fbpx
AMHARIC

በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የዱር እንስሳት በ2100 ከመሬት ሊጠፉ ይችላሉ-ጥናት

የአለም የአየር ንብረት ለውጥ ባግባቡ ካልተሰራበት በያዝነው ክፍለ ዘመን መጨረሻ የደን፣ የብዝሃ ህይወትና የዱር እንስሳት ሃብትን በግማሽ ያጠፋል ሲል አዲስ ጥናት አመልክቷል።

በአለም የዱር እንስሳት ሃብት ፈንድ አድራጊነት በኢስት አንግሊያና ጃሜስ ኩክ ዩንቨርሲቲዎች የተሰራው ይህ ጥናት እንደሚያሳየው፥ 60 በመቶ እፅዋትና 50 በመቶው የዱር እንሰሳት በአማዞን፣ ማዳጋስካርና በመላው አለም ዙሪያ በአውሮፓውያኑ 2100 ይጠፋሉ።

ጥናቱ በአለም የአየር ንብረት ለውጥ አማካኝነት በሚፈጠር የመጠጥ ውሃ እጥረት ምክንያትም በሰዎችና እንስሶት መካከል ውጥረት ይፈጠራል ብሏል።

በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የባህር ውሃ መጠን እየጨመረ ሲሄድም በወስጡ ያሉት ዝርያዎች ወደ መሬት እንዲወጡ እና ለአደጋ እንዲጋለጡ ምክንያት ሊሆን ይችላል ተብሏል።

ተመራማሪዎቹ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት ለመመልከት በዓለም ዙርያ 35 በሚሆኑት በተፈጥሮ በጣም የበለጸጉ አካባቢዎች ላይ ወደ 80 ሺህ በሚያህሉ የእፅዋትና የእንስሳት ዝርያዎች ምርምር አካሂደዋል።

በዚህም ሶሰት የተለያዩ የአየር ንብረት ለውጥ ሁኔታ የሚያሳዩ ትንታኔዎች የቀረቡ ሲሆን፥ ይህም በፓሪስ የአየር ንብረት ስምምነት ላይ በተቀመጠው መሰረት የዓለም የሙቀት መጠን በ2 ዲግሪ ሴልሺየስ ከፍ የሚልበት ወቅት ተንብየዋል።

ሌላም በያዝነው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ወደ 3 ነጥብ 2 ዲግሪ ሴልሺየስ ከፍ እንደሚል ተመልክተዋል።

በመጨረሻም የዓለም የሙቀት መጠን 4 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴልሺየስ በሚደርስበት ወቅት፥ ካርቦን ልቀቱ ወደ ላይ እየጨመረ መሄዱን የሚያሳይ ትንበያ ነው በትንታኔው የተካተተው።

በዚህም የጥናቱ ውጤቱ እንደሚያሳየው በአለም አቀፍ ደረጃ የሙቀት መጨመር አማካይ 4 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴልሺየስ ላይ በሚደርስበት ወቅት በተክሎችና በእንስሳት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ይደርስባቸዋል ተብሏል።

ይህም በአማዞን 69 በመቶ የተክል ዝርያዎች የሚጠፉ ይሆናል ነው የተባለው።

 

በተጨማሪም የ3 ነጥብ 2 ዲግሪ ሴልሺየስ የሙቀት መጨመር ሲኖር፥ 50 በመቶ የአማዞን እንስሳት ዝርያዎች እንደሚጠፉ ተጠቁሟል።

ስለሆነም ተመራማሪዎቹ በደንና ብዝሃ ህይወት ሃብት ላይ በከፍተኛ ትኩረት መሰራት ካልተቻለ አደጋው ቅርብ ነው ሲሉ ተንብየዋል።

ለዚህም ሃገራት በአየር ንብረት ለውጥ ላይ መስራትና የአለም የሙቀት መጠንን መቆጣጠር አለባቸው ነው የተባለው።

ምንጭ፥ ፕሬስቲቪ

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram