fbpx

በፈረንሳይ የአራት አመት ህጻንን ከህንጻ ላይ ከመውደቅ የታደገው ማሊያዊ ስደተኛ ዜግነት ሊያገኝ ነው

በፈረንሳይ የአራት አመት ህጻንን ከአራተኛ ወለል ህንጻ ከመውደቅ የታደገው ማሊያዊ ስደተኛ ዜግነት ሊያገኝ ነው።

ማሞዱ ጋሳማ የተባለው ይህ የ22 አመት ወጣት፥ በፈረንሳይ ፓሪስ አውራ ጎዳናዎች ላይ ከሚገኝ አንድ ህንጻ አራተኛ ወለል ላይ ሊወድቅ የነበረን ህጻን ነው የታደገው።

ወጣቱ የህንጻው ጫፍ ላይ ሆኖ ለመውደቅ ተቃርቦ ወደ ነበረው ህጻን፥ እጆቹን ብቻ በመጠቀም ከወጣ በኋላ ከሞት ታድጎታል።

በአካባቢው በጉዞ ላይ የነበረው ወጣት ህጻኑ የህንጻው አራተኛ ወለል ጫፍ ላይ ለመውደቅ ተቃርቦ ይመለከተዋል።

በወቅቱ የህጻኑን አደጋ ላይ መሆን የተመለከተው ወጣት ከመሬት እስከ ህንጻው አራተኛ ወለል ድረስ በእጆቹ እየተሳበ በመውጣት የህጻኑን ህይዎት ታድጎታል።

ይህ ድርጊቱም ከበርካታ ፈረንሳውያን አድናቆትና ሙገሳ አስችሮታል፤ የህይዎት አድን ተግባሩን ተከትሎም “ሸረሪቱ” የሚል ስያሜን ሰጥተውታል።

የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮንም ቤተ መንግስት አስጠርተው ለፈጸመው በጎ ተግባር አመስግነውታል።

ፕሬዚዳንት ወጣቱ ለሰራው በጎ ተግባርም የፈረንሳይ ዜግነት እንደሚያገኝ ተናግረዋል።

በወቅቱ ለፈጸመው የህይዎት ማዳን ስራም የሜዳልያ ሽልማት ተበርክቶለታል።

ከዚህ ባለፈም ከፈረንሳይ የእሳት እና ድንገተኛ አደጋዎች ክፍልም የስራ እድል ቀርቦለታል ነው የተባለው።

የፓሪስ ከንቲባ አን ሂዳልጎ ወጣቱ ለሰራው ስራ አመስግነው ድርጊቱን ለሌሎች አርዓያ የሚሆን ነው ብለውታል።

ጋሳማ አስቸጋሪውን የባህር ላይ ጉዞ በማለፍ ባለፈው አመት ፈረንሳይ መግባቱ ይነገራል።

 

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram