fbpx

ባለንበት የዲጅታል ዘመን የልጆቻችንን ጤና ለመጠበቅ የሚረዱ 11 ምክረ ሀሳቦች

ባለንበት የዲጅታል ዘመን የልጆቻችንን ጤና ለመጠበቅ የሚረዱ 11 ምክረ ሀሳቦች፡-

አሁን ያለንበት ዘመን ዲጂታላዊ ሲሆን ከታዳጊ እስከ አዋቂዎች ድረስ የስማርት ስልክ ተጠቃሚ መሆናችንም ጥቅም እና ጉዳትን ይዞ መጥቷል።

ግሎባል ዌልነስ ኢንስቲትዩት የተባለው ተቋም Wellness in the Age of the Smartphone በሚል ርዕስ ይዞት በወጣው መረጃ ያለንበት የቴክኖሎጂ አቢዮት ማምለጥ የማንችላቸው የህይወት ውጣ ውረዶችን ደቅኗል ነው ያለው።

በአንድ በኩል አሰራርን በማቅለል፣ በፍጥነት መልዕክትን በመለዋወጥ ፋይዳ ሲያበረክት በሌላ በኩል ለአዕምሯዊ ጤንነት ችግርም እየዳረገ ነው።

ወላጆች ስማርት ስልኮች የልጆቻቸውን ማህበራዊ፣ አካላዊና ስሜታዊ ሁኔታዎች እንዲሁም የወደፊት ህይወታቸው ላይ የሚያሳርፉትን መጥፎ ወይም ጥሩ አሻራ በመገምገም ላይ እንዲያተኩሩ አስገዳጅ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል።

በዲጅታል ዘመን ልጅን ያለ ስማርት ስልክና ሌሎች የቴክኖሎጂ ውጤቶች ወደ ትምህርት ቤት መላክ የማይቻልበት እና ቤት ውስጥም ልጆች ከቴክኖሎጂ ምርቶች ጋር እንዲያሳልፉ ልቅ መብት የሰጠ የሚመስሉ ነባራዊ እንቅስቃሴዎችም አሉ።

በርካታ ተመራማሪዎች ባደረጓቸው ጥናቶች የስማርት ስልክና መሰል የቴክኖሎጂ ውጤቶች አጠቃቀም በልጆች ላይ አሉታዊም ሆነ አውንታዊ ጫና እንደሚኖረው ይስማማሉ።

ተመራማሪዎቹም ባለንበት የዲጂታል ዘመን የልጆቻችንን ሁለንተናዊ ጤንነትና ደህንነት ለመጠበቅ ይረዳሉ ያሏቸውን 11 ምክረ ሀሳቦች ሰንዝረዋል።

1.ልጆች ስማርት ስልክ ወይም ሌላ የቴክኖሎጂ ውጤት ስክሪን የሚመለከቱበትን ጊዜ መወሰን
ልጆች የስማርት ስልክ ሱስ ተጠቂ ሆነው በማህበራዊና ሌሎች ህይወታቸው ላይ ግድ የለሽ እንዳይሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የሚጠቀሙበትን እና በስክሪን ላይ አፍጥጠው የሚያሳልፉበትን ጊዜ መገደብ ያስፈልጋል ነው የተባለው።

2.አካላዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ማበረታታት
የአካላዊ እድገት ላይ ያተኮሩ የምርምር ጥናቶች እንደሚያሳዩት ልጆች ለረጅም ጊዜ በስክሪን ላይ ማሳለፋቸው አካላዊ እንቅስቀቃሴ እንዳያደርጉና ለውፍረት እንዲጋለጡ ያደርጋል።

በመሆኑም ወላጆች በዲጅታል ዘመን ጤናማ ልጅ ለማሳደግ አካላዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ማበረታታት አለባቸው።

1. አዕምሯዊ ደህንነታቸውን መከታተል
ተመራማሪዎች የማህበራዊ ሚዲያ እና የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት እያደገ መምጣት የድብርት፣ የውጥረት አና ራስን የማጥፋት ሰለባ የመሆን እድልን እየጨመረ መምጣቱን ይገልጻሉ።

ወላጆች የልጆቻቸውን አዕምሯዊ መረበሽና ህመምን የመረዳት ልምድ ስለሚኖራቸው በየጊዜው እየተከታተሉ መፍትሄ ማበጀት ይገባቸዋል።

2. የጭንቀት መቀነሻ መንገዶችን እንዲለማመዱ ማድረግ
ግሎባል ዌልነስ የተባለው ተቋም ለአዕምሯዊ ጤንነት ዋነኛው ስጋት ቴክኖሎጂው ራሱ ሳይሆን በቴክኖሎጂው አማካይነት የሚሰራጩ መረጃዎች፣ ልጆች ከጓደኞቻቸው ጋር የሚያደርጓቸው የመልዕክት ልውውጦች ናቸው ይላል።

ወላጆች ልጆቻቸው ለጭንቀት እንዳይዳረጉ እና ጭንቀት ቢያጋጥማቸው መረጋጋት የሚችሉበትን የተመስጦ፣ የመዝናናት እና ሌሎች ተግባራትን እንዲያዘወትሩ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

3.የአቻ ጓደኝነታቸውን እንዲያጠናክሩ ምቹ ሁኔታ መፍጠር
በማህበራዊ ሚዲያ ግንኙነት በመፍጠርና ከሌሎች አቻዎቻቸው ጋር መተዋወቅ የተለመደ ነገር ነው፤ ሆኖም በአሁኑ ጊዜ ብቸኝነትን የሚያዘወትሩ ታዳጊዎች እየተበራከቱ ነው።

ስለሆነም ወላጆች ልጆቻቸው በተጨባጭ ከሌሎች ልጆች ጋር በአካል እንዲዝናኑና እንዲጫወቱ በማድረግ የአቻ ጓደኝነታቸውን ማጠናከር አስፈላጊ ነው።

4. የቀጥታ ኢንተርኔት የጤና መረጃዎችን መጠቀም
በርካታ የጤና መረጃዎች በኢንተርኔት በቀጥታ ማግኘት የሚቻልበት ዘመን ላይ ተደርሷል፤ በመሆኑም ወላጆች አንዳንድ አሳሳቢ ምልክቶችን በልጆቻቸው ላይ ሲመለከቱ ወዲያውኑ በቀጥታ ኢንተርኔት ላይ በመፈለግ መፍትሄ ማበጀት ይችላሉ ነው የተባለው።

5. የአካል ብቃትና ደህንነትን ለመጠበቅ የሚረዱ መተግበሪያዎችን መጠቀም
በአሁኑ ወቅት ልጆችም ሆኑ ወላጆች አካላዊ ጤንነታቸውን መጠበቅ የሚችሉበትን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲለማመዱ የሚረዱ መተግበሪያዎች በመመረት ላይ ናቸው።

ወላጆች እነዚህን የዲጅታል ዘመን መተግበሪያዎች ለልጆቻቸው ጤንነትም ሆነ ለራሳቸው ቢጠቀሟቸው መልካም ነው።

6. የመኝታ ክፍል ደንብ ማዘጋጀት
በርካታ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት በርካታ ሰዎች በሚተኙበት ሰዓት በመኝታ ክፍላቸው ውስጥ ለረጅም ሰዓት ስማርት ስልክና መሰል ቴክኖሎጂ የመጠቀም ልማድ ያዘወትራሉ።
ይህ ደግሞ ለከፍተኛ የዓይን፣ የአዕምሮና ሌሎችም ችግሮች እየዳረገ ይገኛል።

ሆኖም ወላጆች ራሳቸውም ሆኑ ልጆች በመኝታ ሰዓት ከምንም ዓይነት የቴክኖሎጂ ስክሪን እንዳይገናኙ የሚያደርግ የመኝታ ክፍል ደንብ አውጥተው መተግበር ይገባቸዋል።

7. የመረበሽ ሁኔታዎች እና የደህንነት ስሜቶች ላይ መወያየት
ስማርት ስልክን በሚጠቀሙ ሰዓት ሙሉ ትኩረት የሚያርፈው የስማርት ስልኩ ስክሪን ላይ በሚታዩ መረጃዎች፣ ምስሎች ወዘተ ላይ ነው።

ልጆች ከቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት በፊት ጤንነታቸውን ሊያስቀድሙ ይገባል፤ አዕምሯቸውን የሚረብሻቸውና ትኩረታቸውን የሚሰርቅ ጉዳይ ካለ ለወላጆቻቸው በግልፅ መናገር አለባቸው።

8. ከልጆች ጋር ስለ ዲጅታል ስነ ምግባር መወያየት
ልጆች ወደ ጉርምስና ከፍ ሲሉ በቀጥታ ኢንተርኔት ስለሚለቀቁ መረጃዎች ዓይነት፣ ከሌሎች ሰዎች ጋር እንዴት ተግባቦት መልዕክት መለዋወጥ እንዳለባቸው፣ በጠቃሚ ጉዳዮች ላይ የክርክር ሀሳቦችን እንዴት ማንፀባረቅ እንደሚኖርባቸው፣ የዲጂታል መልካም ዜጋ መሆን ስለሚቻልባቸው መንገዶች በወላጆች ሊመከሩ ይግባል።

9. የሰብዓዊነት መንፈሳቸውን እንዲያጠናክሩ ማገዝ
ቴክኖሎጂ ከአጠቃቀም ጉድለት የተነሳ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሰዎችን እውነተኛ ጠቃሚ መንፈሳዊ እሴቶች በመለዋወጥ ላይ ይገኛል።

በመሆኑም ልጆች በቴክኖሎጂው ዓለም ውስጥ እውነተኛውን የሰውን ልጅ መልካም ተሞክሮና እሴት እንዲያጎለብቱ አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ ግድ ይላል።

ምንጭ፦www.psychologytoday.com

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram