በደሴ ከተማ በደረሰ የኤሌክትሪክ አደጋ ሦስት ሰዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ በአራት ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።
በመምሪያው የ2ኛ ፖሊስ ጣቢያ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር አሳምነው ሙላት ለኢዜአ እንደገለጹት ትናንት እኩለ ቀን ላይ አደጋው የደረሰው በአገር ግዛት ክፍለ ከተማ ኪዳነምህረት እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነው።
አደጋው የደረሰው የመንገድ ላይ የአርማታ ምሰሶ በሚተክሉ ባለሙያዎች ላይ ሲሆን፣ አደጋው የተከሰተው ባለሙያዎቹ ምሰሶውን በሚተክሉበት ወቅት ምሰሶው ከኤሌክትሪክ መስመር ጋር በመገናኛቱ መሆኑን ዋና ኢንስፔክተር አሳምነው ገልጸዋል።
በደረሰው የኤሌክትሪክ አደጋም ሦስት ሰዎች ሕይወታቸው ወዲያውኑ ሲያልፍ በሌሎች በአራት ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሷል።
እንደኃላፊው ገለጻ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ወደ ደሴ ሪፈራል ሆስፒታል ተልከው ሕክምናቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ፡፡
የሟቾቹ አስከሬን ለቤተሰቦቻቸው የተሰጠ ሲሆን የአደጋ መንስኤ የሆነውን ምክንያትና አካል በአግባቡ ለመለየት የምርመራ ቡድን መቋቋሙን አያይዘው መግለጻቸውን የዘገበው አዜአ ነው፡፡
ምንጭ፦ ኢዜአ
Share your thoughts on this post