fbpx

በአሸባሪዎች በግፍ የተገደሉ ኢትዮጵያውያን አጽም ወደ አገራቸው እንዲመጣ ስምምነት ተደርሷል

በሊቢያ በስደት እያሉ በአሸባሪዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸውን ያጡ ኢትዮጵያውያንን አጽም ከተቀበረበት በማውጣት ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ የመጨረሻ እረፍት እንዲያገኝ ለማድረግ ስምምነት ላይ ተደረሰ።

በግብፅ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አል ሲሲ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ ወቅት ትኩረት ሰጥተው ካነሱት ሃሳብ መካከል የዜጎች ከእስር መለቀቅና በአሸባሪዎች በግፍ የተገደሉት አጽማቸው በአገራቸው በክብር እንዲያርፍ የማድረግ ጉዳይ ነው።

የሁለቱን መሪዎች ውይይት የተከታተሉት በግብጽ የኢትዮጵያ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት፤ በሊቢያ በስደት የነበሩና በአሸባሪዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸውን ያጡ ዜጎች አጽማቸው ከተቀበረበት ቦታ ይወጣል።

አጽማቸው የመጨረሻ እረፍት ወደ ሚያገኝበት ኢትዮጵያ እንዲገባ ስምምነት ላይም ተደርሷል።

ለዚህም የግብጽ መንግስትና የጸጥታ ሃይሎች ለመተባበር ሙሉ ፈቃደኝነትና ዝግጅት መኖሩን ፕሬዝዳንቱ መግለጻቸውን አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት ጉዳዩ እልባት ያገኘና ስራው እየተከናወነ መሆኑን አምባሳደር ታዬ አረጋግጠዋል።

በግብጽ በተለያዩ ምክንያቶች ታስረው የቆዩ ኢትዮጵያዊያን ተፈተው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ተወስኗል። በዛሬው ዕለትም በእስር ላይ ከሚገኙት ኢትዮጵያውያን የተወሰኑት እንደተለቀቁ ለማወቅ ተችሏል።

ሁለቱ መሪዎች ውይይታቸው በመግባባት መንፈስ የተከናወነና ውጤታማ መሆኑ ተገልጿል።

ኢዜአ እንደዘገበው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የግብጽ ቆይታቸውን አጠናቀው ዛሬ ወደ አገራቸው ይመለሳሉ።

አይ.ኤስ የተሰኘው ዓለም አቀፍ አሸባሪ ቡድን በሊቢያ በሚኖሩ ስደተኞች ላይ ሚያዚያ 11 ቀን 2007 ዓም በ12 ኢትዮጵያውያን ላይ አሰቃቂ ግድያ መፈጸሙ ይታወሳል።

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram