fbpx

ተሰናባቹ ከንቲባ አዲስ አበባ አሁንም ከሙስና አለመጽዳቷን አመኑ

ተሰናባቹ ከንቲባ አዲስአበባ አሁንም ከሙስና እና ከመልካም አስተዳደር ችግር አለመጽዳቷን አመኑ

ተሰናባቹ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ አሁንም በአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር ሙስና እና መልካም አስተዳደር ችግሮች እንዳልተፈቱ ጠቆሙ፡፡

አቶ ድሪባ ሥልጠናቸውን በትላንትናው ዕለት ለአዲሱ ከንቲባ ማስረከባቸውን አስመልክቶ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ በጻፉት ማስታወሻ እንዳሉት “አሁንም ሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግሮች መኖራቸው እሙን ነው።

የአዲስ አበባ አዲሱ ከንቲባ በመሬትና በሌሎች የመልካም አስተዳደር ችግር በሚታይባቸው ዘርፎች ትኩረት አድርጎ መስራት ይኖርበታል።

በተለይም በመሬት አስተዳደርና በቤቶች ግንባታ ዙሪያ በትኩረት መስራት ይጠበቅባቸዋል። ይህንን ለማድረግም ጠንካራ አመራሮችና የቢሮ ኃላፊዎች ያስፈልጋሉ፡፡ የከተማዋ ሚዲያም ጠንካራ መሆን አለበት” ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

አቶ ድሪባ በዚሁ ማስታወሻቸው በከንቲባነት በቆዩባቸው ባለፉት 5 ዓመታት በአዲስ አበባ በተለይም በቤቶች ግንባታ፤ በትራንስፖርት፤ በትምህርት ተደራሽነት፤ በዉሀና በሌሎችም ዘርፎች ውጤቶች ማስመዝገብ መቻላቸውን ጠቅሰዋል፡፡

አቶ ድሪባ እንደችግር ያነሱትን ሙስና የመልካም አስተዳደር ችግር ለምን ሊቀርፉት እንዳልቻሉ የጠቀሱት ነገር የለም፡፡ ሆኖም ህብረተሰቡ አሁንም ሙስናን በማጋለጥና ተሳትፎውን እንዲያጠናክር በትህትና እጠይቃለሁ ብለዋል፡፡ በቆይታቸው ወቅት ከጎናቸው የነበረውን የአዲስአበባ ከተማ ሕዝብን አመሰግነዋል፡፡

የአዲስአበባ ከተማ ምክርቤት በትላንትው ስብሰባው ኢንጅነር ታከለ ኡማ በንቲ ምክትል ከንቲባ አድርጎ ከመሾሙ በተጨማሪ ዶ/ር ኢንጅነር ሰለሞን ኪዳኔ እና ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ ሾሟል፡፡

በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት የተሻሻለው ከተማዋ ቻርተር የከተማው ከንቲባ ከምክርቤት አባላት መካከል እንደሚመረጥ የሚደነግግ ሲሆን ኢንጅነር ታከለ ደግሞ የምክርቤቱ አባል ባለመሆናቸው ምክንያት ምክትል ከንቲባ በመሆን የከንቲባውን ሥራ እንደሚያከናውኑ ታውቋል፡፡

ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም አምስት ዓመት የስልጣን ቆይታውን ያጠናቀቀው የአዲስአበባ ምክርቤት በሚቀጥለው ዓመት ይካሄዳል ተብሎ እስከሚጠበቀው ምርጫ ድረስ በሥልጣን ላይ ይቆያል፡፡ DireTube

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram