fbpx

በምስራቅ ሐረርጌ ዞን የሕዝብ ጥያቄዎችን አልመለሱም የተባሉ 272 አመራሮች ከኃላፊነታቸው ተነሱ

የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የሕዝብ ጥያቄዎችን አልመለሱም ያላቸውን 272 አመራሮች ከኃላፊነት ማንሳቱን የምስራቅ ሐረርጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ እንደገለጹት ከኃላፊነት የተነሱት የአመራር አካላት በዞንና በወረዳ ሲሰሩ የነበሩ ናቸው ብለዋል።

የአመራር አካላቱ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ የተደረገው በዞኑ ለ20 ቀናት በተካሄደ የተሃድሶ ግምገማ መሰረት ሂስና ግለ ሂስ በማድረግ ኃላፊነታቸውን ብበቃት አለመወጣታቸውን ከስምምነት በመድረሱ መሆኑን ተናግረዋል።

በተሃድሶ ግምገማው የአመራር አካላቱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄን አለመመለስ፣ በኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ውስጥ መዘፈቅ፣ በፕሮጀክት ግንባታ ሥራዎች የአፈጻጸም ጉድለት ማሳየት፣ እንዲሁም የህግ የበላይነትን አለማስከበርን ጨምሮ በሌሎች የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሥራዎች ላይ ድክመት ማሳየታቸውን አቶ ታረቀኝ ገልጸዋል።

አስተዳዳሪው እንዳሉት የግምገማ ሂደቱን ከዞን እስከ ወረዳና ቀበሌ ድረስ በማውረድ ህዝቡ እንዲወያይበትና ሀሳብ እንዲሰጥበት የተደረገ ሲሆን፥ የአመራሮችን ብቃትና ጥንካሬን የመለየት ስራም ተከናውኗል።

በምትካቸው አዲስ ከተሾሙት አመራሮች መካከል 261ዱ በዞኑ ባሉ 24 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደር በአመራርነት የሚሰሩ ሲሆን፥ ቀሪዎቹ 11ዱ በዞን ደረጃ የተሾሙ መሆናቸው አመልክተዋል።

ኦህዴድ የህዝቡን የልማት ጥያቄ በሚገባ በመረዳት ጥንካሬዎቹን ለማስቀጠልና ደካማ ጎኖቹን ለማረም እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ከልማቱ ጋር እኩል እያደገ የመጣውን የህዝብ ጥያቄ በአግባቡ ለማስተናገድም ድርጅቱ የጀመረውን የአሰራር ስርዓት ለውጥ በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።

ድርጅቱ ያደረገው የጥልቅ ተሀድሶ ግምገማ መልካም መሆኑን የገለጹት የሐረማያ ወረዳ ነዋሪ አቶ አብዲ ኢብራሂም በበኩላቸው “እንደዚህ ዓይነት ስር ነቀል ለውጥ ሲደረግ ለመጀመርያ ጊዜ ነው፤ ይህ ደግሞ ለህብረተሰቡ ለውጥ ያመጣል ብዬ አምናለው” ብለዋል።

አዳዲስ የተሾሙትም ሆኑ ነባር አመራሮች የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮችን ለመፍታት ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

 

 

 

ምንጭ፦ኢዜአ

Share your thoughts on this post
%d bloggers like this:
Visit Us On TwitterVisit Us On YoutubeVisit Us On Instagram