fbpx

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ትእዛዝ መሰረት በርካቶች በእጃቸው ያለውን የውጭ ሀገር ገንዘብ ወደ ባንክ እያስገቡ ነው

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ትእዛዝ መሰረት በርካቶች በእጃቸው ያለውን የውጭ ሀገር ገንዘብ ወደ ባንክ እያስገቡ መሆኑን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የውጭ ምንዛሪ በእጃቸው የያዙ አካላት በፍጥነት ወደ ባንክ ገቢ እንዲያደርጉ ባሳለፍነው ሰኞ ሐምሌ 9 2010 በሰጡት መግለጫ ማሳሰባቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በወቅቱም፥ የውጭ ምንዛሪውን ያከማቹ አካላት በእጃቸው ያለውን ገንዘብ በፍጥነት ወደ ንግድ ባንኮች ገቢ በማድረግ ከኪሳራ እንዲድኑም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሀላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥሪ ማቅረባቸውን አስታውሰዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተከትሎም በርካቶች በእጃቸው ያለውን የውጭ ሀገር ገንዘብ ወደ ባንክ እያስገቡ ነው ብለዋል።

በዚህም በጥቁር የውጭ ምንዛሪ ገበያ ሲዘዋወር የነበረው አብዛኛው ገንዘብ ወደ ተለያዩ የንግድ ባንኮች እየመጣ መሆኑን የገለጹት አቶ አህመድ፥ የንግድ ባንኮች የውጭ ምንዛሬ ክምችትም እየጨመረ መጥቷል ነው ያሉት።

ህብረተሰቡ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ጥሪ በዚህ ፍጥነት ምላሽ በመስጠቱም የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳይ ሀላፊ ሚኒስትሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

አቶ አህመድ አክለውም፥ አሁንም የተለያዩ የውጭ ሀገራት ገንዘብን በተለያየ መልኩ ያከማቹ ሰዎች በአፋጣኝ ወደ ባንክ እንዲወስዱ አሳስበዋል።

የውጭ ምንዛሬ የጥቁር ገበያን ለማዳከም በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም አቶ አህመድ ሽዴ በመግለጫቸው ተናግረዋል።

ከሚሰወዱት እርምጃዎች ጎን ለጎንም ከወዳጅ ሀገሮች እና ተቋማት በልማት ፋይናንስ መልክ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባውን የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግ የተሰራው ስራም ውጤታማ መሆኑን ገልፀዋል።

መንግስት ህብረተሰቡን ከአጠቃላይ ኢኮኖሚው ተጠቃሚ ለማድረግ አዳዲስ የፖሊሲ አቅጣጫዎች መያዛቸውንም አቶ አህመድ ሽዴ በመግለጫቸው አብራርተዋል።

በዚህም መሰረት በመንግስት የልማት ድርጅት ስር የሚገኙ አራት ድርጅቶችን አብዛኛውን ድርሻ መንግስት ይዞ ቀሪው ድርሻ ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ባለሀብቶች እንዲተላለፉ መወሰኑን ገልፀዋል።

ሌሎች የመንግስት የልማት ድርጅቶችም ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ወደ ግል እንዲዘዋወሩ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም አቶ አህመድ በመግለጫቸው አስታውቀዋል።

ይህ የሚሆንበት ዋናው ምክንያትን በሀገሪቱ እየተመዘገበ የመጣውን ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ለማስቀጠል ነው ሲሉም አቶ አህመድ አብራርተዋል።

በተጨማሪም የግሉ ሴክተር በኢኮኖሚው ላይ ያለውን ሚና ለማሳደግ እና ዓለም አቀፍ እንቨስትመንትን ወደ ኢትዮጵያ ለመሳብ ያለመ መሆኑንም ገልፀዋል።

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram