ባህርዳር ፡ታህሳስ 05/2010 ዓ/ም (አብመድ)
የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ደነቀ ምትኩ ለአማራ ብዙኃን መገናኛ እንደገለጹት ቀበሌ 03 በሚገኘው የመገበያያ ቦታ ላይ የሚገኝ አንድ የበርበሬ መጋዝን ትናንት ምሽት በ04/04/2010 ዓ/ም 2፡30 ላይ የእሳት ቃጠሎ እንደደረሰበት አስታውቀዋል፡፡
የእሳት ቃጠሎ መከሰቱ እንደታወቀ የአካባቢው ማህበረሰብ በነቂስ በመውጣት ከከተማ አስተዳደሩ እሳት አደጋና መከላከል፣ከያፒ መርከዚ እና ኤርፖርት እሳት አደጋዎች ጋር በጋራ በመሆን ወደ ሌላ ቦታ ሳይዛመት በቁጥጥር ስር ውሏል ፡፡
ህዝቡ መትረፍ የሚችሉትን በማመላለስ አደጋውን ስለተቆጣጠረው ወደ ሌላ ቦታ ሳይዛመት በቁጥጥር ስር መዋሉን ነው ያረጋገጡት፡፡
ከንቲባ ደነቀ እንዳሉት የእሳት ቃጠሎው ምክንያት በአካባቢው በተከሰተ ኤሌክትሪክ መሳሳብ ነው፡፡
አደጋው የተከሰተው ከአቅማቸው በላይ መሸከም ባልቻሉ ትራንስፈርመሮች በአካባቢው የኤሌክትሪክ መሳሳብ ስላለ፣አቅማቸው ከሚችለው በላይ ሰዎች ከትራንስፈርመሮች ሀይል መሳብ ባይችሉ ይመረጣል፡፡እንዲሁም ተቀጣጣይ ነገሮችን በማስወገድ ድንገተኛ የእሳት ቃጠሎን መከላከል እንዲቻል ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የእሳት አደጋው በደረሰበት ጊዜ የሰው እንቅስቃሴ በአካባቢው ስላልነበር በሰው ላይ ምንም አይነት ጉዳት አልደረሰም ሲሉ ገልጸዋል ፡፡
የአካባቢው ህብረተሰብ እና ቃጠሎውን ለማጥፋት የተሳተፉትን ድርጅቶች ሁሉንም አመስግነዋል፡፡