fbpx

በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን የምግብ ዋስና ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ም/ጠ/ሚ አቶ ደመቀ መኮንን ገለፁ

የሀገሪቱን የእድገት ጎዳና ከግብ ለማድረስ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙትን የህብረተሰብ ክፍሎች የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለፁ።

የአዲስ አበባ ከተማ ሁለተኛው ዙር የምግብ ዋስትና መርሃ ግብር ዛሬ በይፋ ሲጀመር፥ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ እና ድህነትንም ከስሩ በመናድ ተደማሪ የልማት አቅም መፍጠር እንደሚገባ ተናግረዋል።

መንግስትም የእነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ በበኩላቸው በከተማዋ ከድህነት ወለል በታች ከሚገኙት 600 ሺህ ያህል ዜጎች

ዛሬ የተጀመረውን ጨምሮ ከ320 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች የምግብ ዋስትና ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ ገልፀዋል።

በዛሬው ዕለት በይፋ የተጀመረው የአዲስ አበባ የምግብ ዋስትና መርሃ ግብር በ55 ወረዳዎች የሚገኙ 200 ሺህ ነዋሪችን ተጠቃሚ ያደርጋል።

ከእነዚህም ውስጥ 168 ሺህ የሚሆኑት በአካባቢ ልማት የሚሰማሩ ሲሆን፥ 32 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ ቀጥታ ድጋፍ የሚደረግላቸው ናቸው ተብሏል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚተገበረው ለዚህ የከተሞች ምግብ ዋስትና መርሃ ግብር 450 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ተመድቧል።

ከዚህ ውስጥ 300 ሚሊየን ዶላሩ ከአለም ባንክ በብድር የተገኘ ሲሆን፥ ቀሪው 150 ሚሊየን ዶላር ደግሞ በመንግስት የተመደበ መሆኑንም ታውቋል።

በአጠቃላይ ለመርሃ ግብሩ ማስፈፀሚያ ከተመደበው ከዚህ በጀት ውስጥም 70 በመቶ ያህሉ በአዲስ አበባ ከተማ ለሚተገበረው መርሃ ግብር እንደሚውል ተጠቁሟል።

በመርሃ ግብሩ ያልተካተቱ ሌሎች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የከተማዋ ነዋሪዎችም ወደፊት ተግባራዊ በሚደረጉት የመርሃ ግብሩ እቅዶች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተነግሯል።

በመጀመሪያው ዙር መርሃ ግብር ከታቀፉት የመዲናዋ ነዋሪዎች መካከል 84 በመቶው በማህበረሰብ አቀፍ ልማት ተሰማርተው ገቢ እያገኙ ሲሆን ቀሪዎቹ በቀጥተኛ ድጋፍ ተጠቃሚዎች ናቸው።

በዙፋን ካሳሁን – ኤፍ.ቢ.ሲ

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram