fbpx
AMHARIC

‹‹አስመራ ድረስ በእግራችሁ መሄድ ትፈልጋላችሁ?››

‹‹አስመራ ድረስ በእግራችሁ መሄድ ትፈልጋላችሁ?›› | አሳዬ ደርቤ በድሬቲዩብ

ኤርትራ ለመሄድ ሽር-ጉድ እያልኩ ነው፡፡

የአውሮፕላን ትኬት መግዣ ዋጋው የቱንም ያህል ቢወደድም አያሳስበኝም፡፡ ምክንያቱም ወደ ኤርትራ የምሄደው በእግሬ ነው፡፡

ወደ አስመራ የማደርገውን ጉዞ በእግሬ እንዲሆን የመረጥኩት ከዚህ በፊት የገባሁትን ቃል ለመጠበቅ በማሰብ ነው፡፡ ከረዥም ዓመታት በፊት ‹‹ሁለቱ አገሮች የታረቁ እለት ከኢትዮጵያ እስከ ኤርትራ ድረስ በእግሬ እጓዛለሁ›› በማለት ቃል ገብቼ ነበር፡፡

እናም ይሄንን ቃሌን ለመጠበቅ ስል እነ ያሬድ ሹመቴ በየዓመቱ አድዋ ተራሮች ድረስ በእግራቸው በመጓዝ የአባቶቻችንን ገድል እንደሚያስቡት ሁሉ እኔም በእግሬ እስከ ኤርትራ ድረስ ለመጓዝ ቆርጫለሁ፡፡

በዚህም የተነሳ በባለፈው ከአዲስ አበባ እስከ ኤርትራ ያለውን ርቀት ለማወቅ መረጃዎችን አገላብጬ ነበር፡፡ እናም ከተወሰነ ፍለጋ በኋላ 1080 ኪ.ሜ የሚል አስደንጋጭ መረጃ አገኘሁ፡፡

ለካ ወንዴ ማክ የሚባለው ሙዚቀኛ ‹‹ሺ ሰማንያ ጠብቂኝ›› በማለት የዘፈነው ‹‹አስመራ ላይ ጠብቂኝ›› ለማለት ኑሯል፡፡

አርቲስቱ የዘፈኑን ግጥም እንዲህ የመሰጠረው በጊዜው የነበረውን ጨቋኝ ስርዓት ፈርቶ ቢሆንም ሙዚቃው ሲለቀቅ የአስመራ ኮረዶች አገራቸውን ለቅቀው ወጥተው ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ‹‹ሺ ሰማንያ ጠብቂኝ›› በማለት የዘፈነላትን ልጅ ያገኛት አስመራ ላይ ሳይሆን ሰንጋ-ተራ አካባቢ ነው እየተባለ ሲወራ ሰምቻለሁ፡፡

ይሄን ብዬ ወደ ዋናው ሃሳቤ ስመለስ ከአዲስ አበባ እስከ ኤርትራ ያለውን 1080 ኪ.ሜ ለመጨረስ የሚያስፈልገውን ጊዜ ሳሰላው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ለመቋጨት ከፈጀው ጊዜ በላይ የሚወስድ መሆኑን ደረስኩበት፡፡

እንደምንም ተሟሙቼ በቀን 25 ኪሎሜትር ብጓዝ እንኳን ወደ 45 ቀን ገዳማ ይፈጃል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ እኔ ጉዞየን ሳልጨርስ በፊት ሁለቱ አገሮች ፍቅራቸውን ጨርሰው ሌላ ጦርነት ሁሉ ሊጀምሩ ይችላሉ ማለት ነው፡፡

እናም ይሄንን ስጋቴን ያጫወትኩት ጓደኛዬ ‹‹ቃል የገባኸው ከየት እስከ የት ድረስ በእግሬ እጓዛለሁ ብለህ ነው?›› በማለት ጠየቀኝ፡፡

‹‹ከኢትዮጵያ እስከ ኤርትራ››

‹‹ታዲያ እንደዚያ ከሆነማ ከአንተ የሚጠበቀው ድንበሩን በእግርህ ማቋረጥ ነው እኮ!›› በማለት ጉዞዬን ሊያቃልልኝ የሞከረ ቢሆንም የራሴን ቃል ማቃለሉና መሸንገሉ አልተዋጠልኝም፡፡ ባይሆን ቃል የገባሁት ወሎ ላይ ሆኜ በመሆኑ ከአዲስ አበባ እስከ ደሴ ያለውን መንገድ በካቻማሌ ባቋርጠው ክፋት የለውም ብዬ አሰብኩ፡፡

እናም ጉዞዬን እውን ለማድረግ ርሃብን ባህል በማድረግ የቆጠብኳትን ጥቂት ገንዘብ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የዓመት እረፍቴን ደግሞ ከመስሪያ-ቤቴ አውጥቼ ወደ ቤቴ በመምጣት እቅዴን ለእሜቴ ስነግራት ያላሰብኩት ዱብ-እዳ ተፈጠረ፡፡

ቁርጥ ባለ ቋንቋ ‹‹ይሄን ያህል ገንዘብ በዋል-ፈሰስ እንድታጠፋ አልፈቅልህም›› አለችኝ፡፡
‹‹ማለት?›› አልኳት፡፡

‹‹ማለትማ እኔና አንተ ስንጋባ ካወጣነው ወጭ በላይ የሆነ ገንዘብ የኢትዮጵያና ኤርትራን ስምምነት ምክንያት በማድረግ አውድመኸው እንዲትመጣ አልፈቅድልህም ማለት ነው!››

‹‹እኔ ግን አንቺ ባትፈቅጅልኝም የገባሁትን ቃል ማጠፍ ስለሌለብኝ ያሰብኩትን ነገር ለማሳከት ወደኋላ አልልም›› አልኳት ደሜ እየፈላ፡፡

‹‹ያንተን ቃል ተወው! ለኢትዮጵያ ቀርቶ ለእኔ ለሚስትህ በሰርጋችን ቀን የገባኸውን ቃል ደርምሰህ በፌስቡክ አካውንትህ ስንት ነገር ስትፈጽም እንደምትውል የማላውቅ እንዳይመስልህ›› በማለት ኩም አደረገችኝ፡፡

እናም እንደ ይስማዕከ ወርቁ ለትንሽ ጊዜ ዝም ካልኩኝ በኋላ ‹‹ቆይ ገንዘቡን ምን ልታደርጊው ፈልገሽ ነው?›› በማለት ጠየኳት፡፡

‹‹ልጃችን አራት ዓመት ስለሞላው የግል ትምህርት ቤት መግባት አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ በተርም አምስት ሺህ ብር ያስፈልጋል ስለተባለ ዓመታዊ የትምህርት ወጭውን እሸፍንበታለሁ›› አለችኝ፡፡

‹‹ABCD ለማስተማር በተርም አምስት ሺህ ብር ጥቂት የበዛ አይመስልሽም?››
‹‹ስትል?››

‹‹አይ ለልጁ ትምህርት የሚወጣው ተምሮ ከሚያመጣው ገንዘብ በለጠ ብዬ ነው፡፡››

‹‹እና የበለጠ እንደሆነስ? መቼም የመንግስት ትምህርት ቤት ውስጥ እናስገባው አትለኝም?››
ዝም ብያት ወጣሁ፡፡

ይሄም ሆኖ ግን ሃሳቤን አልቀየርኩም፡፡ ዋናው ነገር የሁለቱ አገሮች መስማማት እንጂ የሁለታችን መፋታት አይደለም፡፡ ጨክና ጥላኝ ብትሄድ እንኳን ላጣው የምችለው ነገር አልጋ እንጂ ወደብ አይደለም፡፡

እንደውም አገሬ የባህር-በር ባገኘችበት ወቅት ላይ እኔ የነጻነት በር ማግኘቴ ከዶክተር አቢይ የመቶ ቀናት ሪፖርት ውስጥ ስኬት ሆኖ ሊቀርብ ሁሉ ይችላል፡፡ እኔም ከአርባ ቀን በላይ ተጉዤ አስመራ ስደርስ ፓራዲዞ ገብቼ፣ ሜሎቲ ቢራ ጠጥቼ እነ ፊያሚታ ጊላይን ስመለከት አምሽቼ ባዶዬን ከመውጣት እድናለሁ፡፡

እናም ከእኔ ጋር በመጣመር በእግራችሁ አስመራ ድረስ የመሄድ ፍላጎቱ ያላችሁ ሰዎች ‹8400› ላይ ስማችሁን ጽፋችሁ በመላክ መመዝገብ የምትችሉ መሆኑን በማሳሰብ ወጌን ‹ኦሮማይ› አደርጋለሁ፡፡ DireTube

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram