fbpx

HT

ሐበሻ ታይምስ ሚዲያ

AMHARIC

በሞያሌ አካባቢ ተፈጥሮ የነበረውን የፀጥታ ችግር በመስጋት ወደ ኬንያ የገቡ ከ7 እስከ 8 ሺህ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያንን ለመመለስ እየተሰራ ነው – ኮማንድ ፖስቱ

(ኤፍ ቢ ሲ) በሞያሌ አካባቢ ተፈጥሮ የነበረውን የፀጥታ ችግር በመስጋት ወደ ኬንያ የገቡ ከ7 እስከ 8 ሺህ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን የአስቸካይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት ገለፀ።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል አሰፋ አብዮ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫው ላይ እነዚህን ዜጎች ወደ ሀገራቸው ለመመለስ መንግስት የተለያዩ ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

አያይዘውም ሰሞኑን በሀገሪቱ ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር በስፋት መታየቱን አንስተዋል።

ኮማንድ ፖስቱ ከህዝቡ ጋር በመሆን ባለፉት ቀናት በመቶዎቹ የሚቆጠሩ የተለያየ አይነት የጦር መሳሪያዎች እና እስከ 20 ሺህ የሚጠጉ ጥይቶች መያዝ መቻሉንም ነው ያመለከቱት።

በጎረቤት ሀገራት ያለው የፀጥታ ችግር እና የውጭ ሀይሎች በሀገር ውስጥ ተፈጥሮ የነበረውን ሁከትና ብጥብጥ በጦር መሳሪያ ለመደገፍ መፈለጋቸው ለህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውሩ መበራከት ምክንያት ሆነዋል ነው ያሉት።

ኮሚሽነር ጀነራሉ በመግለጫቸው በቀጣይ በሃገሪቱ የጦር መሳሪያ አያያዝና አጠቃቀምን በሚመለከት የህግ ማዕቀፍ ለማውጣት ስራዎች መጀመራቸውን ጠቅሰዋል።

የህግ ማዕቀፉ ጦር መሳሪያ የሚይዘውን ግለሰብ ማንነት፣ የአያያዝ ሁኔታ፣ የጦር መሳሪያው የሚያዝበት ቦታና ጊዜን የሚወስን መሆኑንም ነው የጠቀሱት።

በቀጣይም የህግ ማዕቀፉ ለሚመለከተው አካል ቀርቦ ተግባራዊ እንደሚደረግም አስታውቀዋል።

ከዚህ ቀደም የጦር መሳሪያ አያያዝን በተመለከተ ጠንካራ የህግ ማዕቀፍ ባለመኖሩና ህብረተሰቡ ለጦር መሳሪያ ያለው አመለካከት ለህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር በር መክፈቱን አስታውሰዋል።

ጸረ ሰላም ሃይሎች የሁከትና ብጥብጥ ውዥንብሮችን በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች በመንዛታቸው ህብረተሰቡ ስጋት ውስጥ ወድቋል ነው ያሉት ጀነራሉ በመግለጫቸው።

አሁን ላይም የህብረተሰቡን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል ይህን ድርጊት በሚፈጽሙ አካላት ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁንና አዋጁን ለማስተግበር የወጣውን መመሪያ በመተላለፍ እስካሁን በቁጥጥር ስር ከዋሉ ሰዎች መካከል ግማሽ የሚሆኑት ተመክረው መለቀቃቸውን ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ ተረጋግቶ መደበኛ ህይወቱን እንዲቀጥል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ከዚህ ባለፈም ጸረ ሰላም ሃይሎችን በማጋለጥና የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመግታት መረጃ በመስጠት እያደረገ ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram