰው እኮ ይታያል። ይሄን ዓይነት ነገር የሚፈጥሩ. . . ለምንድነው እንደዛ የሚሆነው?

አሁን የሆነ አንድ ቡድን ከውስጥ ሆኖ ኢህአዴግን አዳክሞ ስልጣን የያዘ ቡድን አለ። ኢህአዴግ ይሁን አይሁን የማይታወቅ ማለት ነው። እኔ በኢህአዴግ ውስጥ “ከለር ሪቮሉሽን” (የቀለም አብዮት) ተካሂዷል ባይ ነኝ ። ሥርዐት ያልቀየረ “ከለር ሪቮሉሽን” ተካሂዷል ባይ ነኝ። ያን “ከለር ሪቮሉሽን” ያካሄደ ሰው ከውስጥም ከውጪም ሲመሳጠር እንደነበረ የታወቀ ነው። ይሄ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ግልጽ ሊሆን ይገባል።

ከውስጥም ከውጪም ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር እንደተመሳጠረ ማንም አይክደውም። ምናልባት እሱ ነው ምስጢራችንን የሚያውቀው ብሎ. . . ያደረገው ለዚህ ነው። ሌላ አይደለም። ስለዚህ እኔ በአንድ ሰው ላይ ሲስተም እያለ በአንድ ሰው ላይ ይሄ ነው ይሄ ነው ብሎ እንደ . . . እንትን ማለት በራስ አለመተማመን ነው። የያይዘከው ስልጣን ራሱ የያዝከው መሆኑን አለማመን ነው። አያምኑንም። ቤተ መንግሥት የእውነት ገብተናል ወይ? በእውነት ሥልጣን ይዘናል ወይ? የመተዳደሪያ ግልጽ የሆነ ፖሊሲም የላቸውም። የአጭር ጊዜ የረዥም ጊዜ ምንድን ነው የምንሆነው? ወዴት እየሄድን ነው? ሀገሪቱ ወዴት እየሄደች ነው? ማነው ጠላት ማነው ወዳጅ የሚባለው? . . . በቃ እኮ አንድ ሰው አጀንዳ እየፈጠሩ፤ ትኩስ ዜናዎች እየፈጠሩ ከአንዱ ወደ አንዱ ቦታ እየተንቀሳቀሱ በቃ ማሳለፍ ነው። እኔ የጦርነት አውድማ እያስመሰሉ ሀገሪቱን። ወዳጅ የነበረ ሕዝብ. . . በማያውቀው እንደዚህ ጠላትህ ነው። ጠላት “ዲፋይን” እያደረጉ እያቀበሉ ሥልጣን ለማራዘም የሚጠቀሙበት ጉዳይ እንጂ ታጋይ ታጋይ ነው። እኔም ታጋይ ነኝ። ጌታቸውም ታጋይ ነው። “ኤቭሪባዲ ወዝ ታጋይ በቃ”። አንድ ነን ሁላችንም ማለት ነው። የነሱ ሸር ነው።

ቢቢሲ፡ አንድ የመጨረሻ ጥያቄ ላንሳ፤ ያኔ ሜክሲኮ አካባቢ ስትገናኙ አቶ ጌታቸው ኮፍያ አድርገው ነበር?

አቶ ነጋ፡ ኮፍያ ማድረጉ ስለምናምን ማድገሩ “ኢረለቫንት” (እርባና ቢስ) ጥያቄ ነው የሚመስለኝ።

ቢቢሲ፡ በፎቶ ስለማይታወቁ ሕዝብ ማወቅ የሚፈልገውን ነው የምጠይቅዎት።

አቶ ነጋ፡ (ሳቅ) በቃ ተወው። ይሄ ጥያቄ ይቅርብህ። ምንም የምመልሰው አይደለም። ይሄ አይጠቅመኝም ተወው አልኩህ። ለኔ ትርጉም የሚሰጠኝ አይደለም።

BBC Amharic

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram