በባህርዳር ከተማ በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚከፋፈሉ 100 የመኖሪያ ቤቶች እየተገነቡ ነው
ባህር ዳር መጋቢት 12/2010 በባህርዳር ከተማ አስተዳደር በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚከፋፈሉ 100 የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ መጀመሩን የከተማው ቤቶች ልማትና አስተዳደር ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ባይነሳኝ ዘገየ ለኢዜአ እንደገለጹት ከተማ አስተዳደሩ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ነዋሪዎችን የቤት አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ አስተዳደሩ ካለፈው ዓመት ጀምሮ እየሰራ ነው።
ለቤቶቹ ግንባታ ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦ እየተሰራ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም በግንቦት 20 ክፍለ ከተማ የ14 መኖሪያ ቤቶች ግንባታ መጀመሩን ተናግረዋል።
እየተገነቡ ያሉት መኖሪያ ቤቶች እያንዳንዳቸው ሳሎንና መኝታ ቤት የጋራ መታጠቢያና መፀዳጃ ቤትን ያሟሉ እንደሚሆኑ አስረድተዋል።
በሁለተኛው ዙር ከሚገነቡት መኖሪያ ቤቶች መካከል 86ቱ በብሎኬት የተቀሩት ደግሞ በእንጨትና ጭቃ እንደሚገነቡ ጠቁመዋል።
የቀሪ ቤቶችን ግንባታ በቅርቡ በማስጀመርም ግንባታቸውን እስከ ቀጣዩ ዓመት አጋማሽ ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ ለተጠቃሚዎች እንደሚከፋፈል አስታውቀዋል፡፡
”ቤቶቹ በአነስተኛ ክፍያ የቤት ችግር ላለባቸውና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ነዋሪዎች በዕጣ የሚተላለፉ ይሆናል” ብለዋል።
የቤቶቹ ግንባታ በዋናነት እየተከናወነ ያለው በኢንጅነሪንግ ትምህርት ዘርፍ ከዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቀው በማህበር በተደራጁ ወጣቶች አማካኝነት ነው።
በግንባታው ከተሰማሩ ማህበራት መካከል ክቡር ምስጋናውና ጓደኞቻቸው የህብረት ሽርክና ማህበር አስተባባሪ ወጣት ክቡር ተባባል 14 ቤቶችን በቡሎኬት ለመገንባት ውል ወስደው እየሰሩ ነው።
ግንባታውን አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ እያከናወኑ መሆኑን ጠቁመው፤ በገቡት ውል መሰረት እስከ ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም ገንብተው ለማጠናቀቅ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጿል።
በመጀመሪያው ዙር በተገነቡ ቤቶች የዕጣ ዕድለኛ የሆኑት አቶ ሰማኽኝ ሞላ በሰጡት አስተያየት ከነበረባቸው የቤት ችግር መላቀቅ እንደቻሉ አስረድተዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ባመቻቸው ዕድል ተጠቃሚ በመሆናቸውም ያለምንም ችግር ልጆቻቸውን እንዲያስተዳድሩ አስችሏቸዋል።
አስተዳደሩ ባለፈው ዓመት በ10 ሚሊዮን ብር የጀመራቸውን 86 መኖሪያ ቤቶች በተያዘው ዓመት አጋማሽ ገንብቶ በማጠናቀቅ የቤት ችግር ላለባቸው ዝቅተኛ ነዋሪዎች በዕጣ ማስተላለፉ ይታወሳል።