fbpx
AMHARIC

በአፍሪካ የአህያ ቄራዎች ቢዘጉም እርዱ ቀጥሏል

በኢትዮጵያ በቢሾፍቱ ስራውን ማከናወን ጀምሮ የነበረ የአህያ ቄራ በደረሰበት ተቃውሞ መዘጋቱ ይታወሳል፡፡ በሩቅ ምስራቅ በተለይም በቻይና ከፍተኛ ገበያ አለው ለሚባለው የአህዮች ቆዳ ሲባል የሚደረገው ይህን መሰል እርድ ጋናን ጨምሮ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት እገዳ ቢጣልበትም አህዮችን እያረዱ ወደ ውጭ ሀገር መላክ ግን አሁንም ቀጥሏል፡፡


በምስራቅ ጋና ዶባ ከተማ የአህያ የእርድ አገልግሎት የሚፈጽማባቸው ሶስት ቦታዎች አሉ፡፡ በአንደኛው የእርድ ቦታ ያሉ ሰራተኞች የአህያ ስጋውን በትጋት ይቆራርጣሉ፡፡ ለሽያጭ ዝግጁ እንዲሆን ደግሞ በጪስ ያጥኑታል፡፡ ከእነርሱ መካከል አንዱ የሆነው 29 ዓመቱ ጋብሪየል አያልዞያ አህዮቹን ማረድ ከጀመረ ስድስት ዓመት አስቆጥሯል፡፡ “አህዮች ብቻ አይደሉም፡፡ ላሞች እና አህዮች ናቸው፡፡ ሁሌም ቢሆን እንቀላቅላቸዋለን” ይላል ጋብሪየል ።

በቻይና ለአህያ ቆዳ ያለው ፍላጎት መመንደጉ በጋና እና በሌሎችም የአፍሪካ ሀገራት ያሉ አህያዎች እርድ እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል፡፡ የአህያ ቆዳ ቻይናውያን ለሚያመርቱት ኢጃዮ ለተባለ ባህላዊ መድኃኒት መስሪያ ያገለግላልና ነው ከጋና እስከ ቡርኪፋናሶ፣ ከማሊ እስከ ታንዛንያ በሺህዎች የሚቆጠሩ አህዮች እያታረዱ የሚገኙት፡፡

ኢጃዮ ለእርጅና፣ ለመሃንነት እና ለወሲባዊ ስንፈት ጭምር ፍቱን መድኃኒት ነው ይባልለታል፡፡ ለዚህ መድኃኒት በዋና ግብዓትነት የሚያገለግለው ጊላቲን ከተቀቀለ የአህያ ቆዳ መገኘቱ እንስሳቱን በባትሪ የሚፈለጉ አድርጓቸዋል፡፡ በዶባ የሚገኘው ይህን የእርድ ስፍራን ጨምሮ በጎበኘኋቸው ቄራዎች በቀን በትንሹ 15 አህዮች ያታረዳሉ፡፡ የዶባው ጋብሪየል አህዮችን ከተለያዩ ቦታዎች እንደሚገዙ ይናገራል፡፡ “እዚህ አህዮችን እና ላሞችን እናረባለን፡፡ በቡርኪና ፋሶም የተወሰኑ የሚያረቡ አሉ፡፡ በእኛ ቦታ እጥረት ከገጠመን ወደ ቡርኪና ፋሶ ተጉዘን እንገዛለን” ይላል ጋብሪየል፡፡

የዶባ ነዋሪው አካሶማ ጄምስ እንደ ሌሎቹ የአካባቢው ሰዎች ሁሉ በርካታ አህዮች አሏቸው፡፡ አገልግሎተ ብዙዎቹ አህያዎች በጄምስ ዘንድ ትልቅ ስፍራ አላቸው፡፡ ከማንኛውም ተሸከርካሪ በረከሰ ዋጋ የመጓጓዣ አገልግሎት ከመስጠት፤ ማረሻ እየጎተቱ ማሳቸውን እስከ ማለስለስ ድረስ የኑሯቸው አለኝታ ናቸው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ጄምስ ለአህዮቻቸው ይፈሩላቸው ጀምረዋል፡፡ ለአህዮች ያለው ፍላጎት መጨመሩን ተከትሎ የእንስሳቱ ስርቆትም የዚያኑ ያህል አሻቅቧል፡፡

“የእኔን አህዮች ለመውሰድ ሲፈታተኑን ቆይተዋል፡፡ በቤት ውስጥ፣ በቅጽር ግቢያችን ሳይቀር፡፡ አንዳንዴ እኩለ ለሊት ላይ ይመጡና ሁሉንም ይወስዷቸዋል” ሲል ጄምስ ለዶይቼ ቬለ አስረድቷል።

በቻይና ያለው የአህዮች ብዛት በሀገሪቱ ለእንስሳቱ ያለውን ከፍተኛ ፍላጎት ማሟላት አልቻለም፡፡ ለዚህ አንዱ ምክንያት አህዮችን በቻይና በብዛት ማራባት አስቸጋሪ ስለሆነ ነው፡፡ ከቻይና ጋር ጠንካራ የኢኮኖሚ ትስስር ያላቸው እና አህዮች በብዛት የሚገኙባቸው የአፍሪካ ሀገራት ይህን የፍላጎት እና አቅርቦት አለመጣጠን ለመቅረፍ እንደ አማራጭ ቢወሰዱ ሊገርም አይገባም፡፡ በርካታ አፍሪካውያን የአህያ ባለቤቶች ከእዚህ ከፍ ያለ ፍላጎት በመጀመሪያ ተጠቃሚ እንደነበሩ “ዶንኪ ሳንክቸዋሪ” በተሰኘው የአህዮች ደህንነት ተንከባካቢ ድርጅት የሚሰሩት ሲሞን ፖፕ ይናገራሉ፡፡

“እየተናገርን ያለነው ትርፍ አህዮቻቸውን ስለሸጡ ሰዎች ነው፡፡ አንዳንዶቹ ይህን በፍቃደኝነት ነው ያደረጉት ምክንያቱም ይህን የማድረግ አቅሙ ስለነበራቸው እና ዋጋቸው ሽቅብ በመናሩ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚያን ትርፍ እንስሳት መሸጥ የገንዘብ ማበረታቻ ነበረው” ሲሉ ወደ ኋላ መለስ ብለው ያስታውሳሉ።

ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን አፍሪካውያን በጋጣ ያሏቸውን አህዮች መሸጥ እምቢኝ አሉ፡፡ ይህን ጊዜ ነው የአህዮች ስርቆት እና ከየቦታው ማደን የተስፋፋው፡፡ ይህ ደግሞ በርካታ አፍሪካውያን የህይወታቸው መደገፊያን እንዲያጡ አድርጓቸዋል፡፡ “ሰዎች ጠዋት ከእንቅልፋቸው ሲነቁ አህዮቻቸው ተሰርቀው፣ ታርደው እና ቆዳቸው ተገፎ ያገኛሉ” ይላሉ ፖፕ የስርቆቱን መጠን ሲያስረዱ፡፡

የአህያ ስጋ የሚበልተው በሰሜን ጋና ዋሌ ዋሌ የሚገኘው ፋብሪካን ብቻ ብንወስድ በቀን ከ140 እስከ 150 አህዮች ይፈልጋል፡፡ ፋብሪካው ቀደም ሲል አህዮችን በሀገሬው መገበያያ ከ250 እስከ 450 ሴዲስ በሆነ ዋጋ ያገኝ የነበረ ቢሆንም በስተኋላ ዋጋቸው በእጥፍ በመጨመሩ ስራውን አቁሟል፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ይህ አዲስ ክስተት በጋና ያለውን የአህዮች ቁጥር ክፉኛ አመናምኖታል፡፡ ጋና በጎርጎሮሳዊው 2015 ጋና የነበራት የአህዮች ብዛት 14‚500 እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የአህዮች እርድ ከተጀመረ ወዲህ ግን አህዮች በፍጥነት በመጥፋት ላይ ካሉ እንስሳት ተርታ እንደተሰለፉ የጋና የእንስሳት ጥበቃ እና ተንከባካቢ ማህበር ይፋ አድርጓል፡፡

ይህን አካሄድ ለመቀልበስ ያሰበ የሚመስለው የጋና የምግብ እና እርሻ ሚኒስቴር የአህያ ንግድን ከልክሏል፡፡ ምስራቅ አፍሪካዊቷ ታንዛንያም ተመሳሳይ እርምጃ ወስዳለች፡፡ በግንቦት 2009 ዓ.ም የታንዛንያ የግብርና ሚኒስቴር አህዮችን ከመጥፋት ለመታደግ በሚል የአህዮችን ቄራም ሆነ የውጭ ንግድ አግዷል፡፡ ይህ ኮምጨጭ ያለ እርምጃ ውጤታማ እንደሆነ የዶንኪ ሳንክቹዋሪው ፖፕ ይናገራሉ፡፡

“በታንዛንያ ንግዱ ከታገደ በኋላ ዋጋው ይበልጥ ተመጣጣኝ ወደ መሆን ተመልሷል፡፡ ይህ ማለት አርሶ አደሮች፣ ግለሰቦች እና ሌሎች ማህበረሰቦች አህዮችን መግዛት ይችላሉ፤ ስርቆትንም በከፍተኛ መጠን ይቀንሰዋል ማለት ነው” ባይ ናቸው።

በታንዛንያ ጎረቤት ኬንያ ግን መንግስት የተከተለው የተለየ አካሄድን ነው፡፡ ሶስት የአህያ ቄራዎች ስራቸውን እያከናወኑ በሚገኙባት ኬንያ አሁንም አህዮች ለውጭ ገበያ ይታረዳሉ፡፡ እንደ ሀገሬው መገናኛ ብዙሃን ከሆነ እነዚህ ቄራዎች በቀን እስከ 500 አህዮችን ይበልታሉ፡፡ ይህ የኬንያ መንግስት አካሄድ ከአንድ ወገን ተቃውሞዎችን ቢያስነሳም በሌላኛው ወገን ያሉት የስራ ዕድል የሚፈጥር እና ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኝ በመሆን ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ይበልጥ አስፈላጊ ነው ሲሉ ይከራከራሉ፡፡

እንደ ታንዛንያ ሁሉ በኢትዮጵያም የውጭ ገበያን ታሳቢ አድርጎ የተቋቋመ የአህያ ቄራ እንዲዘጋ ተደርጓል፡፡ ምክንያቱ ግን ለየቅል ነው፡፡  ሻንግ ዶንግ በተሰኘ የቻይና ድርጅት በቢሾፍቱ ስራ ጀምሮ የነበረው የአህያ ቄራ ሳምንታት ሳይሻገር የተዘጋው በአካባቢው ነዋሪዎች ተቃውሞ ነበር፡፡ የአህያ ቄራው በሚገኝበት ቃጂማ በተባለ አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች ድርጊቱ “ባህል እና እሴታችንን የተጻረረ ነው” ሲሉ ድርጅቱ ገና በግንባታ ላይ ሳለ ጭምር ጥቃት ሰንዘረውበታል፡፡ በቀን 200 አህያዎችን አርዶ ለውጭ ገበያ የማቅረብ አቅም አለው የተባለው ድርጅት ቆየት ብሎ ስራ መጀመሩ ሲሰማም ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል፡፡

የቃጂማው የአህያ ቄራ በነዋሪዎች ውትወታ እና ተቃውሞ ከስራ ውጭ እንዲሆን ቢደረግም የአህያ ደህንነት ተንከባካቢው ድርጅት ግን በኢትዮጵያ ያሉ አህዮች ነገር አሁንም ያሳስበዋል፡፡ በኢትዮጵያ የአህያ ቄራ ቢታገድም ጎረቤቷ ኬንያ ቄራዎቹ እንዲሰሩ መፍቀዷ ሀገሪቱ ለወሰደችው እርምጃ እንቅፋት ነው ይላሉ የዶንኪ ሳንክቹወሪው ፖፕ፡፡ “ከእነዚህ ሀገራት አህዮች በህገወጥ መንገድ ወደ ኬንያ ይሸጋገራሉ፡፡ ይህን የቄራዎቹ ባለቤቶች ጭምር የሚናገሩት ሆኗል፡፡ አህዮች እንደልብ ስለማይገኙ እነርሱን የሚያገኙባቸው ቦታዎች ሰፊ ክልል የሚሸፍኑ እና በሌሎች ሀገራት ያሉ እንዲሆን አድርገዋል” ይላሉ ፖፕ፡፡

በጋና እንደ ጄምስ ያሉ የአህያ ባለቤቶች መፍጨርጨራቸውን ቀጥለዋል፡፡ ሀገሪቱ ባለፈው ዓመት ጥር ወር የአህያ ቆዳ ንግድን ብታግድም የእርምጃው ተፈጻሚነት የተልፈሰፈሰ ነው ሲሉ የእንስሳት መብት ተከራካሪዎች ይወቅሳሉ፡፡ የጋና የእንስሳት ጥበቃ እና ተንከባካቢ ማህበር አስተባባሪ  አምባሳ አሉይዛህ ከተቺዎቹ አንዱ ናቸው፡፡ “እንደተለመደው ጋናውያን ይህን በማድረግ የመጀመሪያ ነን በማለት መኩራራት ይፈልጋሉ፡፡ ግን አፈጻጸሙስ? ጉዳዩ ወደ ህጎች የመጣን እንደው አንተገብራቸውም” ሲሉ ይነቅፋሉ።

የዶንኪ ሳንክቹወሪው ፖፕ በበኩላቸው የቻይና እና የአፍሪካ ባለስልጣናት ጊዜው ከመርፈዱ በፊት ለአህዮች ጥበቃ እንዲያደርጉ ያሳስባሉ፡፡ “ለተወሰኑ የአፍሪካ ሀገራት ተጨባጭ የሆነ ከፍተኛ አደጋ ተደቅኖባቸዋል፡፡ ንግዱ በሚቀጥሉት አራት እና አምስት አመታት በዚሁ ከቀጠለ አህያ የሚባል ነገር በሀገራቱ አይኖርም” ሲሉ ፖፕ ያስጠነቅቃሉ።

በቻይና ያሉ የባህላዊ መድኃኒት አምራች ኩባንያዎች የጀመሯቸው የአህዮች ማራባት መርኃ ግብሮች ፍሬ ካፈሩ የአፍሪካ አህዮችን ህልውና ይታደጉት ይሆናል፡፡ ከኩባንያዎቹ አንዱ የሆነው ዶንግ ኢጂያዎ አዳዲስ የማራባት ዘዴዎችን ለማግኘት ምርምር እንደሚያካሄድ ይፋ አድርጓል፡፡ ድርጅቱ ለመድኃኒት ምርቱ የሚያስፈልጉትን አህዮች ለማርባት ተስፋ ያደረገው ከሁለት ዓመት በኋላ በጎርጎሮሳዊው 2020 ነው፡፡ በአፍሪካ ላሉ በርካታ አህዮች እና ባለቤቶቻቸው ግን ያኔ ሁሉም ነገር የዘገየ ይሆናል፡፡

ማክስዌል ሱክ/ ተስፋለም ወልደየስ

ልደት አበበ – DW

 

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram