በ4 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ተግባራዊ የሚደረግ የእንስሳትና የዓሣ ልማት ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ

በመጪዎቹ ስድስት ዓመታት በ4 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ተግባራዊ የሚደረግ የእንስሳትና የዓሣ ዘርፍ ልማት ፕሮጀክት ይፋ መሆኑን የግብርናና እንስሳት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ በፕሮጀክቱ ትግበራ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የተዘጋጀ የምክክር መድረክ በቢሾፍቱ ከተማ በተካሄደበት ወቅት ነው ያስታወቀው።

በሚኒስቴሩ የፕሮጀክቱ ብሔራዊ አስተባባሪ ዶክተር ቶማስ ቸርነት እንደተናገሩት ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ለማድረግ ከዓለም ባንክ 170 ሚሊየን ዶላር ብድርና ከዓለም አቀፍ የልማት ማህበር ደግሞ 6 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ተገኝቷል።

ከፈረንጆቹ 2018 እስከ 2023 ድረስ በሚቆየው በዚህ ፕሮጀክት በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ ትግራይ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝና ጋምቤላ ክልሎች ተግባራዊ እንደሚደረግ አስታውቀዋል ።

በዋናነት የእንስሳትና ዓሣ ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ እስከ ዘመናዊ ግብይት ለማረጋገጥ ትኩረት የሚደረግበት ሲሆን፥ በተመረጡ 58 ወረዳዎችና 1 ሺህ 625 ቀበሌዎች ውስጥ የሚተገበር ይሆናል ተብሏል።

ፕሮጀክቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ የዘርፉ አንቀሳቃሽ የሆኑትን የፌዴራልና የክልል ተቋማትን በሰው ኃይል ከማጠናከር ባለፈ የቁሳቁስና የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያደርግም ተገልጿል።

የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎችን የጥሬ እቃ አቅርቦት በማሳደግ ዘላቂ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንዲቻልም በአራቱ የልማት ቀጠናዎች- ወተት ፣ ዶሮ፣ ስጋና ዓሣ አምራችና አቀነባባሪው ላይ በትኩረት እንደሚሰራ አቶ ቶማስ ገልፀዋል።

የግብርናና እንስሳት ሚኒስትሩ ተወካይ ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ በበኩላቸው “በሃገሪቱ ካላው እምቅ የእንስሳት ሀብት በሰፊው ለመጠቀም እንዲቻል የእንስሳት ሀብት ልማት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ለተግባራዊነቱ እየተሰራ ነው” ብለዋል።

ፕሮጀክቱ የእንቅስቃሴ አካል መሆኑን ጠቁመው፣ “በተለይ ዘመናዊ አሰራርን የሚጠቀም ሕብረተሰብ ለመገንባትና በገበያ የሚመራ የእንስሳት ሀብት ልማት ለማስፋፋት ጠቀሜታው የጎላ ነው” ብለዋል።

በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ተወካይ ሚስተር ፓውል ጆናታን በበኩላቸው ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ የተሰጠው ብድር የሀገሪቱን ልማት ለመደገፍ ወቅታዊና ትክክለኛ መሆኑን ገልጸዋል።

“በተለይ ፕሮጀክቱ የወተት ጥራትና ምርታማነትን በማሻሻል፣ ለገበያና ኢንዱስትሪ ጥሬ እቃ የሚውል አቅርቦትን በማሳደግ የዘርፉ ተዋናዮችን ተጠቃሚነት በዘላቂነት እንደሚያረጋግጥ ታምኖበታል” ብለዋል።

ፕሮጀክቱ የህብረተሰቡን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ ቋሚ የገቢ ምንጭ በመፍጠር የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እንደሚደግፍ የዓለም ምግብና እርሻ ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ሚስስ ፋጡማ ሰኢድ ናቸው።

በዚህም ከአንድ ሚሊየን በላይ የእንስሳትና ዓሣ አርቢዎች፣ በዘርፉ የተሰማሩ ማህበራት፣ ሴቶችና ወጣቶች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተጠቁሟል።

ምንጭ፦ ኢዜአ

Share your thoughts on this post

%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram