fbpx

አሜሪካ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሚመሩት መንግሥት ሙሉ ድጋፍ እንደምታደርግ ገለጸች

የግንቦት 20 በዓልን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒኦ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለሚመራው መንግሥት አገራቸው ያልተቆጠበ ድጋፍ እንደምታደርግ አስታወቁ፡፡

ሚኒስትሩ በጻፉት ደብዳቤ፣ ‹‹አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድን እንኳን ደስ አለዎት እያልኩ፣ በኢትዮጵያ ትልቅ የፖለቲካ ለውጥ ለማምጣት ባላቸው ቁርጠኝነትና በቅርብ ዓመታት የተመዘገበውን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማስቀጠል ሙሉ ድጋፋችን አይለያቸውም፤›› ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያና አሜሪካ ቀጣይነት ላለው ዕድገት፣ ለዴሞክራሲ፣ ለሰብዓዊ መብቶች፣ ለሰላም፣ ለደኅንነትና ለመልካም አስተዳደር ባላቸው ቁርጠኝነትና በተለይም እጅግ አስፈላጊና ተዕዕኖ ፈጣሪ በሆኑ ኢትዮጵያዊ አሜሪካዊ ዜጎች ምክንያት የረዥም ጊዜና ጥልቅ የሆነ ጉድኝት አላቸው ብለዋል፡፡

ፖምፒኦ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ድጋፍ እንደምታደርግ ሲገልጹ በአንድ ወር ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡ ግንቦት 10 ቀን 2010 ዓ.ም. ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በነበራቸው የስልክ ውይይት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለአዲሱ ሥልጣናቸው እንኳን ደስ አለዎት ካሉ በኋላ፣ የዴሞክራሲ ለውጦችን ለማስፋት በሚደረገው ጥረት የአሜሪካ ጠንካራ ድጋፍ እንደማይለያቸው አስታውቀው ነበር፡፡

ከፖምፒኦ በተጨማሪ የግንቦት 20 በዓልን በማስመልከት የሳዑዲ ዓረቢያ ንጉሥ ሳልማን፣ የኳታር ኢሚር ሼክ ታሚም ቢን ሃማድ አል ታኒ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ፕሬዚዳንት ሼክ ከሊፋ ቢን ዛይድ አል ሳባህና የህንድ ፕሬዚዳንት ሽሪ ፕራናብ ሙኬሬጂ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አድርሰዋል፡፡

ሪፖርተር

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram