ቻይና የፕሬዚዳንትነት የመቆያ ጊዜ ገደብን አነሳች
የቻይና ህዝቦች ኮንግረስ በፕሬዚዳንትነት የማገልገል የመቆያ ጊዜ ላይ የተጣለውን ገደብ ማንሳቱ ተነግሯል።
የኮንግረሱ ውሳኔም አሁን ቻይናን በመምራት ላይ ያሉት ፕሬዚዳንት ዢ ጂምፒንግ መሪ ሆነው እስከ ህይወታቸው ፍፃሜ እንዲቀጥሉ የሚያስችል ነው ተብሏል።
የቻይና ህዝቦች ኮንግረስ ዛሬ ባካሄደው ስብሰባው የፕሬዚዳንትነትየመቆያ ጊዜ ገደብ ላይ የቀረበውን ህገ መንግስታዊ ማሻሻያውን ያፀደቀው።
በኮንግረሱ በተካሄደው የድምፅ አሰጣጠም ማሻሻያው ላይ 2 ሺህ 964 ድምፅ የተሰጠ ሲሆን፥ በዚህም መሰረት በ2 ሺህ 959 ድጋፍ፣ ሁለት ተቃውሞ እና ሶስት ድምፀ ታእቅቦ ህግ መንግስታዊ ማሻሻያው ጸድቋል።
ቻይና እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1990 ወዲህ የፕሬዚዳንትነት የመቆያ ጊዜ ለሁለት አምስት ዓመት መሆን አለበት በሚል ገደብ ጥላበት ቆይታለች።
ሆኖም ግን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2023 ስልጣናቸውን ያስረክባሉ ተብለው የሚጠበቁትን ፕሬዚዳንት ዢ ጂምፒንግ በቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ኮንግረስ ላይ በፓርቲው ባህል መሰረት የሚተካ አቅም ያለው ተተኪ ሳይቀርብ ቀርተዋል።
በአንፃሩ የእሳቸው አስተሳሰብ በፓርቲው ሕገ መንግሥት ውስጥ እንዲካተት እና ከጉባኤው በኋላ ዢ ጂምፒንግ የሚተካ ሌላ ሰው እንደሌለ ከድምዳሜ ተደርሷል።
ከዚህ በመነሳትም በፕሬዚዳንትነት የማገልገል የመቆያ ጊዜ ገደብ እንዲነሳ የተወሰነ ሲሆን፥ ውሳኔውም ፕሬዚዳንት ዢ ጂምፒንግ የቻይና መሪ ሆነው እንዲቀጥሉ እድሉን ያሰፋላቸዋል።
ምንጭ፦ ቢቢሲ