በየካቲት ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ወደ 15 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ አለ
በየካቲት ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ወደ 15 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ ማለቱን የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ አስታወቀ።
ኤጀንሲው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ መሰረት የዋጋ ግሽበቱ ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር የ2 ነጥብ 5 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
የምግብ ዋጋ ግሽበት ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር ወደ 20 ነጥብ 9 በመቶ ከፍ ያለ ሲሆን፥ ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች ዋጋ ደግሞ ወደ 9 ነጥብ 8 በመቶ ከፍ ብሏል።
በያዝነው ወር ካለፈው ወር ጋር ሲነጻጸር በዚህኛው ወር ከእህል ክፍሎች አብዛኛዎቹ ጭማሪ ያሳዩ ሲሆን፥ የጥራጥሬ፣ የአትከልትና የፍራፍሬ ዋጋ በመጠኑ ጭማሪ ታይቶበታል።
በየካቲት ወር የበርበሬና ቅመማ ቅመም ዋጋ በአንድ ወር ውስጥ ባልተለመደ መልኩ እጥፍ ጭማሪ በማሳየቱ ለዋጋ ግሽበቱ መጨመር አስተዋጽኦ አድርጓል ብሏል ኤጀንሲው።
ሆኖም ሥጋ፣ ወተት፣ አይብና ዕንቁላል ዋጋ ላይ መጠነኛ ቅናሽ ታይቷል።
ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች ደግሞ በጫት፣ አልባሳትና ጫማ፣ የቤት ማደሻ እና ማስዋቢያ ቁሳቁሶች (በተለይ የቤት ክዳን ቆርቆሮ)፣ የሀይል ፍጆታዎች፣ የቤት ውስጥ መገልገያዎች፣ የጤና ወጪ እንዲሁም በሆቴሎች የሚወሰዱ ምግቦችና መጠጦች ላይ ጭማሪ በማሳየቱ ለዋጋ ግሽበቱ መጨመር አስተዋጽኦ እንዳደረገ ኤጀንሲው ገልጿል።
Share your thoughts on this post