fbpx

ቦርጭ የሚያስከትለው አደጋ

ባደጉ አገራትም ይሁን ባላደጉት አገራት ውፍረት በተለይም ቦርጭ ግለሰቦችን፣ የጤና ተቋማትንና መንግስታትን እያሳሰበ ይገኛል፡፡

ቦርጭ በስብ አማካኝነት ሆድ ላይ የሚከማች ሲሆን፥ ጉበትን ጨምሮ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎቻችንን በስብ እንዲከበቡ ያደርጋል፡፡

ለቦርጭ ሊያጋልጡን ከሚችሉ ዋነኛ ጉዳዮች መካከል በስኳር የበለጸጉ ምግቦችን አብዝቶ መመገብ፣አብዝቶ መጠጣት፣የፕሮቲን ይዘት የሌላቸው ምግቦችን መመገብና ሌሎቹም ናቸው፡፡

በተጨማሪም ሴቶች መውለድ ሲያቆሙ ከሆርሞን ለውጥ ጋር ተያይዞ ቦርጭ ሊከሰት ይችላል፡፡

በህይወት ስንኖር ጭንቀት ሊያጋጥም የሚችል ነገር ቢሆንም ከልክ ያለፈ ጭንቀት የሰውነታችንን የስኳር መጠን የሚቆጣጠረውን፣ የምግብ መፈጨትን የሚሳልጠውንና ሌሎችንም ድርጊቶች የሚከውነው ሆርሞን ላይ ጫና በመፍጠር ለቦርጭ ያጋልጠናል ይላሉ፡፡

ከወላጆቻችን የምንወርሰው ዘር እንዲሁም እንቅልፍ ማጣትና ሌሎችም ጉዳዮች ለውፍረትና ለቦርጭ ሊዳርጉን የሚችሉ ጉዳዮች ናቸው፡፡

እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸው ምክንያቶች ጤናችን ላይ ምን ዓይነት ጉዳት ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ጥናቶች ምን እንደሚሉ እንመልከት፡፡

ቦርጭና የስኳር ህመም

በሰውነችን ላይ በተለይም የቦርጭ የስብ ክምችት እየጨመረ በሚሄድበት ወቅት በዓይነት ሁለት የስኳር ህመም የመጋለጥ ዕድላችንም እየጨመረ ይሄዳል፡፡

ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከሆነ በተለይም በወገብ ዙሪያ ያለውን የስብ ክምችት መቀነስ በሽታው እንዳይከሰት ያደርጋል ይላሉ፡፡

ቦርጭና የልብ ህመም

ከመጠን በላይ የሆነ የስብ ክምችት በተመሳሳይ ለልብ ህመም የሚዳርግ ሲሆን፥ ስብንና ኃይልን በማጠራቀም የሚታወቀውን ሆርሞን ይዘቱ እንዲጨምር በማድረግ ለበሽታው ሊዳርገን ይችላል ይላሉ፡፡

ጤናማ የሆነ አቋም ላይ እንደሚገኙ ወይንም ከመጠን ማለፎን ለማረጋገጥ ወደ ህክምና ተቋማት ጎራ ቢሉ በቀላሉ ማወቅ ይችላሉ፡፡

ቦርጭና የደም ግፊት

ይህም በተመሳሳይ ሆድ አካባቢ ያለው የስብ ክምችት መጠን እየጨመረ ሲሄድ፥ በበሽታው የመያዝ ዕድልን በዚያው መጠን ይጨምራል ይላሉ፡፡

ይህ በሽታ የሚከሰተው በኩላሊት ጀርባ በኩል ያለው አካል ለስብ ክምችት ሲጋለጥ የኩላሊትን ስራ በሚያስተጓጉልበት ወቅት ነው ይላሉ ጥናቶች፡፡

ቦርጭና ካንሰር

በተለይም በወገብ ዙሪያ የሚከማቹ ስቦች ለተለያዩ ዓይነት የካንስር ህመሞች ሊዳርግን ይችላል፡፡

የቅርብ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከሆነ ከሰውነታችን ስብ የሚለቀቁ ፕሮቲኖች የተለያዩ መንገዶችን በማለፍ ለካንሰር ህመም እንደሚያጋልጡ ጠቁመዋል፡፡

ቦርጭና በእንቅልፍ ወቅት የትንፋሽ መቆራረጥ

በእንቅልፍ ወቅት በትንፋሽ መቆራረጥ ምክንያት 18 ሚሊየን የሚደርሱ አሜሪካውያን እንደሚጠቁ ጥናቶች አሳይተዋል፡፡

ይህ ሁኔታ ከሴቶች ይልቅ ወንዶች ላይ ይበረታል ብለዋል፡፡

ቦርጭ ስለሚያስከትላቸው ጉዳቶች ይህንን ካልን እንዴት መከላከል እንችላለን የሚለውን ደግሞ እንመልከት፡፡

ከላይ የጠቀስናቸው ቦርጭን ሊያስከትሉ የሚችሉ ድርጊቶችን መከላለከል እንዳለ ሆኖ፤ ከዚህ በተጨማሪ በሳምንት ሁለት ጊዜ የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ በሳምንት ለ150 ደቂቃዎች የእግርመንገድ መራመድ፣ የሆድ ስፖርቶችን መስራትና ሌሎችንም እንቅስቃሴዎች ማድረግ መፍትሄዎች ናቸው፡፡

በተጨማሪም የአመጋገብ ስርዓትን ማስተካከል፤ አትክልቶችን መመገብ፣ የፕሮቲን ይዘት ያላቸውን ምግቦች እንደ አሳ እና የእንስሳ ተዋፅዖችን ማዘውተር፣ በቂ ውሃ መጠጣት እና የስኳር ይዘት ያላቸውን መጠጦች ያለመውሰድ ዋነኛ መፍትሄዎች መሆናቸውን ጥናቶች አመልክተዋል፡፡

 

ምንጭ፦ቶፕቴን

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram