fbpx

በደቡብ ክልል ሶስት ከተሞች ሰሞኑን በተፈጠረ ግጭት የ15 ሰዎች ህይወት ማለፉን የክልሉ መንግስት አስታወቀ

በደቡብ ክልል ሃዋሳ፣ ወልቂጤና ወላይታ ከተሞች ሰሞኑን በተፈጠረ ግጭት የ15 ሰዎች ህይወት ማለፉን የክልሉ የኮሙዩኒኬሽም ጉዳዮች ቢሮ አስታውቋል።

የደቡብ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ሃይሉ እንደገለጹት፥ አሁን ላይ ግጭቱ ተከስቶባቸው በነበሩ አካባቢዎች አንጻራዊ ሰላም ሰፍኗል።

ሁኔታዎችን ቀድሞ ወደነበሩበት ሁኔታ ለመመለስ የሚያስችሉ ህዝባዊ ውይይቶች ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።

በሃዋሳ ከተማ ግጭቱ ትናንትና ከትናንት በስቲያ ከነበረው ድባብ በአንጻሩ ዛሬ ሰላም መስፈኑን የሚያሰረዱት አቶ ሰለሞን፥ በሰዎችና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።

በከተማዋ ዳርቻ አካባቢዎች ግን አሁንም ወደ ዝርፊያ ያመሩ አለመረጋጋቶች እየታዩ መሁኑን አመላክተዋል።

ከ2 ቀናት በላይ ይህንኑ ግጭት ያስተናገደችው ሀዋሳ ከተማ የ10 ሰዎች ህይወት ሲጠፋባት 9 ሰዎች ላይ ከባድና 80 ዎቹ ላይ ቀላል ጉዳት ደርሷል፤ ከ 2 ሺ 500 በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውንም ነው የገለጹት።

በወልቂጤ ከተማም የ2 ሰዎች ህይዎት ማለፉንና ግምቱ ያልታወቀ ንብረትም መውደሙ የተገለጸ ሲሆን፥ አሁን ላይ አንፃራ ሰላም መስፈኑን ነው አቶ ሰለሞን የሚናገሩት።

በወላይታ ከተማም በትናንትናው እለት አለመረጋጋቱ የተከሰተ ሲሆን፥ በሰላማዊ ሁኔታ በሰልፍ የተጀመረው ጉዳይ ወደ ግርግርና ሁከት ተቀይሮ ለ3 ሰዎች ህይወት መጥፋት፣ 10 ሰዎች ጉዳትና ንብረትም መውደም ምክንያት ሆኗል ብለዋል።

በእነዚሁ አካባቢዎች በዛሬው ዕለት አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት የተፈጠረ ሲሆን፥ ከሁከትና ግርግሩን ወጥተው ቀድሞ ወደነበሩበት ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስ ህብረተሰቡን የማወያየት ስራ እየተሰራ ነው።

ከዚሁ ጎን ለጎንም የተፈናቀሉ ሰዎችን የመርዳት ስራዎችም እየተሰሩ ነው ተብሏል።

በሁከቱ ተሳታፊ የነበሩ ወንጀለኞችንም ለፍርድ የማቅረብ ስራ እየተሰራ ነው ተብሏል።

በዙፋን ካሳሁን – ኤፍ.ቢ.ሲ

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram