በጅማ የትራፊክ አደጋ የሰርግ ስነ ስርዓትን ወደ ሀዘን ቀይሯል

በጅማ ከተማ በሰርግ ስነ ስርዓት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ አሳዛኝ ክስተተን ፈጥሮ አልፏል።

ከስተቱ የሆነው እንዲህ ነው፥ የጅማው ሙሽራ ከላጤነት ወደ ትዳር ህይወት ለመግባት፤ የሰርግ ስነ ስርዓቱንም ከወዳጅ ዘመድ ጋር ለማክበር ሚያዚያ 28 መረጦ ሁሉንም ነገር አዘጋጅቷል።

አጃቢዎቹን መርጦ ታዳሚዎቹንም ጋብዞ ሙሽሪትን ለማምጣት ጉዞው ወደ ሙሽሪት ቤት ሆኗል።

በርካታ ተሽከርካሪዎችም እንደተሰጣቸው ማእረግ ተደርድረው እየሄዱ ነበር፣ የከትናንት በስቲያዋ እሁድ ግን ይህን ሰርግ እነሱ ባሰቡት መንገድ እንዲፈጸም አልፈቀደችም ።

የሙሽሮችን ቀስም የሰበረ የታዳሚውንም ደስታ በሃዘን ማቅ ያለበሰ የትራፊክ አደጋ ደረሰ።

በደረሰው የትራፊክ አደጋም ከአጃቢዎቹ መካከል የሙሽራው የቅርብ ጓደኛ፤ ካገባ ገና አንድ ዓመት የጫጉላ ህይወትን የኖረ ወጣት በአደጋው ህይወቱን አጣ።

በአደጋው ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል አንዱ የነበረው ሙስጠፋ ለጉዳት የዳረጋቸውን አጋጣሚ ሲናገር፥ አሽከርካሪው ለምን በሌላ መኪና ተቀደምኩ በሚል እልህ ፍጥነቱን መቆጣጠር አቅቶት ነው የተገለበጠው ይላል።

አደጋው የደረሰውም ለምን ተቀደምኩ ብሎ ሲሮጥ የነበረው መኪና መገንጠያ መንገድ ላይ መታጠፍ ተስኖት በመገልበጡ ነው።

ስሜን አትንገሩ ያለው ሙሽራውም ሃዘኑ ከልክ በላይ መሆኑንና ለሟች ከመጸለይ ያለፈ ቃላት አውጥቼ ለመናገር ይቸግረኛል ብሏል።

በጅማ ዞን የትራፊክ ፖሊስ ረዳት ኢንስፔክተር ኦላና ጆቴ እንደሚናገሩት፥ አደጋውን ያደረሰው አኝከርካሪ ለጊዜው መሰወሩን እና እየተፈለገ መሆኑን ተናግረዋል።

እንዲህ አይነት አደጋዎች የሰርግ ደስታዎች ወደሃዘን እንዳይለወጡ አስቀድመን ቅስቀሳ ስናደርግ ነበር ያሉት ኢንስፔክተር ኦላና፥ ሰሚ በመጥፋቱ ሙሽራ ሊያመጡ የሄዱ ሰርገኞች አስከሬን ተሸክመው ተመለሱ ብለዋል።

በሰርግ ስነ ስርዓት ላይ በሞተር ሳይክል ዚግዛግ ማሽከርከር፣ የተኝከርካሪ የእቃ መጫኛ ላይ ሰው ጭኖ መጓዝ ተዘውትረው የሚፈጸሙ የአደጋ አጋላጮች በመሆናቸው መቆም አለባቸው ሲሉም ያሳስባሉ።

በሙክታር ጣሃ – ኤፍ.ቢ.ሲ

Share your thoughts on this post