fbpx
AMHARIC

ብሔር ተኮር ትንኮሳዎች አገራዊ አንድነትን ያፈርሳሉ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ አንፃራዊ ሠላም የሰፈነ ቢሆንም በተለያዩ ሁኔታዎች ብሔር ተኮር ትንኮሳዎችና ግጭቶች መታየታቸው አልቀረም፡፡ እነዚህ ደግሞ በአገሪቱ ዘላቂ ሠላም እንዳይኖር ከማድረጉም በላይ አገራዊ አንድነትን ያፈርሳሉ፡፡

አቶ ንጋቱ አብዲሳ፣ በፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር የግጭት የቅድመ ማስጠንቀቂያና ዘላቂ መፍትሄ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ጄኔራል ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ በህዝቦች ውስጥ የተለያዩ አመለካከቶች ቢኖሩም ህብረተሰቡ ሰላምን በተመለከተ አንድ አይነት አመለካከት መያዝ መቻሉ በአንድ አገር ዘላቂ ሠላምን ያሰፍናሉ ከሚያስብሉ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው፡፡ በህዝቦች መካከል መከባበርና መቻቻል መኖሩ፤ እንዲሁም በመከባበርና መቻቻል ውስጥ የሚገለጽ አንዱ ለሌላኛው ሃይማኖትና ባህል የሚገባውን ክብር መስጠት መቻሉም ተደማሪ የዘላቂ ሠላም መሰረቶች ናቸው፡፡

በኢትዮጵያም እነዚሁ መገለጫዎች ዘመናትን ተሻግረው የሚገለጹ ሲሆን፤ በህዝቡ መካከል ያለው መከባበር፣ መቻቻልና አብሮነትም ኢትዮጵያን ሠላማዊና የተረጋጋች አገር እንድትሆን አድርጓታል፡፡
ይህ እውነት እንደተጠበቀ ቢሆንም አሁን ላይ አልፎ አልፎ በየቦታው የሚታዩ ግጭቶች መኖራቸውን የሚናገሩት አቶ ንጋቱ፤ እነዚህ ግጭቶች በዋናነት አሁን ባለው ፌዴራላዊ አስተዳደር በአንድ ክልል ውስጥ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች የመኖራቸውን ያክል ክልሉን የሚያስተዳድረው አካል ሁሉንም በፍትሃዊነት ካለማገልገልና አንዱን ጠቅሞ ሌላውን ከመግፋት የሚመነጭ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ማንኛውም ዜጋ በየትኛውም ቦታ ተንቀሳቅሶ ሀብት የማፍራት መብት ቢኖረውም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ይሄ ሕገ መንግሥታዊ መብት ሲጣስ እየተስተዋለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህ ግን የብሔር ግጭት ነው ተብሎ በሙሉ አፍ የሚነገር ሳይሆን፤ የብሔር ግጭት እንዲመስል ያደረገው ጥቂቶችና በኃላፊነታቸውም ጥቅም ፈላጊዎች በሚፈጥሩት ትንኮሳ የሚከሰት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካና ምጣኔ ሀብት ምሑር የሆኑት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸ ይሄን ሐሳብ ይጋራሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ ብሔርን መሰረት አድርጎና ዘርን ማጥፋት ላይ ተመስርቶ የተከናወነ ግጭት ተከስቶ አያውቅም፡፡ የሚስተዋሉ ግጭቶችም የብሔር ግጭት ከሚባሉ ይልቅ የጎሳ ግጭት ቢባሉ ይቀላል፡፡ ምክንያቱም የጎሳ ግጭቶች ለረዥም ጊዜ የነበሩ ናቸው፡፡ በተለይ በደቡቡ፣ በምዕራቡና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አካባቢ ያሉ ጎሳዎች፤ አንደኛ፣ በመሬት፤ ሁለተኛም በከብቶች ውሃና ግጦሽ ምክንያት በየጊዜው ግጭቶች ይከሰታሉ፡፡ አሁን የሚታዩት ነገሮች ግን 27 ዓመት ሙሉ በብሔር ብሔረሰቦች ላይ የተመሰረተ አስተዳደር ሲቋቋም በወረዳና በዞን ደረጃ ጎልቶ እየታየ ያለ ነው፡፡

እንደ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ገለፃ፤ በተለይም ባለፉት ሦስት ዓመታት የነበረው ግጭት ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ጎሳን ወይም ብሔርን ሽፋን በማድረግ የሚከናውኑ እንደመሆኑ፣ ወደ ጎሳና ብሔር አዘል ግጭት እየተቀየሩ የመጡ መስለዋል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ አካላት በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ እየኖሩ ሀብትና ሥልጣን ለማግኘት ሲሉ አንዱን ጎሳ ወይም ብሔረሰብ ተጠግተው ትንኮሳ የሚፈጽሙ ናቸው፡፡ በዚህ መልኩ ጎሳና ብሔርን ተላብሰው የሚከናወኑ ትንኮሳና ግጭቶች ብሔር ብሔረሰቦችን ይረብሻሉ፡፡ የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች ሠላም ካልሆኑ ደግሞ አገሪቱ ሠላም አትሆንም፡፡ አገራዊ አንድነትም አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡ በመሆኑም ይሄን መሰል ትንኮሳና ግጭቶች በአገሪቱ የሚታየውን አንፃራዊ ሠላም ዘላቂ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ላይ ተጽዕኖ አላቸው፡፡

አቶ ንጋቱ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ህዝቡ ተዋዶና ተፋቅሮ አብሮ እየኖረ ነው፡፡ አሁን የሚታየው ግን እነዚህ ህዝቦች በዚህ መልኩ እንዳይኖሩ ለማድረግ ለአንድ ብሔር የማድላትና ሌሎችን በመግፋት የመልካም አስተዳደር ችግር በመፍጠርና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን በመንፈግ ብሔር መሰል ግጭት እንዲፈጠር ማድረግ ነው፡፡ ከጥቅም ጋር የተያያዘው ይህ ትንኮሳም ህዝቡ በሠላም አብሮ እንዳይኖር፣ በጋራም ሀብት እንዳያፈራና በአገሪቱም ዘላቂ ሠላም እንዳይመጣ እያደረገ ነው፡፡ በኦሮሚያና በኢትዮያ ሶማሌ ክልል፣ በጌዲዮና ጉጂ፣ እንዲሁም በቤንሻንጉል ጉሙዝ የተፈጠሩ ችግሮችም ችግሩ የብሔር ሳይሆን ብሔርን የተጠጋ የጥቅም ጉዳይ ለመሆኑ ማሳያዎች ናቸው፡፡

ይሄን ሐሳብ የሚጋሩት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በበኩላቸው እንደሚገልጹት፤ ብሔርና ጎሳን ተገን አድርጎ የሚከሰት ትንኮሳና ግጭት ሠላማዊ እንቅስቃሴን ያውካል፤ ዜጎችም ተዘዋውረው እንዳይሠሩ ይገድባል፡፡ በአለፉት ሦስት ዓመታትም አንዱ ብሔር ሌላውን ብሔረሰብ ከመካከላችን ውጣልን የሚለው ትንኮሳ ተጀመረ፡፡ በቅርቡም በጉጂና ጌዲዮ ሕዝቦች በተፈጠረው ግጭት 800ሺ ሰው እንደተፈናቀለ የሚነገረው ቁጥር በራሱ ችግሩን ያጎላዋል፡፡ እነዚህ ሕዝቦች ግን ለዘመናት በሠላም የኖሩ ናቸው፡፡ የችግሩ መፈጠርም የመንግሥት አስተዳደር መድከሙን ማሳያ ቢሆንም፤ እውነቱ ግን ወደ ቅሚያና ዝርፊያ ለማምራት፣ አገር ለማመስና በመሃል ቀዳዳ ፈጥሮ ሥልጣን ለመያዝ ያስችለናል በሚል የሚፈጠር የጥቂቶች ሴራ ነው፡፡

“ሲጀመር በዚች አገር ውስጥ መጤ እና ነባር የሚባል ሕዝብ የለም” የሚሉት አቶ ንጋቱ በበኩላቸው፤ አንድ ሰው በአገር ውስጥ እስካለ ነባር መሆኑንና በቦታው ያለመወለዱና ያለመኖሩ እንግዳ ያሰኘው እንደሆነ እንጂ በየትኛውም ቦታ ተንቀሳቅሶ መሥራት የሚችል እንደመሆኑ መጤ ሊባል እንደማይገባውም ገልጸዋል፡፡ ይህ መጤና ነባር የሚል የጥቂቶች አስተሳሰብም በህብረተሰቡ ውስጥ ጥላቻ እንዲፈጠር፣ በሠላም አብሮ እንዳይኖር ሠላሙን ለማደፍረስና ዘላቂ ሠላምም እንዳይመጣ የሚደረግ ጥረት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ዶክተር ቆስጠንጢኖስ እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ በለውጥ ላይ የነበረች፣ ከረዥም ዓመታትም ብዙ ፈተና ያለባት ናት፡፡ ለአብነት፣ በዓፄ ኃይለሥላሴ ዘመን የነፃ አውጪ ድርጅቶች ነበሩ፤ በደርግ ወደ 30 የሚደርሱ ነፃ አውጪ ነን በሚሉ አካላት አገሪቱ ስትታመስ ነበር፡፡ ኢህአዴግ ከመጣም በኋላም 17 ድርጅቶች የሽግግር መንግሥቱን ይዘው ነበር፡፡ ኢህአዴግ ሲረከብ ግን አንፃራዊ ሠላም ሰፍኖ የነበረ ቢሆንም፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት የነበረው ነውጥ አገሪቱን ለማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆን ለህብረተሰቡ አኗኗር ትልቅ ፈተና እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በተለይም ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ ወደ ኃላፊነት ከመምጣታቸው በፊት ባሉት ወራት አዲስ አበባና አካባቢዋ ዕቃ እንኳን ሊገባና ሊወጣ፣ ሕዝቡም ሊንቀሳቀስ የማይችልበት ደረጃ ላይ ተደርሶ ነበር፡፡

አልፎ አልፎ የሚታዩ የግጭት መንስኤዎችን ማስተካከል ካልተቻለና ችግሮቹም መሰረታዊ መፍትሄ ካላገኙ በአገሪቱ የሚፈለገውን ዘላቂ ሠላም ለማምጣት አይቻልም፡፡ ሠላም ከሌለም ልማት አይኖርም፣ የሥራ ዕድል መፍጠርም አይቻልም፤ የዴሞክራሲ ምህዳሩም ሊሰፋ አይችልም፡፡ እነዚህ በሌሉበት ደግሞ በጎሳም ሆነ በዘር ሽፋን የሚደረገው ስውር ተግባር አይገታም፤ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችም አይቀጥሉም፡፡ ይህ ደግሞ ጽንፈኝነትን፣ በጉልበት እየዘረፍን እንኑር የሚሉና ወደ ውንብድና የሚሄዱ ቡድኖችን ይፈጥራል፡፡ የነበረው አንፃረዊ ሠላምም ይደፈርሳል፤ በመጨረሻም አገርን ያፈርሳል ፡፡

ዜና ትንታኔ
ወንድወሰን ሽመልስ – የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram