በአሉ ግርማን ያሳጣን ኦሮማይ ነው!

“እውቁ ደራሲ በዓሉ ግርማ ከቤቱ እንደወጣ የት እንደደረሰ ሳይታወቅ ቀርቷል፡፡ ከጠፋ ከጥቂት ቀናት በኋላ መኪናው መንገድ ላይ ቆማ ተገኝታለች፡፡ ‘ኦሮማይ’ በተባለው መጽሐፉ የተነሳ እንደተገደለ ይገመታል፡፡ ስለዚህ ምን ይላሉ?…” የሚል ነበር መሪ ጥያቄዋ፡፡

ሌ/ኮ መንግሥቱ ለዚህ ጠያቄ ቀጥታ ፈጣን መልስ መስጠት አቅቷቸው ብዙ ሲዋትቱ በመጽሐፉ ውስጥ ይስተዋላሉ፡፡ ከገጽ 211 እስከ ገጽ 219 (የሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ትዝታዎች፣ ቅጽ አንድ፣ 1994 ዓ.ም. ) ድረስ ወለሌ ይላሉ፡፡ ሐቅ እየመጣ ሲተናነቃቸው እውነቱን መቋቋም ሲያቅታቸው ካንዱ ነጥብ ዘለው ወደ ሌላው እየዘለሉ አስገራሚ መልስ ሰጥተዋል፡፡ ሁሉንም እዚህ ላይ ዘርግፎ ማሳየት ያንባቢን ጊዜ መሻማት ነውና፤ ከመልሶቻቸው ውስጥ አንኳር አንኳሩን እየቆነጻጸልኩ ማመልከትን ፈቅጃለሁ፡፡

ሌ/ኮ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም እንዲህ እያሉ መልሰዋል፡፡ “. . . በዓሉ ግርማን የማውቀው ከአብዮቱ በፊት ነበር፡፡ እኔ5 ከአሜሪካን አገር እንደመጣሁ ወደ ሐረር ከመሄዴ በፊት ለጥቂት ቀናት አዲስ አበባ አንድ ሆቴል ውስጥ አርፌ ነበር . . . እዚያ ቦታ ነው በዓሉ ግርማ፣ ብዙነሽ በቀለና እኔ የተዋወቅነው . . . የተሰጠውን የሥራ መመሪያ በእጄ ጽፌ ያረቀቅሁት እኔ ራሴ ነኝ…” እያሉ ከላይ ከተቀመጠው መሪ ጥያቄ ጋር የማይዛመድ መልስ እየመለሱ ሁለት ገጽ ሙሉ ይፈጁብናል፡፡ (የሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ትዝታዎች፣ ቅጽ አንድ፣ 1994 ዓ.ም. ፣ ገጽ 212 – 213) ጠያቂዋ ገነት ቢቸግራት ቀጣዩን ጥያቄ ማስከተሏን ልብ እንላለን፡፡ “ስለዚህ እርስዎ ቀይ ኮከብን በተመለከተ በዓሉ ግርማን መጽሐፍ ጻፍ ብለውታል የሚባለው እውነት ነዋ!?” ስትል ታፋጥጣቸዋለች፡፡ ሌ/ኮ መንግሥቱ ይመልሳሉ፡፡ “አላልኩትም፡፡ እሱ የፕሮፓጋንዳውና የሥነ ጽሑፍ ዘመቻው አካል ነው እንጂ በግሉ እንዲጽፍ የታዘዘው አንድም ነገር የለም… ‘ኦሮማይ’ን ጻፈ፡፡ መጽሐፉን ጽፎ ሲጨርስ ሊያሳትም ሄደ . . . በዓሉ ለሚመለከተው ሁሉ አሳይቷል፡፡ አልፎልኛል ብሎ አሳተመ፡፡ ተሰራጨ . . . ‘መጽሐፉን አምጡልኝ’ አልኩ፡፡ አንድ ሳምንት ፈጀብኘ፡፡ ማታ ማታ ነው የማነበው፡፡ ጭቅጭቅ እንዳስነሳ ስለተነገረኝ በደንብ አድርጌ አንብቤ ጨረስኩት፡፡ እኔን እንዳውም አመሰገነኝ እንጂ አልነቀፈኝም. . .” እያሉ አሁንም ወደ ዋናው ጥያቄው ምላሽ ሳይመጡ ሦስት ገጾች ያስገሸልጡናል፡፡ (የሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ትዝታዎች፣ ቅጽ አንድ፣ 1994 ዓ.ም. ፣ ገጽ 214- 216) ትእግስታችንን ቢፈታተነንም ወደ ፊት ስናዘግም አሁንም ከዳርዳርታ ጋር እንጨዋወታለን፡፡

ሌ/ኮ መንግሥቱ ከገጽ 216 – 219 (የሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ትዝታዎች፣ ቅጽ አንድ፣ 1994 ዓ.ም.) በሰፈረው ምላሻቸው ላይ፤ ረቂቁን እንዲያዩ አስቀድሞ በበዓሉ በራሱ ቀርቦላቸው ባለመመቸት ምክንያት ለማንበብ ያልታደሉትን ሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስን፣ እራሱን በዓሉ ግርማንና በኋላም የደህንነቱን ሚኒስትር ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደ ሥላሴን ጠርተው በየተራ ማነጋገራቸውን ይተርካሉ፡፡ እንዲህ እንዲህ እያሉ. . . “. . .ፍቅረ ሥላሴን አስጠራሁ. . . ‘ይሄ መጽሐፍ እንዴት ታተመ? ከመታተሙ በፊት አይተኸዋል ወይ? ’ አልኩት፡፡ ‘አላነበብኩትም ፡፡ ለቦርዱ ነው ያስተላለፍኩት ’ አለኝ . . . ከዚያ በኋላ በዓሉን እራሱን አስጠራሁት፡፡ ’. . . የብዙ ሰው ደም፣ የብዙ ሰው ላብ፣ የብዙ ሰው ትግል ውጤት ነው፡፡ ያንተ የብቻህ የሥራ ውጤት አይደለም፡፡ ይሄ የኢትዮጵያ አብዮት ታሪክ አካል ስለሆነ አቀናጅተህ ለታሪክ እንዲቀመጥ እንጂ አንተ በስምህ ባለቤት ሆነህ እንደራስህ ሥራ አገጣጥመህ እንዴት በመጽሐፍ ልታወጣ ቻልክ?’ አልኩት፡፡ ‘ይሄ አልገባኝም ነበር፡፡ እንደዚህ ይሆናል ብዬ አላሰብኩም፡፡ አሁን ነገሩን ሳሰላስለው ምን ያህል ስህተት እንደሰራሁ ተረድቻለሁ’ አለ፡፡ አመነ . . .” ይሉናል የቀድሞው ፕሬዚዳንታችን ሌ/ኮ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም፡፡

ጥቂት አንቀጾችን ካጓጓዙን በኋላ ደግሞ “. . . አብዮቱን ለመጉዳት የሠራኸው አለመሆኑን እረዳለሁ፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ባለህበት ኃላፊነት ቦታ የምትቆይበት ሁኔታ ሊኖር አይችልም. . . ለማንኛውም አሁን ወደ ቤትህ ሂድ ብዬ አሰናበትኩት. . .” ካሉ በኋላ፤ ከኮሎኔል ተስፋዬ ወልደ ሥላሴ ጋር ስለነበራቸው ቆይታ ያወጉናል፡፡ “. . .ትንሽ ጊዜ ቆይቶ‘በዓሉ ግርማ ጠፋ’ የሚል ነገር ተነገረኝ፡፡ ተስፋዬ ወልደ ሥላሴ መጥቶ ‘በዓሉ ጠፋ’ አለኝ. . . ‘ወዴት ነው የሄደው?’ ስል፣ ‘እኛ አናውቅም’፡፡ ብቻ ጠፍቷል፡፡’ አለኝ. . . በራሴ መንገድ ለማጣራት ሞከርኩ፡፡ የምጠይቃቸው ሁሉ ’ሰውዬው ብዙ ጠላቶች አፍርቷል፡፡ በትክክል ስለሆነው ነገር የምናውቀው ነገር የለም፡፡ የየራሳችን ጥርጣሬ አለን፡፡ የተጨበጠ መረጃ ግን የለንም’ የሚል መልስ ነው የሚሰጡኝ፡፡ ምን ማድረግ ይቻላል? ከዚያ በኋላ በከተማ ውስጥም ‘በዓሉ ተገድሏል’ በማለት መወራቱ ቀጠለ፡፡ ሕይወትም ቀጠለ፡፡ ሥራም ቀጠለ . . . .’ (የሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ትዝታዎች፣ ቅጽ አንድ፣ 1994 ዓ.ም. ፣ ገጽ 217- 219) ብለው በዓሉን የበላውን ጅብ አለማወቃቸውን በእንዲህ አይነት ፌዘኛ ምላሽ ደምድመውልናል . . . ጓድ ሊቀመንበር!!!!

Share your thoughts on this post

Advertisements
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram