fbpx

HT

ሐበሻ ታይምስ ሚዲያ

AMHARIC

[አስደንጋጭ] የደራሲ ይስማዕከ ሚስት፣ ”ስቃይና ብሶቴን ስሙኝ” ትላለች

የደራሲ ይስማዕከ ሚስት፣ ”ስቃይና ብሶቴን ስሙኝ” ትላለች

  • “ሁለት ልጆቼን የማበላቸው አጥቼ ተቸግሬአለሁ”
  • “ህይወቴ በአደጋና በስጋት የተሞላ ነው”

የ27 ዓመቷ ወ/ሮ ፀጋ አንዳርጌ ምህረት፣ የዕውቁ ደራሲ ይስማዕከ ወርቁ ባለቤት ናት፡፡ በ1998 ዓ.ም መተዋወቃቸውን የምትናገረው ወ/ሮ ጸጋ፤ ለ12 ዓመታት በትዳር መኖራቸውንና አንድ ወንድና አንዲት ሴት ልጅ ማፍራታቸውን ትገልጻለች፡፡ ሆኖም የደራሲነት ዝናው እየጨመረ ሲመጣ ውጭ ውጭ ማለት እንደጀመረ የምታስረዳው የደራሲው የትዳር አጋር፤ አንድ ልጅ ከወለዱ በኋላ ተለያይተው እንደነበር ትገልጻለች፡፡ ጥንዶቹ ዳግም የተገናኙት ይስማዕከ የመኪና አደጋ ከደረሰበት በኋላ መሆኑን ወ/ሮ ጸጋ ተናግራለች፡፡ ሁለተኛ የአብራካቸው ክፋይ የተወለደችውም በዚህ ጊዜ ነው ትላለች፡፡

ይሁን እንጂ ባላሰብኩት ሰዓት እኔንና ሁለት ህጻናት ልጆቻችንን ባዶ ሜዳ ላይ ጥሎን በመሰወሩ፤ በአሁን ሰዓት ለልጆቼ ቀለብ መግዣ አጥቼ የከፋ ችግር ላይ እገኛለሁ ብላለች – አዲስ አድማስ ዝግጅት ክፍል ድረስ መጥታ ብሶቷን የነገረችን ወ/ሮ ፀጋ አንዳርጌ፡፡ ደርሶብኛል የምትለው በደል ግን ይሄ ብቻ አይደለም፤ እስከ ዛሬ መልካም ስሙንና ዝናውን እንዳላጎድፍበት ብዬ ሲያደርስብኝ የቆየውን ግፍ ደብቄ ቆይቻለሁ የምትለው የደራሲው ባለቤት፤ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ጋር ባደረገችው ቃለ ምልልስ ከዚህ በኋላ የመጣው ይምጣ ብላ የደረሰባትን ሁሉ አፍረጥርጣ ተናግራለች፡፡ እነሆ ከዚህ በታች ቀርቧል፡፡

ጉዳዩን ለማጣራት ለደራሲ ይስማዕከ ወርቁ በሞባይል ስልኩ የፅሑፍ መልዕክት (ቴክስት ሜሴጅ) ልከን “የኮሚቴው ኃላፊ ሽመልስ አበራ ጆሮ ስለሆነ በእነሱ ፊት አነጋግሪኝ” በማለት ምላሽ ቢሰጥም በኮሚቴው በኩል ልናገኘው ያደረግነው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

ከይስማዕከ ወርቁ ጋር እንዴትና መቼ ተዋወቃችሁ?

ከይስማዕከ ጋር የተዋወቅነው በ1998 ዓ.ም እኔ የአንደኛ ደረጃ፣ እሱ የሀይስኩል ተማሪ እያለን ነው። የተዋወቅነውም ቤት ተከራይቶ፣ እኛ ጎረቤቶች ቤት ከገባ በኋላ ነው፡፡ ለአንድ አመት ብቻ በጓደኝነት ከቆየን በኋላ በአንድ ቤት ውስጥ አብረን መኖር ጀመርን። በጥሩ ፍቅር ስንኖር ቆይተን፣ በድርሰቱ እውቅናና ገንዘብ ማግኘት ሲጀምር፣ በሰው ሲታጀብ፣ ከመጠን በላይ መጠጣት መስከር፣ እኔንም መደብደብና ማሰቃየት ጀመረ፡፡ ይባስ ብሎ ባመሸበት ማደር፣ ለትዳሩ ታማኝ አለመሆን ጀመረ፡፡ ብዙ ስቃይና ጭቆና ውስጥ ነው የኖርኩት፡፡ ስልክ ማናገር፣ ከጓደኛና ከቤተሰብ ጋር መገናኘት አልችልም ነበር፡፡

ግን እኮ ይስማዕከ በስራው እውቅናና ዝናን ካገኘ ቆይቷል፡፡ በእነዚያ ጊዜያት ጭቆናና በደል ሲያደርስብሽ እንዴት ዝም ብለሽ ተቀመጥሽ?

እኔ ያገባሁት ለዝና ብዬ አይደለም፤ ገና ተማሪ እያለ ሳይታወቅ ነው፤ ይወደኝ እውደው ነበር፡፡ ማሰቃየትና መበደል ሲጀምር፣ ብዙ ጊዜ ከቤት እየወጣሁ ቤተሰቤ ዘንድ እሄድ ነበር፡፡ ከዚያ ሽማግሌ እየላከ ይቅርታ እየጠየቀ፣ መልሶ ይወስደኛል፡፡ ቤተሰቤም፤ “እስኪ ታገሺው፣ ይሻሻል ይሆናል” ብለው ይልኩኛል፡፡ በዚህ መልኩ አብረን ቆየን፡፡ ሀብትና ንብረትም አፈራን፡፡ ወንዱን ልጃችንን ወለድን፡፡ እኔም ብዙ ውክልናዎችን በመውሰድ፣ በመፅሐፎቹ ሥራ፣ በማተሚያ ቤቱ አብሬው እሰራ ነበር፡፡ በመሀል ብዙ ስቃዮችን፣ ድብደባዎችን ሲያደርስብኝ፣ በቃ ይሄ ነገር ለህይወቴ ያሰጋኛል በሚል ፍቺ ጠየቅሁኝ፡፡ ጉዳዩ ገና በፍርድ ቤት እያለ፣ ሀዋሳ ላይ ጠጥቶ ከሌላ ሴት ጋር አምሽቶ ሲያሽከረክር፣ ያው አገር የሚያውቀው፣ የመኪና አደጋ ደረሰበት፡፡

እኔም ይህን ያህል ጊዜ አብሬው ኖሬያለሁ፤ የልጄ አባት ነው ብዬ፣ ሁሉን ትቼ፣ እሱን ማስታመም ጀመርኩ፡፡ ይህንንም ወዳጅ ዘመድ ያውቃል፡፡ ሌሊት ቀን ሳልል አስታመምኩት፣ ዳነ፡፡ ተሻለውና ያንን ረስቼ፣ አብሬው መኖር ጀመርኩ፡፡ እንደገና ሁለተኛዋ ህፃን ተወለደች፡፡ አሁን ዘጠኝ ወሯ ነው፡፡ ታሞ ከተሻለው በኋላ፣ እኔ ህፃኗን እርጉዝ ሆኜ፣ መልሶ መደብደብ ማሰቃየት ጀመረ፡፡ እርጉዝ ሆኜ ሆዴን ረግጦኝ፣ ብዙ እንገላቶኝ፣ ከሞት ተርፌያለሁ፤ የህፃኗ መትረፍ ራሱ ተዓምር ነው፡፡ ከተወለደች በኋላ ያው ስቃዩን ችዬ መኖሬን ቀጠልኩ፡፡ ለልጆቹ ሥል ነበር ስቃይ የማየው። ከዚያ የፋሲካ በዓል መጋቢት 30 ሊሆን፣ መጋቢት 28 ቀን ፋሲካን ሀዋሳ እናሳልፍ ብሎ ከእነ ልጆቼ ይዞኝ ሄደ፡፡ ይታይሽ ለልጆቹም ለእኔም ለበዓል የሚሆን ልብስ ብቻ ነው የያዝኩት፡፡ እዛ እንደሄድን እኔም ቤተሰቤ ጋ፣ እሱም እህቱ ጋ ገባ፡፡ የበዓል ቀን ልጆቼን አለባብሼ፣ እሱ ቤተሰብ ጋ ስሄድ፣ ሊያናግረኝም ሆነ ልጆቹን ሊያይ ሁሉ አልፈለገም፡፡

ለምን? ምን ተፈጠረ?

ምን አውቃለሁ?! ፊት ሲነሳን፣ ልጆቼን ይዤ፣ ወደ ቤተሰቤ ተመለስኩ፡፡ እኔ እጠብቅ የነበረው፣ ኩርፊያው አልፎለት፣ ወደ አዲስ አበባ እንመለስ እስኪለኝ ነበር፡፡ ዝምታ ሲበዛና ስጠይቅ፣ ተደብቆ ወደ አዲስ አበባ መምጣቱን ተረዳሁ፡፡ እኔም ልጆቼን ይዤ ተመለስኩ፤ ግን የተከራየነውን ቤት ለቅቆ፣ የት እንደገባ ማወቅ አልቻልኩም፡፡

የት ነበር የምትኖሩት?

አራት ኪሎ ባሻ ወልዴ ችሎት ነበር፡፡ ከእነቤት እቃው፣ የኔንም የልጆቼንም ልብስ፣ የልጆች መኝታና መጫወቻ ሁሉ ሳይቀር የለም፡፡ ከዚያም እኔም የምሰራበት፣ የምንተዳደርበት ማተሚያ ቤት ስሄድ፣ ማሽኖቹን የት እንዳደረሳቸው አላውቅም፡፡ የማተሚያ ማሽኖቹ 13 እና 14 ሚ. ብር እንደሚያወጡ ባለሙያዎች ነግረውኛል፡፡ እንዲህ ከሆነ አሁን ሦስት ወር ሊሆነን ነው፣ ለልጆቹ ቀለብ የለ፣ አይጠይቃቸው፣ የት እንዳለ አይታወቅ፤ ራሱን ሰውሯል፡፡ ነገር ግን በኢቢኤስ ቴሌቪዥን፣ በሰይፉ ሾው ቀርቦ፣ መናገር አልችልም ሲል ስሰማ፣ ማመን ነው ያቃተኝ፡፡

ለምን ማመን አቃተሽ?

አንደኛ፤ ጥቁር አንበሳ ለመጨረሻ ጊዜ ለቼክአፕ ሲሄድ አብሬው ነበርኩ፡፡ ዶክተሮቹ፤ “በደንብ ማስታወስ ትችላለህ፣ የረሳኸው ነገር የለም፤ ስፒች ቴራፒው አሪፍ ሆኖልሃል፣ መናገር ችለሃል፤ ወደ ውጭ የሚያስኬድ ነገር የለም” ሲሉት አብሬው ሆኜ ሰምቻለሁ፡፡

ከዳነ በኋላ አብሬው ኖሬያለሁ፤ በደንብ ያወራል፡፡ ብቻ አልፎ አልፎ ይጥለዋል፤ ይህም የሚሆነው መጠጥ ከጠጣና ከተበሳጨ ብቻ ነው። እንደሚናገርና በጣም ሰላም እንደሆነ፣ አብረውት ያሉ፣ የእርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴ ነን የሚሉት ታዋቂ አርቲስቶችና ጓደኞቹ በደንብ ያውቃሉ፡፡ ይሄን ገንዘብ ለመሰብሰብ ነው እንዴ ከኔና ከልጆቹ የተሰወረው? እያልኩ፣ ይሄው ከእነ ልጆቼ በችግር ላይ ወድቄያለሁ፡፡

ለሶስት ወር ያህል አብራችሁ እንዳልኖራችሁ ነግረሽኛል፡፡ ምናልባት በዚህ መሃል እንደገና ታምሞ መናገር ተስኖት ቢሆንስ?

በደንብ እንደሚናገር አውቃለሁ፡፡ ከኮሚቴው ከሌሎች ሰዎች ጋር በውጭ ህክምና ዙሪያ ገንዘብ የማሰባሰቡ ሴራ የተጠነሰሰው በስልክ ነው፡፡ ይሄንን በቀኑና በወቅቱ፣ ከቴሌ ድምፁን ማስወጣት ይቻላል፡፡ ከእህቱ ጋር ሆነው፣ እኔንም በስልክ አስፈራርተውኛል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ከጎኔ ሆኖ የሚረዳኝ በማጣቴ፣ ልጆቹንም ለማንም ሰጥቼ መንቀሳቀስ ስላቃተኝ እንጂ ስለመናገሩ በደንብ ማስረጃ አለ፡፡ ህሊናቸውን ካልካዱ በስተቀር አሁን ከጎኑ ሆነው ገንዘብ ለመሰብሰብ የሚሯሯጡትና ሰይፉ ሾው ላይ ቀርቦ፣ የእሱ አፍ የሆነው፣ ፈሪያት የሚባለው ጓደኛውም፣ በደንብ ያውቃል፡፡

አሁን አንቺ የት ነው የምትኖሪው?

ሐዋሳ ቤት ነበረን፤ አብረን ያፈራነው ቤት ነው። እርግጥ ለመኖሪያ ቤት ሳይሆን ለሆቴልነት ነበር አሰራሩ፡፡ አሁን እዛ ቤት ነኝ፡፡ ፊት ለፊቱ መስታወት ነው፤ እኔም ልጆቹን ይዤ እዛ ሜዳ ላይ ነው ያለሁት፡፡ እዛም የገባሁት በእህቱ በኩል ቤቱን ሊሸጥ ሲያስማማ፣ ቁልፍ ስለነበረኝ፣ ከፍቼ ገብቼ እንዳይሸጥ አሳገድኩት፡፡ አሁን አንዳንዴ አባቴ፣ አንዳንዴ ወንድሞቼ እየጠበቁኝ ነው የማድረው፤ በጣም ስጋት ላይ ነኝ፡፡ እህቱ አገሬ እሸት ትባላለች፡፡ ከቤቱ ጎትተው እንዲያስወጡኝ ለፖሊሶች ነግራቸው ነበር፡፡ ህጋዊ ሚስቱ መሆኔን ሲያውቁ፣ አርፈሽ ተቀመጪ አሏት፡፡

እስከ ዛሬ የበደለኝን፣ ያደረሰብኝን ጭቆናና ስቃይ የቻልኩት፣ በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ የገነባው መልካም ስምና ዝና እንዳይበላሽ ብዬ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ አንድ ነገር ያደርገኛል፣ ገና በወጣትነቴ ቢገድለኝ፣ ለቤተሰቤም ለልጆቼም አጎድላለሁ ብዬ ነው፡፡ አሁን ግን ችግሩ ባሰብኝ፤ ልጆቼን የማበላው አጣሁ፡፡ ሜዳ ላይ ወደቅኩኝ፡፡ ከዚህ በኋላ የፈለገው ይምጣ ብዬ ነው፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ጉዱን እንዲሰማ ወደ እናንተ የመጣሁት፡፡ ቅድም መናገር ባይችልስ? ብለሽኛል። መናገር መቻል አለመቻሉ፣ ትዳሩን ለመበተንና ልጆቹን ያለ ቀለብ ሜዳ ላይ ለመጣል ምክንያት አይሆንም፡፡ ከኔ ተደብቆ መጥቶ፣ ከሌላ ሴት ጋር ነበር የሚኖረው፡፡ ከሌላ ሴት ጋር ህይወት መስርቶ፣ ለእኔ ግን በምወዳቸውና በማከብራቸው ሰዎች በኩል፣ የፍቺ ወረቀት ላከልኝ፡፡ ለመሆኑ በጋብቻ ላይ ጋብቻ፣ የአገራችን ህግ ይፈቅዳል?

ህጋዊ የጋብቻ ፊርማ አላችሁ?

አዎ! ወንዱን ልጄን እስካረግዝ ድረስ አብረን እንኖር ነበር እንጂ አልተፈራረምንም ነበር፡፡ ወንዱን ልጄን እርጉዝ ስሆን ተፈራረምን፡፡ ህጋዊ ጋብቻ አለን፡፡ የሚገርምሽ ሃዋሳ የመኪና አደጋ ሲደርስበት፣ ከሌላ ሴት ጋር ነበር፡፡ መቼም በዚያ ሌሊት ከእህቱ ጋር አልነበረም፡፡ ከዚያም በፊት ለትዳሩ ታማኝ አልነበረም፡፡ ይሄን ሁሉ የኢትዮጵያ ህዝብ አውቆት፣ ከዚህ በኋላ ብሞትም አይቆጨኝም፡፡ የኢትዮጵያም ህዝብ መጭበርበር የለበትም፡፡ የሚገርምሽ ለገንዘብ ማሰባሰቢያ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተከፈተው አካውንት ውስጥ 400 ሺህ ብር መግባቱን አረጋግጫለሁ፡፡ ህዝቡ እየተጭበረበረ ነው፡፡ እኔም ከዚህ አካውንት ገንዘብ እንዳይወጣ አሳግጄዋለሁ፡፡ እርግጥ ነው እሱ እኔን ለማጥፋት ከመሞክር ወደ ኋላ አይልም፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለመንግስትም ለኢትዮጵያ ህዝብም ህይወቴ በአደጋና በስጋት የተሞላ መሆኑን መናገር እፈልጋለሁ፡፡ እህቱ በየቀኑ ሀዋሳ የተለያዩ ሰው እየላከች፣ እንዲያስፈራሩኝ እያደረገች ነው፡፡ እኔ እንኳን ብሞት፣ ልጆቼን መንግስትና ህዝብ እንዲጠብቅልኝ አደራ እላለሁ፡፡

የፍቺ መጥሪያ ከደረሰሽ በኋላ ፍ/ቤት ቀረብሽ?

ቀጠሮው ለግንቦት 3 ቀን 2010 ዓ.ም ነበር፤ እኔ ቀረብኩ፣ እሱ የለም፡፡ በመሃል ለሁለተኛ ጊዜ ቀረብኩ፤ አሁንም የለም፡፡ እኔ በመሃል ይግባኝ ብዬ ነበር፡፡ እሱ ስላልቀረበ ፒያሳ የሚገኘው፣ አራዳ ምድብ ችሎት፣ ለሰኔ 26 ፍ/ቤቱ ቀጠሮ ሰጥቶኝ፣ እየተጠባበቅሁ ነው። የይሰማዕከን በደልና ግፍ በተመለከተ፣ ባሻ ወልዴ ችሎት፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሄደሽ ብትጠይቂ፣ ይነግሩሻል፡፡ የሴቶች ጉዳይ አመልክቼ፣ እንረዳሻለን ካሉኝ በኋላ፣ እሱ መሆኑን ሲያውቁ፣ ጉዳዩን ችላ አሉት፡፡ አሁን በኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር በኩል፣ የህግ ድጋፍ ለማግኘት እየጣርኩ ነው፡፡

ለመሆኑ አሁን ምን እየሰራሽ ነው የምትኖሪው?

ምንም እየሰራሁ አይደለም፡፡ እንደምታይው፣ እዚህ አንቺን ለማግኘት ስመጣ እንኳን፣ እነዚህን ህፃናት ይዤ ነው፡፡ ወንዱ 2 አመት ከሰባት ወር፣ ሴቷ 9 ወሯ ነው። ለማን ጥያቸው እመጣለሁ? ለማንስ ሰጥቻቸው ስራ እፈልጋለሁ? የምሰራውና የምንተዳደረው በማተሚያ ቤቱ ነበር፡፡ የማተሚያ ቤቱን እቃዎች ወዴት እንዳሸሻቸው አላውቅም፡፡ አንቺ ልጆች ይዘሽ ዳቦ ሲሉሽ ማቅረብ ካልቻልሽ፣ በቃ በህይወት እንደሌለሽ ቁጠሪው፡፡ አሁን ላይ ይህን ጉድ የሰሙ ሰዎች፤ መቶም ሁለት መቶም፣ አስርም ብር እየሠጡኝ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ሦስት ወር ሊሞላኝ ነው፡፡ የሚገርምሽ በፊትም ባሻ ወልዴ ችሎት እያለን፣ የተሟላ የቤት እቃ ያለበት ቤት ውስጥ ነበር የምንኖረው፡፡ ግን ለቤቱና ለልጆቹ አስቤዛ እንኳን አይገዛም፤ ስሙን ለማጥፋት አይደለም፤ በረሃብ ሲቀጣን ነው የኖረው፡፡ አሁን የሚደርስብኝን ለመቀበል ለመሞትም ጭምር ዝግጁ ነኝ፡፡ ሁሉም ግን በግልፅ መውጣት አለበት፡፡ ዝና ወዲህ ተግባር ወዲያ ነው፣ የእሱ ጉዳይ፤ ስለሆነም የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎኔ ይቁም፡፡

የህግና የፍትህ አካላት ድጋፍ እሻለሁ፡፡ በእህቱ በኩል የሚልክብኝን ዛቻና ማስፈራሪያ፣ ፖሊስ እንዲያስቆምልኝ እፈልጋለሁ፡፡ በጣም አንገብጋቢው ጉዳይ፣ የዕለት የሚሆን የልጆች ቀለብና ተያያዥ ወጪዎች ያስፈልጉኛል፡፡ ይህን በማጋለጤ ህይወቴ አደጋ ላይ እንደሚወድቅ አውቃለሁ፡፡ ለሚደርስብኝ ሁሉ ሀላፊነት የሚወስደው እሱና በሱ ዙሪያ ያሉ፣ ጋሻ ጃግሬዎቹ እንደሆኑ፣ አበክሬ መናገር እፈልጋለሁ፡፡ ፍትህ እሻለሁ፡፡

ምንጭ፡- አዲስ አድማስ

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram