ቻይና አፍሪካን በሚመለከት ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የቀረበባትን ክስ ውድቅ አደረገች
ቤጂንግ “ለአፍሪካ ሀገራት የምታቀርበው ብድር የአህጉሪቱ ሀገራት በእዳ ውስጥ እንዲዳክሩ እያደረገ ነው” በሚል በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የቀረበባትን ክስ ውድቅ አደረገች።
ቻይና ለአፍሪካ ሀገራት እያቀረበች ያለችው ብድር ሀገራቱ በኢንዱስትሪ ለመበልቀግና ለመዘመን የያዙትን እቅድ ለማሳካት እያገዘ መሆኑን ነው ያነሳችው።
የቻይና የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አገራቸው የአፍሪካን የእዳ ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እንደምታየው ገልፆ፥ ሁለቱም ወገኞች መሰረተ ልማትና ኢንዱስትሪ በአህጉሪቷ እንዲስፋፋ እየሰሩ መሆናቸውን አስታውቋል።
ውግዘቱ የመጣው የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሪክስ ቲለርሰን ማክሰኞ ወደ አፍሪካ ከሚያደርጉት ጉዞ አስቀድሞ ትናንት ባቀረቡት ንገግር ቻይና በአህጉሪቱ ላይ ያላት የልማት አስተሳሰብ አፍሪካን ጥገኛ እያደረጋት ነው ይህምሉዓላዊነታቸውን ያዳክማል ማለታቸውን ተተከትሎ ነው።
ቲለርሰን የቻይና ኢንቨስትመንት የመሰረተ-ልማት ክፍተቱን ቢያሟላም ነገር ግን ከፍተኛ የሆነ እዳ አገራቱ እየተሸከሙ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ውንጀላው ሚዛኑን የጠበቀ ያለመሆኑን ገልጸው ቻይና የአፍሪካ ቀዳሚ አበዳሪ አገር አለመሆኗን አስታውቋል።
ይልቁንም የቻይና ብድር ወደ መሰረተ ልማት እና ማምረቻ ኢንዱስትሪዎች እንደሚሄድ ነው ያመለከተው።
በተጨማሪም አንዳንድ የአፍሪካ አገራት ከፍተኛ እዳ ሊሸከሙ የቻሉት በረዥም ጊዜ ሂደት መሆኑንና በቅርብ ዓመታት ውስጥ የተፈጠረ ክስተት አይደለም ብለዋል።
ቲለርሰን በአሜሪካና በአፍሪካ ግንኙነት ላይ ያደረጉት ንግግር የመጀመሪያቸው ሲሆን፥ የትራምፕ አስተዳደር የአፍሪካውያንን ህይወት ለማሻሻል ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ በድርቅ አደጋ ውስጥ ለሚገኙ ለአህጉሪቷ አራት አገራት 533 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ዋሽንግተን መለገሷን አስታውቀዋል።
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2015 በቻይና አፍሪካ ግንኙነት ጉባዔ ላይ የቻይና ፕሬዚዳንት ሺ ጂን ፒንግ ቤጂንግ 60 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ለአህጉሪቷ እንደምትሰጥ ቃል መግባታቸው ይታወሳል።
ምንጭ፦ ሲ ጂ ቲ ኤን