በትግራይ ክልል በየደረጃው እየተካሄደ ያለውን የጥልቅ ተሀድሶ ግምገማ ተከትሎ ህዝባዊ ኮንፈረንስ ለማካሄድ ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል አስታወቁ፡፡
ምክትል ርዕስ መስተዳድሩ ይህን ይሉት በክልሉ በመካሄድ ላይ ያለውን የጥልቅ ተሀድሶ ንቅናቄና ሌሎች ጉዳዮችን አስመልክቶ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡
ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በየደረጃው እያካሄደ ያለው የጥልቅ ተሀድሶ ግምገማ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በየደረጃው በሚገኙ አመራሮችና የመንግስት ሠራተኞች የተካሄደው ግምገማዊ ኮንፈረንስ ህወሓትና ህዝቡን ወደ አንድ አስተሳሰብ ለማምጣት የረዳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከእዚህ በመነሳት በቅርቡ የሁሉም ብሔሮችና ብሔረሰቦች ተወካዮችን ያሳተፈ ህዝባዊ ኮንፍረንስ በመቀሌ ከተማ ለማካሄድ ዝግጅት መደረጉን ነው ዶክተር ደብረጽዮን የገለጹት፡፡
” ኮንፈረንሱ ህዝቦችን እርስ በራሳቸው ለማስተሳሰር ከፍትኛ ፋይዳ አለው” ብለዋል፡፡
የምሁራንና ወጣቶች ኮንፍረንስም በተመሳሰይ መንገድ ቀጥሎ እንደሚካሄድም አመልክተዋል፡፡
ድርጅቱ ባካሄደው ኮንፈረንስ ከምሁራን ጋር ተቀራርቦ ለመስራት በገባው ቃል መሰረት በርካታ ምሁራኖች በጥናትና በምርምር ድርጅቱን ለማገዝ ፍላጎት ማሰየታቸውን አስረድተዋል።
አስካሁን በተለያዩ ሙያዎች ጥናትና ምርምር ለማካሄድ 12 ርዕሶች ተለይተው ወደ ተግባር ለማሸጋገር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ዶክተር ደበረጽዮን ገልፀዋል፡፡