ተተኪው የኢሕአዴግ ሊቀመንበር እስከ ሐሙስ መጋቢት 13 ቀን 2010 ዓ.ም ምሽት ድረስ ይታወቃል
የኢሕአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ ከማክሰኞ መጋቢት 11 ቀን 2010 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ መካሄድ ጀመረ፡፡
የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከመጋቢት 2 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በዝግ ሲመክር መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ስብሰባውን ሰኞ መጋቢት 10 ቀን 2010 ዓ.ም. አጠናቋል፡፡ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ግማሽ ቀን ዕረፍት ካደረጉ በኋላ የምክር ቤቱ ስብሰባ በዝግ መካሄድ ጀምሯል፡፡
እየተካሄደ ያለው ስብሰባ ከሁለት ቀናት እንደማይበልጥ ከምንጮች ለመረዳት ተችሏል፡፡ አንድ መቶ ሰማንያ አባላት ያሉት የኢሕአዴግ ምክር ቤት፣ በዋናነት በኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ተገምግሞ በሚቀርብ ሪፖርትና ለዕይታ ይጠቅማል በተባለ ሰነድ ላይ እንደሚወያይና በመጨረሻም የድርጅቱን ሊቀመንበር እንደሚመርጥ ታውቋል፡፡
በኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች መካከል ያለው ውስጠ ዴሞክራሲ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየላላ እንደመጣና አገሪቱም መቋጫ ባልተገኘለት የፖለቲካ ቀውስ መቆየቷ አይዘነጋም፡፡ በአገሪቱ ከተከሰተው ቀውስ ጋር በተያያዘ አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከፓርቲው ሊቀመንበርነትና ከአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም የመልቀቂያ ጥያቄ ካቀረቡ ድፍን አንድ ወር ቢሞላቸውም፣ እስካሁን እሳቸውን የሚተካው ማን እንደሆነ አልታወቀም፡፡ የኢሕአዴግ ምክር ቤት ይህንን ክፍተት ለመሙላት ነው ስብሰባ የተቀመጠው፡፡
መንግሥት አገሪቱን በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ማስተዳደር አልቻልኩም በማለቱ፣ በመላ አገሪቱ ተግባራዊ የሚሆን ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥራ ላይ ውሏል፡፡
አገሪቱ ካለችበት ቀውስና የሰላም መደፍረስ ሳትወጣ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለስምንት ቀናት በዝግ ሲመክር ቆይቷል፡፡ በስብሰባውም በአመራሩ መካከል የአመለካከት አንድነት በሚፈጠርበት፣ በአገሪቱ ሰላምና ደኅንነት በሚረጋገጥበት፣ በብሔራዊ ፓርቲዎች መካከል ጠንካራ ውስጠ ዴሞክራሲ በሚጎለብትበትና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት እንዳደረገ ተገልጿል፡፡
የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ከዚህ በፊት ፓርቲው ባስቀመጣቸው ውሳኔዎች አፈጻጸምና የታዩባቸው ጉድለቶች ሰፊ ውይይት ማድረጉን የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል፡፡ ‹‹በአሁኑ ወቅት እያጋጠሙ ያሉ የአመራር ድክመቶች የወለዳቸውን ችግሮች ለማረም የሚያስችል አመለካከትና አንድነት የሚፈጥር ሁኔታ መኖሩን አረጋግጧል፤›› ሲል በመግለጫው አውስቷል፡፡
‹‹በዚህ ግምገማ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እያንዳንዱ ብሔራዊ ድርጅት አገሪቱ ያስመዘገባቸው ለውጦችና በሒደት ያጋጠሙ ፈተናዎች በሚመሩዋቸው ክልሎችና በአገር አቀፍ ደረጃ ያላቸውን አስተዋጽኦ በዝርዝር በመፈተሽ ጥንካሬዎቻቸው ጎልብተው እንዲቀጥሉ፣ ጉድለቶች ደግሞ በፍጥነት እንዲታረሙ አቅጣጫ አስቀምጧል፤›› ሲል በመግለጫው አስረድቷል፡፡
የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በምክር ቤቱ አማካይነት የአመራር ክፍተቱ እንደሚሟላ ጠቁሞ ይህም በኢሕአዴግ ፕሮግራም፣ ሕገ ደንብና በተለመደው አሠራር መሠረት እንደሚሆን አስታውቋል፡፡
በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ስምምነት የተደረሰባቸው የውሳኔ ሐሳቦች ለኢሕአዴግ ምክር ቤት ቀርበው ተቀባይነት ካገኙ፣ የግንባሩን ሊቀመንበር ለመምረጥ ወደ ድምፅ አሰጣጥ እንደሚሸጋገር ታውቋል፡፡
ተተኪው የኢሕአዴግ ሊቀመንበር እስከ ሐሙስ መጋቢት 13 ቀን 2010 ዓ.ም. ምሽት ድረስ ይታወቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ፣ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ተተኪ የፓርቲው ሊቀመንበርና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ማን ይሆናል? የሚለው አሁንም ድረስ የብዙዎች መነጋገርያ አጀንዳ ነው፡፡ ከተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትር ማንነት በተጨማሪ አገሪቱን ከገባችበት ችግር ያወጣታል? የሚለውም የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡
ሪፖርተር ጋዜጣ