fbpx

በሳዑዲ አረቢያ በእስር ላይ ከሚገኙት ኢትዮጵያውያን ውስጥ 1 ሺህ ያህሉ ከነገ ጀምሮ ይለቀቃሉ

በሳዑዲ አረቢያ በእስር ላይ ከሚገኙት ኢትዮጵያውያን ውስጥ 1 ሺህ ያህሉ ከነገ ጀምሮ እንደሚለቀቁ ተገለፀ።

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከሳዑዲ አረቢያ በስልክ እንደተናገሩት፥ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሳዑዲ አረቢያ ጉብኝት በአጠቃላይ ስኬታማ ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ጉብኝት አንዱ እና ዋነኛ አላማው አድርጎ የነበረው የዜጎች መብት እና ከለላ ጉዳይ መሆኑንም አቶ አህመድ ተናግረዋል።

በዚህ ረገድም በተለያዩ እስር ቤቶች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከእስር እንዲለቀቁ ከስምምነት መደረሱን አንስተው፥ በዚህም 1 ሺህ ኢትዮጵያውያን ከነገ ጀምሮ ከተለያዩ እስር ቤቶች እንዲለቀቁ ትእዛዝ ተላልፏል ብለዋል።

ከእነዚህም ውስጥ 900 ወንዶች እና 100 ደግሞ ሴቶች መሆናቸውን የተናገሩት አቶ አህመድ፥ በቀጣይም ዜጎቹ ወደ ሀገራቸው የሚመለሱ ይሆናል ብለዋል።

አቶ አህመድ ሽዴ አክለውም፥ የሳዑዲ አረቢያ መንግስት በግብርና፣ በቱሪዝም እና በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ኢትዮጵያ ውስጥ ለመሳተፍም ከስምምነት መደረሱን አቶ አህመድ ተናግረዋል።

ለዚህም ይረዳ ዘንድ በቅርቡ የሳዑዲ አረቢያ መንግስት የኢንቨስትመንት ቡድን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣም አስታውቀዋል።

ሽብርተኝነትን በመዋጋት ዘርፍም ሁለቱ ሀገራት ተባብረው ለመስራት መስማማታቸውን አቶ አህመድ ገልፀዋል።

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram