fbpx

አትሌት ብርቱኳን አደባና እዮብ አለሙ ለ4 ዓመታት ከሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች ታገዱ

አትሌት ብርቱኳን አደባ እና አትሌት እዮብ አለሙ ለ4 ዓመታት ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች ላይ እንዳይሳተፉ መታገዳቸውን የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሁለቱ አትሌቶች የተከለከለ መድኃኒት በመጠቀም የህግ ጥሰት በመፈፀማቸው ነው የኢትዮጵያ ብሄራዊ የፀረ አበረታች ቅመሞች ጽህፈት ቤት ውሳኔ ያሳለፈባቸው።

በዚህም መሰረት አትሌት ብርቱኳን አደባ በሪሁን በሻንጋይ ዓለም አቀፍ ማራቶን ውድድር ላይ “ኤግዞጂንየስ ስቴሮይ” የተባለ የተከለከለ መድሃኒት መጠቀሟ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ህዳር 13 2016 በተደረገባት ምርመራ ተረጋግጧል።

ይህንን ተከትሎም አትሌት ብርቱኳን አደባ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከሰኔ 22 2017 እስከ ሰኔ ሰኔ 22 2021 ድረስ ለ4 ዓመታት ማንኛውም ውድድር ላይ እንዳትሳተፍ እድግ ተጥሎባታል።

አትሌት እዮብ አለሙ ወልደጊዮርጊስም በቻይና ሎንግኮው በተካሄደ የማራቶን ውድድር ላይ ኢ.ፒ.ኦ የተባለ የተከለከለ አበረታች መድኃኒት መጠቀሙ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ጥቅምት 29 2017 በተካሄ ምርመራ ታውቋል።

ይህንን ተከትሎም አትሌት እዮብ አለሙ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከየካቲት 05 2018 እስከ የካቲት 05 2022 ለተከታታይ 4 ዓመታት ከማንኛውም አትሌቲክስ ውድድር ላይ እንዳይሳተፍ እድግ ተወስኖበታል።

በዚህም መሰረት አትሌት ብርቱኳን አደባና እዮብ አለሙ ለቀጣይ 4 ዓመታት በሀገር አቀፍ፣ ዓለም አቀፍና በሌሎችም ማናቸውም ስፖርታዊ ውድድሮች ላይ የማይሳተፉ ይሆናል።

ጽህፈት ቤቱ በቀጣይም የተጀመረውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ በመቀጠል በተለይም በየደረጃው የምርመራና ቁጥጥር ተግባራትን በማከናወን የህግ ጥሰት በሚፈፅሙ አካላት ላይ አስተማሪ የሆኑ እርምጃዎችን የሚወሰድ መሆኑን አስታውቀዋል።

ሁሉም ባለድርሻ አካላትም በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ የበኩላቸውን ገንቢ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ጥሪውን አስተላልፏል።

ጽህፈት ቤቱ ከዚህ ቀደም የተከለከለ መድኃኒት በመጠቀም የህግ ጥሰት የፈፀመውን አትሌት አሊ አብዶሽን ለ4 ተከታታይ ዓመታት በማነኛውም ሀገራዊም ይሁን ዓለማቀፋዊ ውድድሮ እንዳይሳተፍ ቅጣት ማሳለፉ ይታወሳል።

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram