fbpx

በችግር አምጪ ሃሳቦች ችግሮች አይፈቱም!

«የአበው ውብ ብሂል…
ከችግር አላቆ መፍትሄን ቢጠራም
እሾህን በእሾህ ለችግር አይበጅም።
እናም…
መንገዱን ለውጦ
ሌላ ሃሳብ ለማዝመር
ልብ ካልቆረጠ… ከሆነ ስስታም
በችግር አምጪ ሃሳብ ችግሩ አይፈታም»

«እርካብና መንበር» በተሰኘው መጽሐፍ በቀዳሚው ምዕራፍ በመግቢያ ላይ የሰፈረ ወፍራም ሃሳብ ነው። ሃሳቡን እንዲወፍር ያደረገው በቁጥብ ቃላት በስነ-ግጥም መቅረቡ ብቻ ሳይሆን የምዕራፉን ሃሳብ ተሸክሞ መዝለቁ ነው። መልዕክቱም « እሾህን በእሾህ» የሚለውን ብሂል ውድቅ የሚያደርግ ሳይሆን የአባባሎችን አውዱ እንድናስተውል የሚያደርግ ጥልቅ ሃሳብ ነው።

ነገሮች ሲበታተኑ ለማስተካከል ይመቻሉ ይባላል። በማናችንም ህይወት ውስጥ ብዙ ችግሮች ሊከሰቱ ይችላሉ።ያጋጠሙንን ችግሮች የምንፈታባቸው መንገዶች ናቸው ልዩነቱንና ዘላቂነቱን የሚያረጋግጡት። ወይም ደግሞ ችግሮቹን ስንፈታ አንጠልጥለን በይደር የተውናቸው ሃሳቦች ወይም ጉዳዮች ናቸው የችግሮቻችን መፍቻ ስልቶች ብቃት የሚለኩት።

ችግሮችን ለመፍታት የምናደርጋቸው ስሌቶች ሁሉ ወደ አንድ ወገን ያዘነበሉ የሚሆኑበት መንገድ ብዙ ነው። ምክንያቱ ደግሞ የችግሩ አካል ሁሉ ችግሮችን ለመፍታት የመፍትሄ ሃሳብ ሊኖራቸው እንደሚችል ባለማመን ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ብቸኛው አማራጭ የችግሩን ምንጮች የመፍትሄው አካል የማድረግ ብቃት ነው። ለዚህም ነው የችግሮችን ምንጭ ማወቅ መፍትሄ ለመፈለግ ግማሽ መንገድ እንደመሄድ ይቆጠራል የሚባለው።

ሀገራችን በበርካታ ችግሮች ውስጥ በርካታ የችግር መፍቻ ስልቶችን እየቀየሰች ዓመታትን ተሻግራለች። ሁልጊዜም ችግሮቿን ለመፍታት የምትወስዳቸው አማራጮች ጊዜያዊ መፍትሄን ያመጣሉ እንጂ ዘላቂ የማይሆኑበት አጋጣሚ ብዙ ነው። በመሆኑም አንዱን ችግር ስንፈታ ሌላው እየተተካ ከችግሮች ጋር ዘመናትን ተጉዘናል።

ዳኒስ ዋሊ የተባለ ፀሐፊ ‹‹በሕይወት ውስጥ ያሉን ቀዳሚ ምርጫዎች ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛው ሁኔታህን አምነህ መቀበል፤ ሁለተኛው ደግሞ ሁኔታዎችህን ለመለወጥ ኃላፊነትን መውሰድ›› ነው ይላል። በመሆኑም አሁን ያለውን ሀገራዊ ሁኔታ በመረዳት ከገዘፈው የመደመር አስተሳሰብ ጋር አዛምደንና አዋህደን ኃላፊነታችንን መወጣት ከቻልን ችግሮቻችንን በዘላቂነት መፍታት እንችላለን።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የመደመርን ፅንስ ሃሳብ ይዘው ሲመጡ ብዙዎቻችን እንደወረደ ነበር የተቀበልነው።አሁንም ድረስ መደመርን በትክክለኛው አስተሳሰብ የተረዳው የህብረተሰብ ከፍል ብዙ ነው ለማለት አያስደፍርም። ምክንያቱም አሁንም የመደመርን ስሌት በተንሻፈፈ አረዳድ ተረድተው የቃል ተደማሪ የሆኑ ብዙዎች አልጠፉም። በመደመር ስሌት ውስጥ የገዘፈው ፅንስ ሃሳብ በፍቅር፣በአንድነት፣ በይቅር ባይነት፣ ጠቃሚ ያልሆነውን ኋላቀር አስተሳሰብ በማስቀረት፤ በአንድ ሃሳብ ለአንድ ለሀገር ዕድገት መስራት ሲቻል ነው የችግር መፍቻው ስልት ዘላቂ የሚሆነው።

ባለፉት ጥቂት ወራት በመደመር ስሌት የፍቅርና የምስጋና ቀን መድረስ ከሚገባን ማማ የሚያደርሰንን የመጀመሪያ ጡብ አስቀምጠናል። የመደመር ስሌት አብሳሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለዚህም ነው «ዛሬ ያለ ትናንት ዋጋ የላትም፡፡ የዛሬ መሰረታችን ትናንት ነው። አገራችን የብዝሃነት አገር ናት፡፡ ይህን ብዝሃነት ማክበርና መቀበል ሲቻል ኢትዮጵያዊነት ይለመልማል፡፡ ድህነትን የማሸነፊያ አቅም ይጎለብታል፡፡…ያለምንም መመዘኛ የተዋደዳችሁ እለት ያኔ እኔንና ከእኔ ጋር ሌት ከቀን የሚተጉ ባልደረባዎቼን እንዳመሰገናችኋቸው ይቆጠራል» ያሉት፡፡

መደመር ከቃል ይልቅ በተግባር የሚገለጥ ጥልቅ እሳቤ ነው። እንዲሁም ያሉብንን ውስብስብ ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል የአንድነት ማጠንከሪያ የገዘፈ ቃል ነው። ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያን ወደ ቀደመው ገናናነቷ እንደምትመለስ ተስፋን ሰንቀናል። ወደ ብልፅግና መሻገሪያው ድልድይ ይቅርታ፣ ፍቅርና መደመር ነው ብለናል። ፍቅር እየተሰበከ ፣ ሌብነት እየተወገዘ ሁሉም ለሥራ እንዲነሳ አገሩን እንዲያለማ ጥሪ ቀርቦልናል። ከኛ የሚጠበቀው በእርግጥም የተደመርን መሆናችንን የምናሳየው የበለፀገች ኢትዮጵያን ለማየት የሚጠበቅብንን ጡብ በፍቅር ስናስቀምጥ ብቻ ነው።

አንድ የሚያደርገን ያለፈውን ችግር ለመፍታት ተመራጭ የሆነው አስተሳሰብ «እሾህን በሾህ» ዓይነት ዘዴ አለመሆኑን መረዳታችን ነው። በመደመር እሳቤ ሁሉም ሰው በአስተሳሰብ አንድ እንዲሆን አይጠበቅም። ትልቁ እውነት ለአንድ አላማ መነሳትን ማስቀደሙ ላይ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ « ችግሩን በፈጠረው አስተሳሰብ፣ ችግርን መፍታት አይቻልም» በማለት አልበርት አንስታይን ዋቢ አድርገው መግለፃቸውም ካለምክንያት አይደለም። በመጠላላትና በመጠላለፍ የሚፈታ ችግር አይኖርም። ችግሮቻችን ከልብ መፍታት ከፈለግን ያለፈውን ጠባሳ ረስተን በአዲስ መንፈስ ለመለወጥ መጣር ይኖርብናል።

የመደመር ጥያቄ ለብሄሮችና ለዜጎች ብቻ የተተወ አይደለም። በሁሉም ሙያ ላይ የተሰማራን ዜጋ ሁሉ ያገባናል! ይመለከታል! ልንል ይገባል። ያኔ ነው በችግር አምጭ ሃሳቦች ችግሮች እንደማይፈቱ እርግጠኛ የምንሆነው! ያኔ ነው የመደመር እሳቤ የሚገዝፈው። ያኔ ነው ኢትዮጵያም ወደቀደመው ገናና ስሟ የምትመለሰው። ያኔ ነው ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለአንዲት የበለፀገች ኢትዮጵያ ግንባታ ባቀበለው ጡብ ልክ በኩራት አንገቱን ቀና የሚያደርገው። ያኔ ነው ለህዝቡ ትልቅ ተስፋና አቅም የሚፈጠረው።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram