fbpx
AMHARIC

በርካታ የኮንዶሚኒየም ተመዝጋቢዎች ቁጠባቸውን እያቋረጡ ነው

  • የውጭ ኮንትራክተሮችን ለማስገባት በድጋሚ አጀንዳ ይቀርባል

የኮንዶሚኒየም ቤቶች ባለቤት ለመሆን ከ900 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎች የተመዘገቡ ቢሆንም፣ አብዛኞቹ ወርኃዊ ቁጠባቸውን እያቋረጡ መሆኑ ታወቀ፡፡

የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ነዋሪዎቹ ቁጠባቸውን የሚያቋርጡት ከአቅም ጋር በተያያዘ ከሆነ ምርጫቸውን ማስተካከል እንደሚችሉ አስታውቋል፡፡

የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር እየተጓተተ ያለውን የጋራ ቤቶች ግንባታ ለማፋጠን፣ የውጭ ኮንትራክተሮችን በኢትዮጵያ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ ውስጥ ለማስገባት እንዲፈቀድ በድጋሚ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጋር ለመነጋገር ዕቅድ መያዙ ተገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ1996 ዓ.ም. በድጋሚ በ2005 ዓ.ም. ባስተዋወቃቸው አራት የመኖሪያ ቤቶች መርሐ ግብሮች፣ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ቤት ፈላጊዎች ተመዝግበዋል፡፡

በተለይ በ20/80 እና በ40/60 መኖሪያ ቤቶች ፕሮግራሞች ከ900 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች ተመዝግበው ዕድላቸውን በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡

የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር አምባቸው መኰንን (ዶ/ር) ረቡዕ የካቲት 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፣ 624 ሺሕ ተመዝጋቢዎች ቁጠባቸውን እያቆራረጡ ነው፡፡ ቁጠባቸውን በትክክል እየቆጠቡ የሚገኙት ደግሞ ከ100 ሺሕ አይበልጡም ብለዋል፡፡ ሕጉ በስድስት ወራት ቁጠባቸውን ያቋረጡ ይሰረዛሉ ስለሚል ተመዝጋቢዎች በአግባቡ እንዲቆጥቡ አሳስበዋል፡፡

‹‹ምዝገባው በሚካሄድበት ወቅት ለባለሦስት መኝታና ለባለሁለት መኝታ የተመዘገቡ ይኖራሉ፡፡ ተመዝጋቢዎቹ በሒደት አቅማቸው ከተፈተነ ምርጫቸውን ማስተካከል ይችላሉ፤›› ሲሉ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በሁለቱም ፕሮግራሞች መንግሥት የሚያካሂደው የቤቶች ግንባታ የሚቀጥል ሆኖ፣ ነገር ግን ለፍጥነት ሲባል በኅብረት ሥራ ማኅበራት ተደራጅተው ቤታቸውን መገንባት የሚፈልጉ የሚስተናገዱበት ዕድል መመቻቸቱን አስረድተዋል፡፡

ከሁለቱ ማለትም ከ20/80 እና ከ40/60 መርሐ ግብሮች ወጥተው በማኅበር ለመደራጀት የሚፈልጉ ተመዝጋቢዎች፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሕጉን አሻሽሎ ለማስተናገድ ዝግጀት እያደረገ መሆኑንም ሚኒስትሩ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በመኖሪያ ቤቶች መንግሥት እየተፈተነባቸው ከሚገኝባቸው ጉዳዮች መካከል ዋነኛው፣ በዕቅዱ መሠረት ግንባታ ማካሄድ አለመቻሉ ነው፡፡

በ2008 ዓ.ም. የሥራ አፈጻጸሙ ደካማ የሆነበት ምክንያት የገንዘብ አቅርቦት አነስተኛ ሲሆን፣ በ2010 ዓ.ም. ደግሞ የኮንትራክተሮች አቅም ደካማ መሆን ምክንያት ሆኖ ቀርቧል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው የአዲስ አበባ ቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ለሚያሳትመው ‹‹ቁጠባ ቤቶች›› መጽሔት እንደገለጹት፣ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ በ1996 ዓ.ም. ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ 300 ሺሕ ቤቶች ሲገነቡ፣ 175 ሺሕ ቤቶች ለተጠቃሚዎች መተላለፋቸውን፣ 136 ሺሕ የሚሆኑት ደግሞ በመገንባት ላይ ናቸው፡፡

ነገር ግን በተመዝጋቢዎች መብዛትና ለተጠቃሚዎች በሚተላለፉ ቤቶች ቁጥር መካከል ከፍተኛ ክፍተት ከመኖሩ በላይ፣ ተመዝግበው ለሚጠባበቁ አዳርሶ ለመጨረስ ከ50 ዓመት ያላነሰ ጊዜ  ይፈጃል እየተባለ ነው፡፡

ይኼ አካሄድ ሥጋት የሆነበት መንግሥት ቀደም ብሎ ከአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች በተጨማሪ የውጭ ኮንትራክተሮችን ለማስገባት ወስኖ ነበር፡፡

በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ዓለም አቀፍ ጨረታ ያወጣ ሲሆን፣ በዚህ ጨረታ 28 የውጭና የአገር ውስጥ ደረጃ አንድ ኮንትራክተሮች ተሳትፈው ነበር፡፡ ከዚህ ውስጥ 14 የሚሆኑት ተለይተውም ነበር፡፡

የቀድሞ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር አቶ መኩሪያ ኃይሌ በ18 ወራት ውስጥ 80 ሺሕ ቤቶችን የሚገነቡ የውጭ ኩባንያዎች በቅርቡ ይገባሉ ሲሉ በጥቅምት 2008 ዓ.ም. መናገራቸው አይዘነጋም፡፡

ነገር ግን መንግሥት ይኼን ጉዳይ ከተመለከተ በኋላ በድጋሚ ሐሳቡን በመቀየር የውጭ ኩባንያዎች በዚህ ሥራ ማስገባት ኢኮኖሚውን (የውጭ ምንዛሪውን) ወደ ውጭ እንዲወጣ ማድረግ ነው በማለት ሰርዞታል፡፡

ይኼንን ጉዳይ በተመለከተ የአሁኑ ሚኒስትር ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ የእርሳቸው ማኔጅመንት ከመምጣቱ በፊት መንግሥት ይኼንን ጉዳይ የዘጋ ቢሆንም፣ በጉዳዩ ላይ በድጋሚ ከመንግሥት ጋር እንደሚነጋገሩበት አስታውቀዋል፡፡

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram