በማህበራዊ ሚዲያ የጥፋት መልዕክት በሚያስተላልፉ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ
የጥፋት ተልዕኮ ይዘው አሉባልታና የውሸት መልዕክት በማህበራዊ ሚዲያ በሚያስተላልፉ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት አስታወቀ።
ከተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት አካላት የተዋቀረ ቡድን ከሞያሌ ወደ ኬኒያ የተሰደዱ ዜጎችን የማስመለስና የማረጋጋት ስራ እየሰራ መሆኑም ተገልጿል።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል አሰፋ አብዩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት መግለጫን ዛሬ ለጋዜጠኞች በገለጹበት ወቅት፤ አንዳንድ አካላት ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም በተለይ የነዳጅ አቅርቦትን ለማስተጓጎል ከመቼውም በላይ በመንቀሳቀስ ያልተገባ መረጃ እያሰራጩ መሆናቸውን አብራርተዋል። ይህም ነዳጅ በማመላለስ የተሰማሩ አካላት ላይ ስጋት ፈጥሯል።
በመሆኑም ኮማንድ ፖስቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሚፈቅደው አግባብ ይህን የጥፋት ተልዕኮ ለማስፈጸም በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ “የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ ይቀጥላል” ነው ያሉት።
ህብረተሰቡ ይህን በመገንዘብ መደበኛ ስራውን ካለ ስጋት መቀጠል እንዳለበት ኮሚሽነር ጄነራሉ አስገንዝበዋል።
በአንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረውን አለመረጋጋት ወደ ደም አፋሳሽ ግጭት ለመቀየር ወደ አገር ውስጥ የሚገባ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመሩንም ገልጸዋል።
ካለፈው ሁለት ወር ወዲህ ብቻ በመቶዎች የሚቆጠር ህገ ወጥ መሳሪያ በቁጥጥር ስር መዋሉንም ለአብነት ጠቁመዋል።
ኮማንድ ፖስቱ ህገ ወጥ መሳሪያዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል በሚያደርገው እንቅስቃሴ ማህበረሰቡ ድጋፍ እንዲያደርግና ለአገር ሰላም ዘብ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።
ከዚህ አኳያ “የኢትዮጵያን ሰላም የማይፈልገው የሻዕቢያ መንግስት ከመቼውም በላይ አገራችንን ለማተራመስ እየሰራ ነው” ሲሉም ኮሚሽነር ጄነራሉ ተናግረዋል።
“በመሆኑም ሁሉም ኢትዮጵያዊ በተለይ በድንበር አካባቢ ያሉ ወገኖች የሻዕቢያ ተልዕኮ እንዳይሳካ እንደተለመደው ከጸጥታ አካላት ጋር እጅና ጓንት ሆነው እየሰሩ ነው” ብለዋል።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በቁጥጥር ስር የዋሉ አካላት ጉዳያቸው እየተጣራ መሆኑን የተናገሩት ኮሚሽነር ጄነራሉ፤ “በቀጣይ ጊዜውን ጠብቆ ምን ያህል ሰዎች አዋጁን ተላልፈው በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ለህዝብ ይፋ ይሆናል” ብለዋል።
በሌላ ዜና ሞያሌ አካባቢ በተፈጠረው አለመረጋጋት ወደ ኬኒያ የተሰደዱ ዜጎችን ለማስመለስ ከፌደራልና ክልሎች የተወጣጣ ቡድን ተዋቅሮ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቁመዋል።
ቡድኑም ዜጎች ወደ ቀዬአቸው ተመልሰው የቀደመ ኑሯቸውን እንዲመሩ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን የተናገሩት ኮሚሽነር ጀነራል አሰፋ፤ እስካሁን ባለው ሂደትም ወደ አገራቸው የተመለሱ ዜጎች መኖራቸውን አውስተዋል።